የነዳጅ እጥረት በትግራይ ክልል
ረቡዕ፣ ሰኔ 18 2017
አንዴ እየከፋ ሌላ ጊዜ በአንፃራዊነት እየተረጋጋ ረዥም ወራት ያስቆጠረው በትግራይ ያለው የነዳጅ አቅርቦት ችግር አሁን ላይ አሳሳቢ ደረጃ ደርሶ በእጥረቱ ምክንያት አምራች ድርጅቶች እየተዘጉ፣ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ጨምሮ ሌሎች እየተስተጓጐሉ፣ የእርዳታ አቅርቦት ተግባራት እክል እየገጠማቸው ይገኛል። የትግራይ ንግድና ኤክስፖርት ኤጀንሲ ከትናንት በስትያ ለንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ለነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን እንዲሁም ለኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የጻፈው ግልፅ ደብዳቤ በግንቦት ወር ወደ ትግራይ እንዲገባ ከሚጠበቀው 33 በመቶ ብቻ መግባቱን፣ በያዝነው ሰኔ ወር ደግሞ እጅጉን ቀንሶ በየጊዜው ከሚፈለገው 27 በመቶ ብቻ ነዳጅ ወደ ትግራይ መላኩን ያመለክታል።
ኤጀንሲው ወደ ሀገሪቱ በየዕለቱ የሚገባ የነዳጅ መጠን ባልቀነሰበት፥ያውም በጨመረበት ወደ ትግራይ የሚላከው ግን መቀነሱ አሳሳቢ መሆኑን አንስቷል። በትግራይ ንግድና ኤክስፖርት ኤጀንሲ የንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ክንደያ ለዶቼቬለ እንዳሉት ባለፉት 7 ቀናት ወደ መቐለ፣ ሽረ፣ ማይጨው የመሳሰሉ የክልሉ ከተሞች ነዳጅ ያልተላከ ሲሆን ወራት ያስቆጠረውን የነዳጅ እጥረት ተከትሎ በትግራይ የእርዳታ እና መድኃኒት ስርጭት ተስተጓጉሎ ይገኛል። የትራንስፖርት አገልግሎት እና የኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይም ችግሮች መፈጠሩን ገልፀዋል። በማሳያነትም ከ150 በላይ አስቸኳይ እህል እና መድኃኒት የጫኑ መኪኖች በነዳጅ እጦት ምክንያት ለተከታታይ 15 ቀናት ቆመው እንዳሉ አቶ ካሳሁን ገልፀዋል።
አቶ ካሳሁን ክንደያ «ድሮ በቀን ከነበረው ከ12 እስከ 16 መኪና ነዳጅ አሁን በከፍተኛ መጠን ቀንሶ በቀን አንድ ወይም ሁለት ሆንዋል። ይህ ፈፅሞ አያሠራም» ብለዋል።
በዚህ የነዳጅ እጦት ምክንያት ባለቤትነቱ የጣልያናውያን ባለሀብቶች የሆነ ኢታካ የተባለ የልብሶች አምራች ኩባንያ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ሥራውን ሙሉበሙሉ ያቋረጠ ሲሆን፥ ከ1,500 በላይ የሚሆኑ የድርጅቱ ሠራተኞችም ከስራ ውጭ መሆናቸውን ከድርጅቱ ሠራተኞች ሰምተናል። ኢታካ በትግራይ ብቸኛው ወደ ውጭ ሃገራት ምርቶችን የሚልክ ድርጅት ነው። በሌላ በኩል በመቐለ ሂደት ላይ የነበሩ የአስፋልት መንገድ ሥራ ፕሮጀክቶች የሥራ ተቋራጮቹ በገጠማቸው የነዳጅ እጥረት ምክንያት ግንባታቸው ተስተጓጉሎ ይገኛል። በትራንስፖርት ዋጋም እንዲሁ ከፍተኛ ጭማሪ ይስተዋላል።
የታክሲ ሹፌሩ ሮቤል «በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሁሉም ባለተሽከርካሪም ሆነ፣ ባለታክሲ ከጥቁር ገበያ ነው እየገዛ ያለው። ስለዚህ በትራንስፖርት ዋጋ ላይም ጭማሪ የግድ ነው። ቤንዚል ዛሬ 230 ብር በሊትር እየተሸጠ ነው። ለምሳሌ ከኤርፖርት ወደ ማሀል ከተማ ከ5 እስከ 600 የነበረው ዋጋ አሁን 800 ብር ሆኗል። በአንድ ጉዞ 200 ብር አካባቢ ጨምረናል። እኛም እየተቸገርን ነው፣ ተጠቃሚውም እየተቸገረ ነው» ብሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በድጎማ የሚያስገባው ነዳጅ ከሀገሪቱ ውጭ ወጥቶእንደሚሸጥ በተደጋጋሚ ይገልፃል። ዶቼቬሌ ያነጋገራቸው የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ደስታው መኳንንት «ለኮንትሮባንድ ተጋላጭ ወደተባሉ አካባቢዎች ነዳጅ በኮታ እያዳረስን ነው» ይላሉ።
የነዳጅ ኮንትሮባንድን በሚመለከት የተናገሩት የትግራይ ንግድና ኤክስፖርት ኤጀንሲ ከፍተኛ «ባለሥልጣኑ አቶ ካሳሁን ክንደያ ከዚህ ጋር በተያያዘ ለትግራይ የቀረበ ቅሬታ ወይ ክስ የለም፣» በማለት በነዳጅ ላይ ክልሉ ከፍተኛ ቁጥጥር እንደሚያደርግም ገልፀዋል።
በመቐለ የተለያዩ አካባቢዎች መታዘብ እንደሚቻለው፥ በማደያዎች ነዳጅ ባይኖርም በየመንገዱ ቤንዚል እና ናፍታ በሊትር ከ230 እስከ 250 ብር ይሸጣል። ይህን የሚከውኑት አካላት ነዳጁን ከአፋር ክልል በሕገወጥ መንገድ እንደሚያስመጡት ሰምተናል።
ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ
ሸዋዬ ለገሠ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር