1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የነሐሴ 4 ቀን፣ 2012 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ዓርብ፣ ነሐሴ 8 2012

ባየር ሙይንሽን በሻምፒዮንስ ሊጉም ድል ተጎናጽፎ ዘንድሮ ሦስተኛ ዋንጫውን ለማንሳት ግስጋሴውን ተያይዟል። አጥቂው ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ ግብ አዳኝነቱን ቀጥሏል። ኤር ቤ ላይፕሲሽ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ይፋለማል። የአውሮጳ ሊግ የሩብ ፍጻሜ ግጥሚያም ዛሬ እና ረቡዕ ይከናወናል፤ አንድ የጀርመን ቡድን ተጋጣሚ ነው።

Fußball UEFA Champions League I FC Bayern Muenchen v Chelsea FC
ምስል Getty Images/M. Hangst

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

የጀርመኑ ኤር ቤ ላይፕሲሽ ሐሙስ ማታ ከአትሌቲኮ ማድሪድ፤ እንዲሁም በቡንደስሊጋው እና በጀርመን እግር ኳስ ማኅበር የዘንድሮ የዋንጫ ባለቤቱ ባየር ሙይንሽን ከባርሴሎና ጋር ዐርብ ይጋጠማሉ። ለአውሮጳ ሊግ ሩብ ፍጻሜ ደግሞ የጀርመኑ ባየር ሌቨርኩሰን የጣሊያኑ ኢንተር ሚላንን የሚገጥመው ዛሬ ማታ ነው።  ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ ሊያቀና ነው ሲባልለት የነበረው ጄዶን ሳንቾ ከቦሩስያ ዶርትሙንድ የቡድን አባላቱ ጋር ዛሬ ለልምምድ ወደ ባድ ራጋትስ አቅንቷል። በፎርሙላ አንድ 70ኛ ዓመት በዓል የሲልቨርስቶን ፉክክር የማርሴዲሱ ሌዊስ ሐሚልተን በሬድ ቡል አሽከርካሪ ማክስ ፈርሽታፓን ተበለጠ። በዘንድሮ ውድድር መርሴዲስ ለመጀመሪያ ጊዜ ድል ርቆታል። 

የሻምፒዮንስ ሊግ

ምስል picture-alliance/SvenSimon/F. Hörmann

በሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ የመልስ ግጥሚያ ባየር ሙይንሽን ቸልሲን እንደተጠበቀው በሰፋ ልዩነት አሸንፎታል። ቸልሲ የተሸነፈው 4 ለ 1ሲኾን፤ በደርሶ መልስ ውጤቱ 7 ለ1 የኾነ ሰፊ የግብ ልዩነት ነበር። በፖርቹጋል ሊዛቦን ከተማ በሚከናወኑ የግማሽ እና የፍጻሜ ግጥሚያዎች እንደ በፊቱ የደርሶ መልስ ግጥሚያ አይኖርም። በኮሮና ተሐዋሲ መዛመት የተነሳ ውድድሮቹ በአንድ ዙር ጥሎ ማለፍ ነው የሚከናወኑት።

ለሩብ ፍጻሜው ያለፉ ቡድኖች አትሌቲኮ ማድሪድ፣ ፓሪስ ሳንጀርሜን፣ አትላንታ፤ ላይፕሲሽ፤ ባየር ሙይንሽን፣ ባርሴሎና፤ ኦሎምፒክ ሊዮን እና ማንቸስተር ሲቲ ናቸው። በዚህም መሠረት በግማሽ ፍጻሜው፦ ባየርሙይንሽን ከባርሴሎና፤ ኤር ቤ ላይፕሲሽ ከአትሌቲኮ ማድሪድ፤ ማንቸስተር ሲቲ ከኦሎምፒክ ሊዮን፤ አታላንታ ቤርጋሞ ከፓሪስ ሴንጄርሜን ይፋለማሉ።

ኤር ላይፕሲሽ ከአትሌቲኮ ማድሪድ

የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎችም ረቡዕ ዕለት፦ አታላንታ ቤርጋሞ ከፓሪስ ሴንጄርሜን፤ ሐሙስ፦ ኤር ቤ ላይፕሲሽ ከአትሌቲኮ ማድሪድ፤ ዐርብ፦ ባየርሙይንሽን ከባርሴሎና፤ እንዲሁም ቅዳሜ ዕለት፦ ማንቸስተር ሲቲ ከኦሎምፒክ ሊዮን ይከናወናሉ።

ምስል Imago Images/firo Sportphoto/M. Engelbrecht

ኤር ቤ ላይፕሲሽ ለቀጣዩ ግጥሚያው ቅዳሜ ዕለት ወደ ሊዛቦን አቅንቷል። ላይፕሲሽ ፖርቹጋል ውስጥ በቂ የረፍት ጊዜ ለመውሰድ አቅዶ ነው አስቀድሞ የተጓዘው። ተጋጣሚው አትሌቲኮ ማድሪድ በቡድኑ ኹለት ሰዎች ላይ የኮሮና ተሐዋሲ መገኘቱ ቅዳሜ ዕለት ከተነገረ በኋላ ቡድኑ ውስጥ መረበሽ ተከስቷል።

ኤር ቤ ላይፕሲሽ ቅዳሜ ዕለት ያረፈው ከሊዛቦን ከተማ በስተምዕራብ በሚገኘው ኤስቶሪል (Estoril) የተሰኘው ዘመናይ ሆቴል ውስጥ ነው። ቡድኑም በኹለተኛ ዲቪዚዮን ተሳታፊ በኾነው እና ከከተማው ኹለት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ፕራዪያ ኤስቶሪል ስታዲየም ውስጥ ነው ልምምዱን የሚያከናውነው።

የኤር ቤ ላይፕሲሽ አሰልጣኝ ዩሊያን ናግልስማን ወደ ሊዛቦን ከመብረራቸው በፊት ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፦ «ወደ ሩብ ፍጻሜ በመግባታችን በጣም ደስ ብሎኛል። አንድ ኹለት ዙር ለማለፍም እንጥራለን» ብለዋል። ኹለት ዙር ማለት እንግዲህ የዋንጫ ፍጻሜ ማለት ነው። በእርግጥ አሰልጣኙ እንዳሉት ኤር ቤ ላይፕሲሾች ለዚያ ይደርሳሉ ወይ? ያጠራጥራል።  ተፋላሚው አትሌቲኮ ማድሪድ በአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ከፍተኛ ልምድ ያለው ብርቱ ተፎካካሪ ነው።

የአትሌቲኮ ማድሪድ ተሐዋሲው የተገኘባቸው ኹለት ሰዎች በአኹኑ ወቅት ራሳቸውን ከሰው ለይተው ቤት ውስጥ ተቀምጠዋል።  ማንነታቸው ግን አልተገለጠም። ከእነሱ ጋር የተገናኙ ሰዎችም ዳግም ምርመራ ይደረግላቸዋል ተብሏል። በአጠቃላይ ምርመራ የተደረገው ለ93 ሰዎች ነበር። ተጨማሪ ሰዎች ላይ የኮሮና ተሐዋሲ ከተገኘ ምናልባት በኹለቱ ቡድኖች መካከል የሚደረገው ውድድር ለሌላ ጊዜ ሊተላለፍም ይችል ይኾናል።  አትሌቲኮ ማድሪድ ስለ ኮሮናው ጉዳይ ለአውሮጳ እግር ኳስ ማኅበራት ኅብረት (UEFA) ብሎም ለስፔን እና ፖርቹጋል የእግር ኳስ  እና የጤና ባለሥልጣናት ማሳወቊን ይፋ አድርጓል።

ምስል picture-alliance/dpa/S. Stein

የኮሮና ተሐዋሲ በአውሮጳ የበጋ ረፍት ወቅት ሊባባስ እንደሚችል ነው የሚነገረው። ስቱዲዮዋችን በሚገኝበት በቦን ከተማ እና አካባቢው ብቻ እንኳን በአኹኑ ወቅት 112 ሰዎች በኮሮና ተሐዋሲ ተጠቅተዋል። በዚሁ አካባቢ እስካኹን ድረስ 1578 ሰዎች በኮሮና ተሐዋሲ ተጠቅተው 1441ዱ አገግመዋል። በጀርመን በአጠቃላይ ደግሞ 216.327 ሰዎች በተሐዋሲው ተጠቅተው 207,130 አገግመዋል። የሟቾች ቊጥር በአጠቃላይ 9.197 ነው።

ባለፈው ወር  የአትሌቲኮ ማድሪድ ተቀናቃኝ ሪያል ማድሪድ አጥቂ ማሪያኖ ሲያዝ በኮቪድ-19 ተጠቅቶ ነበር። በእርግጥ አኹን ሪያል ማድሪድ ከውድድሩ ተሰናብቷል። ሴቪላ በአኹኑ ወቅት ስሙ ያልተጠቀሰ አንድ ተጨዋቹ በኮሮና መጠቃቱ ተገልጧል። ሴቪላ በሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ባይኾንም በአውሮጳ ሊግ ለሩብ ፍጻሜ ተጋጣሚ ነው። የእንግሊዙን ዎልቭስ ዱይስቡርግ ጀርመን ውስጥ ነገ የሚጋጠመው። ዛሬ ማታ በተመሳሳይ ሰአት ማንቸስተር ዩናይትድ ከኮፐንሃገን ጋር ይፋለማል።  ከነገ በስተያ የሚጫወቱት፦ ሻካታር ዶኒዬትስክ ከባዝል እንዲሁም  ዎልቨርሐምፕተን ከሴቪላ ናቸው።

ባየር ሙይንሽን

ባየር ሙይንሽን በሻምፒዮንስ ሊጉም ድል ተጎናጽፎ ዘንድሮ ሦስተኛ ዋንጫውን ለማንሳት ግስጋሴውን ተያይዟል። አጥቂው ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ ግብ አዳኝነቱን ቀጥሏል።  ቸልሲን 4 ለ1 ባሸነፉበት ግጥሚያ 2 ግቦችን ያስቆጠረው ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ በ13 ከመረብ ያረፉ ኳሶች በሻምፒዮንስ ሊጉ ግብ አዳኝነቱን አስጠብቋል።

ምስል Getty Images/M. Hangst

የቦሩስያ ዶርትሙንዱ ኧርሊንግ ሃላንድ በ10 ግቦች ኹለተኛ ደረጃን ይዟል። ሌላኛው የባየር ሙይንሽኑ ሠርጌ ግናብሬ ከሌሎች አምስት ተጨዋቾች ጋር የሦስተኛ ደረጃን ይዟል። የጁቬንቱሱ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በ4 ግቦች ከእነ ቲሞ ቬርነር እና ሌሎች 9 ተጨዋቾች ጋር 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የናፖሊ ተከላካዮችን አርበድብዶ ድንቅ ግብ ከመረብ ያሳረፈው የባርሴሎናው ሊዮኔል ሜሲ 3 ግቦች አሉት። ከኮከብ ግብ አግቢነት ፉክክሩ እጅግ ርቆ 16ኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው። ሌሎች 11 ተጨዋቾችም በተመሳሳይ 3 ግቦችን ከመረብ አሳርፈዋል።

የጄዶን ሳንቾ ወደ እንግሊዙ ማንቸስተር ዩናይትድ ሊዘዋወር ነው ሲባል የነበረው ግምት ዛሬ ውድቅ የኾነ መስሏል።  ጄዶን ሳንቾ ከሌሎቹ የቦሩስያ ዶርትሙንድ ተጨዋቾች ጋር ለልምምድ ወደ ባድ ራጋትሳ ማቅናቱ ዝውውሩ እውን አለመኾኑን አመላካች ኾኗል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ለሳንቾ ዝውውር ማንቸስተር ዩናይትድን 120 ሚሊዮን ዩሮ ነበር የጠየቀው።

ምስል Getty Images/L. Baron

የቦሩስያ ዶርትሙንድ ኃላፊ ክፍያውን ቡድናቸው ወደ ልምምድ ሜዳ እስኪመለስ ድረስ እንዲፈጸም ቀነ ቀጠሮ አስቀምጠው ነበር። ክፍያውም ሳይፈጸም፤ ዝውውሩም ሳይከናወን ጄደን ሳንቾ ዛሬ ወደ ልምምድ ሜዳ አቅንቷል። ከአራት ዓመት በፊት በ7,8 ሚሊዮን ዩሮ ክፍያ ብቻ ከማንቸስተር ሲቲ ወደ ቦሩስያ ዶርትሙንድ የተዘዋወረው ጄዶን ሳንቾ በዛሬው ልምምዱ ለቦሩስያ ዶርትሙንድ አራተኛ የጨዋታ ዘመንም ተሰላፊ መኾኑን አመላክቷል።

ባለፉት ሦስት የጨዋታ ዘመኖቹም ለቦሩስያ ዶርትሙንድ ለ78 ጊዜያት በቡንደስሊጋው ተሰልፏል። በእነዚህ ጊዜያት 30 ግቦችን ከመረብ ማሳረፍ ሲችል፤ 39 ግቦች እንዲቆጠሩ ኳስ አመቻችቷል። ዘንድሮ በተጠናቀቀው የቡንደስሊጋ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ደግሞ 32 ጊዜ ተሰልፎ 17 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ፤ 17 ግቦች እንዲቆጠሩ ማመቻቸት ችሏል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከሻምፒዮንስ ሊግ እስኪሰናበት ድረስም ለ15 ጊዜያት ተሰልፎ እንደ ባርሴሎናው ብርቅዬ አጥቂ ሊዮኔል ሜሲ በተመሳሳይ ሦስት ግቦችን አስቆጥሯል። በዚህ ኹሉ እንቅስቃሴው ታዲያ ጄዶን ሳንቾ 20ኛ ዓመቱን የደፈነው ከአራት ወር ከዐሥራ አምስት ቀናት በፊት ነበር።

ፎርሙላ አንድ

በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም 70ኛ ዓመት ፉክክር የሬድ ቡሉ አሽከርካሪ ማክስ ፈርሽታፓን ሌዊስ ሐሚልተን በተከታታይ ድል እንዳያስመዘግብ አድርጎታል። ፈርሽታፓን ከትናንቱ ድሉ ጋር ተደምሮ ለዘጠነኛ ጊዜ ማሸነፍ ችሏል።

ምስል Reuters/F. Augstein

ሲልቨርስቶን ውስጥ የሙቀት መጠኑ 44 ሴንቲ ግሬድ በደረሰበት ፉክክር የመርሴዲሶቹ አሽከርካሪዎች ሌዊስ ሐሚልተን እና ባልደረባው ቫልተሪስ ቦታስ የኹለተኛ እና የሦስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል። የፌራሪው አሽከርካሪ ጀርመናዊው ሠባስቲያን ፌትል 12ኛ ደረጃን ይዞ ጨርሷ ል። ሌዊስ ሐሚልተንን ጨምሮ በሲልቨርስቶኑ ሽቅድምድም በርካታ ተወዳዳሪዎች ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ በነበረው ሙቀት የተሽከርካሪዎቻቸው ጎማዎች ላይ ችግር ተከስቶ ነበር።

በውድድሩ ሌዊስ ሐሚልተን እና ባልደረባው ቫለሪ ቦታስ ቀዳሚ ነበሩ። አራተኛ ኾኖ ውድድሩን የጀመረው ማክስ ፈርሻታፓን ሦስተኛ ደረጃን የያዘው የመጀመሪያው ማዕዘን ላይ ነበር። ተረጋግቶ በማሽከርከርም ልክ የመርሴዲስ ተፎካካሪዎቹ ችግር ሲስተዋልባቸው በማፈትለክ  ለድል መብቃት ችሏል። ሌዊስ ሐሚልተን ለአሸናፊው ሬድ ቡል ቡድን እንኳን ደስ ያላችሁ በማለት እንደእነሱ በውድድሩ ሬድ ቡል ብርቱ የጎማ ችግር እንዳልገጠመው ተናግሯል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW