1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የነዳጅ ዕጥረት እያስከተለው ያለው ጫና

ሥዩም ጌቱ
ማክሰኞ፣ መጋቢት 22 2018

«በከባድ መኪና እቃ ነው የምናጓጉዘው፤ አሁን ነዳጅ ጥበቃ በተሰለፍንበት የተመለከትኩት ሁለት አይሱዙ የጭነት መኪና ቲማትም እንደጫኑ እላያቸው ላይ ሲበሰብስ ተመልክቻለሁ»

ነዳጅ ለመቅዳት የተሰለፉ የእርሻ ተሽከርካሪዎች
ነዳጅ ለመቅዳት የተሰለፉ የእርሻ ተሽከርካሪዎችምስል፦ Shewangizaw Wegayehu/DW

«ማደያ ላይ ሁለት-ሶስት ቀናትን አድረን ነዳጅ አለቀ እንባላለን»

This browser does not support the audio element.

‎አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ አሽከርካሪና የተሽከርካሪ ባለንብረት ባለፉት ስድስት ቀናት ነዳጅን ፍለጋ ከከተማ ከተማ ከመሽከርከር ውጭ የተለመደውን የጭነት ስራቸውን በመስራት ምርቶችን ከቦታ ቦታ በማጓጓዝ ገቢ ማግኘት ቀላል አልሆነላቸውም፡፡ 
«በጣም አስቸጋሪ ነው፤ ናፍጣ ለማግኘት ማደያ ላይ ሁለት-ሶስት ቀናትን አድረን አለቀ ይባላል፡፡ ከዚያን ወደ ሌላ ማደያም ሄደን ተመሳሳይ ነገር ይገጥመናል፡፡ ከዱከም እስከ ሸገር ከዚያም ከሆለታ እስከ ሙገር ብንቀሳቀስም በቂ ነዳጅ ባለማግኘቴ ቆመያለው።» 

ያስከተለው ከባባድ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጫና


ይህ የነዳጅ እጥረቱ በጉልህ በሚታይ መልኩ ከፍተኛ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫናን እያስከተለ እንደሆነም ይነገራል፡፡ በጭነት ላይ እያለ ብዙ ምርት ተጠቃሚ ጋር ሳይደርስ እንደሚበላሽም አንድ አሽከርካሪ የታዘቡትን ገልጸውልናል፡፡ 
«በከባድ መኪና እቃ ነው የምናጓጉዘው፤ አሁን ነዳጅ ጥበቃ በተሰለፍንበት የተመለከትኩት ሁለት አይሱዙ የጭነት መኪና ቲማትም እንደጫኑ እላያቸው ላይ ሲበሰብስ ተመልክቻለሁ» በማለት የችግሩን አስከፊነት ገልጸዋል፡፡ 
የነዳጅ እጥረቱ ከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስ እያሳደረም ነው፡፡ ባሳለፍነው ቅዳሜ እለት በምዕራብ ኦሮሚያ ቄሌም ወለጋ ዞን የነዳጅ ችግሩ ባስከተለው የትራንስፖርት እጥረት ከደምቢዶሎ ከተማ ወደ ሙጊ ሲጓዝ በነበረው ገልባጭ መኪና ላይ ለመጓዝ ከተገደዱ በርካታ ዜጎች በሰዮ ወረዳ አባጃራ ቀበሌ ውስጥ በደረሰው የተሽከርካሪው የመገልበጥ አደጋዘጠኙ ወዲያው ህይወታቸው ሲያልፍ በርካቶች ላይ ከቀላል እስከ ከባድ ጉዳት ደርሷል፡፡ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የአከባቢው የአይን እማኝ፤ 
«ህይወታቸው ያለፈው ዘጠኝ ሰዎች ናቸው፡፡ ከቀላል እስከ ከባድ አደጋ ያስተናገዱም አሉ፡፡ እንደ አገሪቱ ያጋጠመው ከነዳጅ እጥረቱ በተጨማሪ እዚህ የመንገድ ችግርም አለ» 

የነዳጅ ማደያምስል፦ Million Haileselassie/DW

በህገወጥ የነዳጅ አዘዋዋሪዎች  እየተወሰደ ያለእርምጃ


‎የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ  እንዳስታወቀው ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ነዳጅን ከነአዘዋዋሪዎቹ በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።
በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ቱሉ ዲምቱ አከባቢ ከሚገኝ የነዳጅ ማደያ ታንከር ውስጥ 46 ሺህ ሊትር ቤንዚን በማሽን በመታገዝ ወደ ተሽከርካሪ በመቅዳት ወደ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ይዞ ሲንቀሳቀስ እጅ ከፍንጅ የተያዘ አሽከርካሪ፤ እንዲሁም በተሽከርካሪው ላይ በህገ-ወጥ መንገድ የነዳጅ ታንከር በማስገጠምና እንቁላል አከፋፋይ በመምሰል ነዳጅ ሲያከፋፍል ነበር የተባለን ተጠርጣሪ ከግብረ-አበሮች ጋር በቁጥጥር ስር እንደዋሉ አስታውቋል። ከእያንዳንዳቸው ተጠርጣሪዎቹ መኖሪያ ግቢም ከ12 በላይ በርሜሎች መገኘታቸውንም የፖለቲስ መረጃው ይተቁማል። 

ፖሊስ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የተያዘው ነዳጅበሕግ አግባብወደ ሌላ ማደያ እንዲገለበጥ በማድረግ ከሽያጩ የሚገኘው ገንዘብ ለመንግስት ገቢ እንዲሆን ተደርጎ በተያዙ ተጠርጣሪዎች ላይም ምርመራ እያደረገ መሆኑን አመልክቷል። 

‎በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባምንጭ ከተማ በተመሳሳይ ሁኔታ 2 ሺህ 400 ሊትር የሚጠጋ ነዳጅ ከግለሰብ ቤት ተከማችቶ በመገኘቱ ግለሰቡ በቁጥጥር ስር መዋሉን የከተማው ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል፡፡ መምሪያው በከተማው ሲቃላ ክፍለከተማ አንድ ግለሰብ ቤት ውስጥ ተከማችቶ የተገኘ 75 ጄሪካን ነዳጅ ማግኘቱንም ጠቁሟል፡፡ 
ትናንት ሰኞ መጋቢት 21 ቀን 2018 ዓ.ም. ደግሞ የአማራ ክልል ፖሊስ ከአጋር የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን 80 በርሜል ነዳጅ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ነው የፌዴራል ፖሊስ የገለጸው። ‎በምዕራብ ጎንደር ዞን በሁለት አይሱዙ ተሽከርካሪ ሲጓጓዝ የነበረ 80 በርሜል ነዳጅ ከተሽከርካሪዎች እና ተጠርጣሪዎች ጋር ቁጥጥር ሥር መዋሉንም ፖሊስ ገልጿል።
‎በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልም የፀጥታ አካላት ባካሄዱት የተቀናጀ ዘመቻ  የኮንትሮባንድ ዕቃዎች፣ ህገወጥ ነዳጅ እና የጦር መሣሪያ በቁጥጥር መዋላቸው ተነግሯል። በተደረገው ክትትል “በጥቁር ገበያ” ሊቸረቸር ነበር የተባለ 1 ሺህ 585 ሊትር ነዳጅ እና ሌሎች በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ ነበር የተባሉ ምርቶች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተጠቁሟል።‎
ህብረተሰቡ በ‎ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ተገዝቶ የሚገባው የነዳጅ ምርት ላይ ሰው ሰራሽ እጥረት በመፍጠር በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚንቀሳቀሱ ያላቸውን ግለሰቦችና ተቋማትን እንዲጠቁም ፖሊስ ትብብር ጠይቋልም፡፡

በአዲስ አበባ ነዳጅ ለመቅዳት ወረፋ የሚጠብቁ መኪኖችምስል፦ Seyoum Getu/DW

በነዳጅ እትረቱ የተከሰተ የሸቀጦች የዋጋ ንረት


በተከሰተው የነዳጅ እጥረት በርካታ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ማስከተሉን ያነጋገርናቸው ሸማቾች ይገልጸውልናል። «ቤት እየሰራሁ ነበር፤ ግን አሁን ባለበት አቁሜለሁ፡፡ ሶስት ሺህ ስንገዛ የነበረው ቀለም ወደ አምስት ሺህ ከፍ ብሏል፡፡ ለግንባታ የሚውል የኤሌክትሪክ ገመድ ደግሞ ከስድስት ሺህ ወደ 12 ሺህ ንሯል» 
‎በዚሁ ባሳለፍነው ሳምንት የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ገጻቸው እንደገለጹት በስድስት ክልሎች እና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች እየተደረገ ያለው ቅንጅታዊ ቁጥጥር  ስኬታማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 
በውስን ቀናት ተደረገ ባሉትም ጠንካራ ክትትል ከ250 ሺህ በላይ ሊትር ቤንዚን እና 200 ሺህ ሊትር የሚጠጋ ናፍጣ በቁጥጥር ስር መዋሉን አስታውቀዋል፡፡ እንደሚኒስትሩ ማብራሪያ በህገወጥ መንገድ በቁጥጥር ስር የዋለውን ነዳጅ በመሸጥ ከ48.6 ሚሊየን ብር በላይ ለመንግስት ገቢ ማድረግ ተችሏል፡፡ በወንጀሉ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች ደግሞ 613 መሆናቸውን  ጠቅሰዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW