1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የነዳጅ እጥረቱ በአማራ ክልል በርካቶችን ለኑሮ መመሰቃቀል ዳርጓል ተባለ

ኢሳያስ ገላው
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 21 2018

በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው የነዳጅ እጥረት አሽከርካሪዎችን ለከፋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መዳረጉ ተገለጸ። አሽከርካሪዎች፣ ከሁለት ሳምንት እስከ አንድ ወር ለሚደርስ ጊዜ ስራ በማቆማቸው ለቤት ኪራይና ለዕለት ጉርስ መቸገራቸውን ተናግረዋል።

Äthiopien Dessie 2026 | Treibstoffknappheit & hohe Preise in der Amhara-Region
ምስል፦ Esayas Gelaw/DW

በአማራ ክልል በነዳጅ እጠረት የአሽከርካሪዎች ምሬት

This browser does not support the audio element.

በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው የነዳጅ እጥረት አሽከርካሪዎችን ለከፋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መዳረጉ ተገለጸ። በወልድያና በደሴ ከተሞች አስተያየታቸውን የሰጡ አሽከርካሪዎች፣ ከሁለት ሳምንት እስከ አንድ ወር ለሚደርስ ጊዜ ስራ በማቆማቸው ለቤት ኪራይና ለዕለት ጉርስ መቸገራቸውን ገልጸው፤ ችግሩ ቤተሰባዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት እስከማይችሉ ድረስ ክፉኛ እንደጎዳቸው በምሬት ተናግረዋል።

መነሻውን የሰሜን ወሎዋን ከተማ ወልድያ አድርጎ ወደተለያዩ አካባቢዎች የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጠው ወጣት አሽከርካሪም ከሁለት ሳምንታት በላይ ምንም ነዳጅ ሳያገኝ መቆሙን ይናገራል።

‘’በምን እገልጸዋለሁ? በወሬው ችግሬን አሳንሰዋለሁ፣ ምንም ቃል የለኝም ወንድም አለም። ማርያምን! እንዲያው ቤት በገባሁ ቁጥር እኔ ሚስቴን እየሸሸሁ መኪና ላይ ማደር ጀምሬያለሁ። የምትበደረው ሰው እንኳ የለህም፣ ገባህ? ስለሚጎድል በቃ ላለመጠየቅ መኪና ላይ እስከማደር፣ የተሰልፈክበት ቦታ እስከማደር ደርሰናል እኛ። እንዴት ብለን እናግኝ? በማህበር በቀን ሁለት መኪና ነው ያሉን፤ በቀን ሁለት መኪና እንዴት እንዴት እንደሚሰጥ ለራሱ አናውቅም። መናገርም አትችልም ወንድም አለም። አሁን ከተቀመጥኩኝ 25 ቀን አለፈ።’’

ሌላኛው መነሻውን ደሴ ከተማ ያደረገ አሽከርካሪም ከነዳጅ አቅርቦት እጥረት ጋር ተያይዞ ከአንድ ወር በላይ ያለ ስራ መቆሙን ገልጾ የቀጣዩ ጊዜ እንደሚያሳስበው ነው የሚገልጸው።

‘’እዚህ ሾፌርነት አለም ላይ ያለ ልጅ አለው፣ ቤተሰብ የሚመራ፣ የቤት ኪራይ ያለበት አለበት። እሺ በቃ? እኔ አሁን ከአንድ ወር በላይ ሆነኝ ካቆምኩኝ ማለት ነው።  ያለን ነገር አሁን እየጨረስን ነው። ወደፊት ምን እንደሚመጣ አናውቅም በቃ። የቤት ኪራይ አለ፣ የአከራይ ፊት እያየን ነው አሁን።

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ቦታ ያሉ በርካታ አሽከርካሪዎች ያለ ስራ ቆመዋል የሚለው አሽከርካሪም፣ የተወሰኑ መኪኖች ብቻ እንቅስቃሴ ላይ ናቸው፤ ነዳጅ ከየት እንደሚያመጡ ግን አናውቅም ይላል።

‘’ ብዙሃኑ ሾፌር ቆሟል። ከየት እንደሚያመጡት አላውቅም፣ እሱን ሲዞሩት ብቻሲንቀሳቀሱ እናያለን። ቁጭ ብለን እኛ እናያለን። በማህበር እስከሚደርስ ድረስ ይሄው ዝም ብለን እጃችን አጣጥፈን ፀሀይ እየሞቅ ነው አሁን ለራሱ ተሰብስበን ይሄው።’’

አሁን በመንግስት በኩል ነዳጅን ለታለመለት አላማ ለማዋል ሲባል በሚደረግ ቁጥጥር የመንግስት መኪና አሽከርካሪዎችና ከባድ መኪኖች ናቸው ተጠቃሚዎች የሚሉት አሽከርካሪም፣ ለእነርሱ የገቢ ምንጭ ሆኗቸዋል፣ በቀላሉ ነዳጅ ማግኘት መቻላቸው ይላሉ።

መነሻውን ደሴ ከተማ ያደረገ አሽከርካሪም ከነዳጅ አቅርቦት እጥረት ጋር ተያይዞ ከአንድ ወር በላይ ያለ ስራ መቆሙን ምስል፦ Esayas Gelaw/DW

‘’ ለፀጥታ ሃይል እና ለምናምን የጠቀመው እጥረቱ ። ሾፌር አሁን ሃያ ቀንም የሚቆም አለ በቃ። አንድማደያ ላይ ማለት ነው። አንድ ቦቴ ተራግፎ 50 ምናምን ነዉ የሚይዘው፣ አይሸጥም፣ 50 ሺህ አይሸጥም። ወደ 25 ሺህ  ተሸጦ በኋላ ያለው ወደ ብላክ ይሄዳል። አዎ፣ ሁለተኛ የመንግስት መኪና እና ቦቴ ናቸው አሁን ሁለቴ ሶስቴ እየቀዱ ሄዱና ይሸጡ ይመጣሉ እሱ ማለት ነው። አንተ እዚህ ቆመህ ታፈጣለህ።’’

በደቡብ ወሎ ዞን መንገድ ትራንስፖርት ሎጂስቲክ መምሪያ ሃላፊ የሆኑት አቶ ኢብራሂም አህመድም ከታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ እየወሰዱ ቢሆንም፣ ህዝቡ ግን በራሱ የታሪፍ ጭማሪውን እየተከላከለ አይደለም ይላሉ።

‘’ ቢያንስ ቢያንስ ህዝቡን ዉጭ እንኳ ቢያስቸግሩት እኛ ጋር ታሪፍ አይጨምሩም፣ ታሪፍም አይጨምሩም እኛ ባለንበት ላይ። ራሱ ይጨምርላቸዋል። እኛ ካስመለስንለት በኋላ ብር በእጁ ከያዘ በኋላ፣ ትንሽ አለፍ ካለ በፍቃደኝነት ይጨምራል። ተገዶ ሳይሆን የሚጨምረው በራሳቸዉ አንዳንዱ።’’

በበርካታ የክልሉ ከተሞች ያሉ አሽከርካሪዎች ለቀናት ከዚያም ለሳምንታት ተሰልፈን ነዳጅ ማግኘት ባለመቻላችን ኑሯችን ተቃወሰ በሚሉበት ሁኔታ፣ ነዳጅን በፍትሃዊነት ለማድረስ ሃላፊነት የተሰጠው የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ይህንን ችግር ለመፍታት ምን እየሰራ ነው ብለን ለመጠየቅ ለቢሮ ምክትል ሃላፊ ስልክ ብንደውልም፣ መልዕክት ብናስቀምጥም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም። ነገር ግን በአማራ ክልል ጠቅላይ ፖሊስ የትራፊክ ደህንነት ዋና መምሪያ ሃላፊ የሆኑት ኮማንደር በቀለ አብዬ አሁን በክልሉ ምንም የነዳጅ እጥረት የለም፣ አሽከርካሪዎች የሚፈጥሩት ችግር ነው ይላሉ።

‘’ በኖርማል ህዝብ ሊያገለግል ቀድቶ አንዳንዱ በብላክ ማርኬት ይሸጥ ነበረ። ይህንንም እንደዚህ አይነት አኳኋን የሚያመጡትም ራሳቸው ናቸው። አንዳንድ አልፎ አልፎ ከአንዳንድ ማደያ ጋር በፊት እየተቀናጁ። አሁን ግን ጥብቅ ቁጥጥር ስለሆነ አንደኛ የነዳጅ ችግር የለም አሁን። የአጠቃቀም ችግር ነበረ እሱም ተስተካክሏል። መጀመሪያው ላይ ይሄ ችግሩ እጥረቱ እንደተፈጠረ እንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ነበሩ የሚነሱ። በኋላ ግን ማደያ ላይም በትክክለኛው አገልግሎት እንዲሰጥ ክትትል እየተደረገ፣ የተቀዳው ነዳጅም በትክክል ለህዝብ አገልግሎት ስለመዋሉ  ቁጥጥርና ክትትል እየተደረገ ስለሆነ አሁን እንደዛ የሚሉት ነገር የለም ።’’
ኢሳያስ ገላው
ታምራት ዲንሳ
ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW