1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የነዳጅ እጥረትና የጥቁር ገበያ መስፋፋት በአማራ ክልል

ሐሙስ፣ መጋቢት 12 2016

በአማራ ክልል ያሉ አሽከርካሪዎች ለከፍተኛ የነዳጅ እጥረት በመጋለጣቸው ሥራቸውን ማከናወን እንዳልቻሉ ተናገሩ ።

አማራ ክልል አሽከርካሪዎች በነዳጅ እጥረት እና በጥቁር ገበያ ተማረዋል
አማራ ክልል አሽከርካሪዎች በነዳጅ እጥረት እና በጥቁር ገበያ ተማረዋልምስል Alemnew Mekonnen/DW

የነዳጅ ግብይቱን ጥቁር ገበያው ተቆጣጥሮታል

This browser does not support the audio element.

በአማራ ክልል ያሉ አሽከርካሪዎች ለከፍተኛ የነዳጅ እጥረት በመጋለጣቸው  ሥራቸውን ማከናወን እንዳልቻሉ ተናገሩ ። አሽከርካሪዎቹ ለቀናት ሰልፍ በመያዝ ከማደያዎች ነዳጅ ለመቅዳት የሚያደርጉት ጥረትም ውጤት እንደሌለው ገልጠዋል ።   የነዳጅ ግብይቱን ጥቁር ገበያው ተቆጣጥሮታል ይላሉ ። የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ በበኩሉ ለነዳጅ አቅርቦት ሦስት መሰረታዊ ችግሮች እንዳጋጠሙት አመልክቷል ። ሆኖም አቅርቦቱን ለማስተካከልና ሕገወጥነትን ለመከላከል ሥራዎች ተጀምረዋልም ብሏል ። በአማራ ክልል ከ280 በላይ የነዳጅ ማደያ ጣቢያዎች እንደሚገኙ 253ቱ በሥራ ላይ እንዳሉ ይነገራል ።

በአማራ ክልል ከተሞች ረጃጅም የተሸከርካሪዎችን ሰልፎች መመልከት እየተለመደ መጥቷል፡፡ ነዳጅ እንደልብ አይገኝም፣ ነዳጁ ቢኖርም ግብቱን ጥቁር ገበያው ተቆጣጥሮታል ነው የሚሉት አሽከርካሪዎች፡፡

በባህር ዳር ከተማ ነዳጅ ለመቅዳት ትናንት ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምረው የተሰለፉ አንድ አሽከርካሪ እስከ ቀኑ 11 ሰዓት ድረስ ሲንገላቱ መዋላቸውን ይናገራሉ፣ ያውም ገና ነዳጅ የጫነ ቦቴ ይገባል በሚል ተስፋ፡፡

"ልዩ የነዳጅ መቅጃ የፈቃድ መታወቂያ (ኩፖን) ያላቸውም አሉ እነሱም ቢሆን አይቀዱም፣ የሆነ አሰራር አለ መሰለኝ፣ እኛ ያ ልዩ የነዳጅ መቅጃ መታወቂያ የለንም፣ መቅጃ ፈቃድ ያላቸው መታወቂያ አምጡ ይባላሉ ግን የተወሰነ ነዳጅ ከተቀዳ በኋላ አቁሟል ይባላል፣ የተወሰነ መኪና ይቀዳል ከዚያ በኋላ የለም ይባላል፣ ባለፈቃዶቹን ማለት ነው፣ አሁን እኔ ጠዋት 12 ሰዓት ነው መጥቼ የተሰለፍኩት ገና ነዳጅ ይመጣል ተብሎ እየጠበቅሁ ነው፡፡” ነው ያሉት፡፡

ሌላ አስተያየት ሰጪ አሽከርካሪ በበኩለቸው "ነዳጅ የለም ቢባልም በጥቁር ገበያው ግን በከፍተኛ ዋጋ እየተሸጠ ነው” ብለዋል፣ እንደአስተያየተ ሰጪው ችግሩ የቁጥጥር ማነስ ነው፡፡

"...የነዳጅ እጥረት አጠቃላይ በሰው ኑሮ ላይ ከባድ ጫና እየፈጠረ ነው፣ ነዳጅ የለም ይባላል ወጣ ስትል ግን በጥቁር ገበያው ላይ ታገኛለህ፣ ከየት እንደሚመጣ አይገባንም፣ በማደያዎች አካባቢ የቁጥጥርና ክትትል ማነስ አለ፣ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ፣ ገቢዎች ቢሮ ተከታትለው ማደያዎች በስርዓት እንዲሰሩ ማድረግ ሲገባቸው ያን አላደረጉም፣ ጥቁር ገበያ ላይ አለ ማደያ ላይ የለም፣ በጥቁር ገበያ ላይ የተሰማሩት ከየት እያገኙት ነው? አሁን ቤንዚን 2 ሊትር 450 ብር በጥቁር ገበያ እየተሸጠ ነው፡፡”

በጥቁር ገበያ ላይ የተሰማሩት ከየት እያገኙት ነው? ነዋሪዎች ይጠይቃሉ ።ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የቁጥጥርና ክትትል አለመኖር ለጥቁር ገበያ ማንሰራራት መንገድ ከፍቷል የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ አንዳንድ ማደያዎችም ቢሆን ይህን ህገወጥነት እንደ ዋና የገቢ ምንጭ አድርገውታል ይላሉ፡፡

አስተያት ሰጪው አክለውም፣ "በጥቁር ገበያው 2 ሊትር ቤንዚን ከ350 ብር በላይ ይሸጣል፣ 77 ብር በሊትር መሸጥ የነበረበት ነው ወደ 175 ብር በሊትር እየተሸጠ ያለው፣ አንዱ ሊትር 175 ብር ከተሸጠ 90 ብር ያክል በአንድ ሊትር በህገወጥ መንገድ ጭማሪ ያሳያል ማለት ነው፤ ከአንድ ቦቴ ነዳጅ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር በህገወጥነት መንገድ ሸጦ ትርፍ ያገኛል (አንድ ቦቴ ነዳጅ 45 ሺህ ሊትር ነዳጅ ይዛል)፡፡ ስለዚህ ህጋዊው መንገድ አይመረጥም፡፡ ለዚህ ዋናው ተጠያቂ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ነው”

አጠቃላይ የነዳጅ ግብይቱ በዝቅተኛ ነዋሪው ላይ ጫና እንዲፈጠርበት እያደረገ በመሆኑ የሚመለከተው የንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ማደያ ከማሸግ ባለፈ በባለሙያዎች ታግዞ ግብይቱን እንዲቆጣጠር አስተያየት ሰጪዎቹ ጠይቀዋል፡፡

"... "ዋጋ ጨምረህ ሸጠሀል፣ እንዲህ አድርገሀል” ብሎ ማደያ ማሸግ መፍትሔ አይደለም፤ መፍትሔው ከማሸግ ይልቅ ባለሙያ መድቦ በተቆረጠለት ዋጋ እንዲሸት ማድረግ ነው፤ 400 ሊትር የሚጠቀም አሽከርካሪ ለምሳሌ ከ20 ሺህ ብር በላይ በጥቁር ገበያ ጭማሪ አድርጎ ይገዛል፣ በአንድ ጉዞ ላይ ይህን ያክል ጭማሪ ካመጣብህ ያን ለማካካስ ከሸቀትህ ላይ ዋጋ ጨምረህ ትሸጣለህ፣ ያ ደግሞ ጫናውን ወደ ህብረተሰቡ ላይ እንዲሆን ያደርጋል፡፡” ሲሉ አስተያየታቸውን ገልጣዋል፡፡

አንድ በአማራ ክልል የሚገኙ የነዳጅ ማደያ ባለሀብት ለዶይቼ ቬሌ እንደነገሩት ደግሞ ለነዳጅ እጥረት ምክንያቱ ነዳጅ በተፈለገው ጊዜ ከወደብ ማምጣት ባለመቻሉ ነው፡፡

የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ኢብራሂም መሐመድ ለነዳጅ እጥረቱ 3 መሰረታዊ ምክንያቶች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡

እንደ ዶ/ር ኢብራሂም፣ ነዳጅ በአቅርቦቱ ላይ መጠነኛ ማስተካከያ ሊያስፈልግ ይቻል ይሆናል በ3 ነገሮች ግን ተጎድተናል ይላሉ፤

ሕገወጦች ከአንድ ቦቴ ነዳጅ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር በሕገወጥ መንገድ ሸጠው አላግባብ ትርፍ ያጋብሳሉ ምስል Alemnew Mekonnen/DW

1)     "በስፋት በየከተማው ነዳጅ ያቀርቡ የነበሩ ባለሀብቶች በየመንገዱ በሚደርስባቸው ወከባና በአሽከርካሪዎቻቸው ላይ በሚደርስ እንግልት በተሽከርካሪዎቻቸው ላይ በሚደርስ ጉዳትና በሌሎች ምክንያቶች ወደ ስራውን ላለመሰማራት ፍላጎት ማሳየት፣

2)    በአንድናድ አካባቢዎች ላይ በተፈጠረ የፀጥታ ችግር ምክንት የነዳጅ አቅራቢዎች እንቅስቃሴ መገደብ፣

3)    ነዳጅ በየከተሞች ከደረሰ በኋላ ነዳጅን ከየትም ተሻምቶ በህገወጥ መንገድ ለመጠቀም ያሉ አሰራሮች ናቸው፡፡” ብለዋል፡፡

ችግሮችን ለማስተካከልና ያለውንየነዳጅ እጥረት ለመከላከል አሠራር መዘርጋቱን ዶ/ር ኢብራሂም ተናግረዋል፣ የመንግስት ተሸከርካሪዎች ለከተማ ውስጥ እንቅስቃሴ ከቢሯቸው በሚፃፍ ደብዳቤ መሰረት በሳምንት አንድ ጊዜ እንዲቀዱ ማድረግ፣ ባለሦስት እግር ተሸከርካሪዎች በቀን 7 ሊትር እንዲቀዱ፣ ታክሲዎች በቀን 20 ሊትር እንዲቀዱ ሆኖ ተሸከርካሪዎቹ በማህበራቸው አማካኝነት በየተመደቡባቸው ማደያዎች ብቻ እንዲቀዱ የሚደረግ እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡

በአማራ ክልል ከ280 በላይ የነዳጅ ማደያ ጣቢያዎች የሚገኙ ሲሆን 253ቱ በስራ ላይ እንደሆኑም ታውቋል፡፡

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW