የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው በኅብረተሰቡ ላይ ያሳደረው ተጽእኖ በኢትዮጵያ፦ ውይይት
እሑድ፣ ጥር 18 2017
በኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ይፋ ከሆነበት ጊዜ አንስቶ መንግሥት ድጎማ ያደርግባቸው የነበሩ አገልግሎቶች ላይ በሒደት ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ተከስቷል ። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አግልግሎት፣ የኢትዮ ቴሌኮም፣ የውኃ እና ፍሳሽ አገልግሎቶች የክፍያ ተመን ቀደም ሲል ጨምረዋል ።
መንግሥት ማክሰኞ ታኅሣሥ 29 ቀን፣ 2017 ዓ.ም ደግሞ የአዲስ አበባ የነዳጅ ምርቶች ግብይት ጉልኅ የመሸጫ ዋጋን ይፋ ካደረገበት ጊዜ አንስቶ ነዋሪዎች ወትሮም ያንገዳግዳቸው የነበረ የዕለት ተዕለት ኑሯቸውን ለመግፋት እጅግ መቸገራቸውን እየተናገሩ ነው ። በተለያዩ ቦታዎችም ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት ተከስቷል ።
በመንግሥት መዋቅር ስር ያሉ ኃላፊዎችን ጨምሮ የተለያዩ አካላት በመቀናጀት የነዳጅ አቅርቦቱን ይሸሽጋሉ ብሎም በጥቁር ገበያ በከፍተኛ ዋጋ ይቸበችባሉ የሚሉ ቅሬታዎች እያስተጋቡ ነው ። እጥረቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ ለአብነት፦ ከሰሞኑ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ተሽከርካሪዎች መቆማቸው ተገልጧል ።
ያም ብቻ አይደለም፥ የክልሉ ነዋሪዎች በባሕላዊ መንገድ በፈረስ በበቅሎ፣ በአህያ እና በጋሪ የመጓጓዣ አገልግሎት መጀመራቸውን መጥቀሳቸው እጅግ አስደምሟል ። «የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው በኅብረተሰቡ ላይ ያሳደረው ተጽእኖ በኢትዮጵያ» የዛሬው እንወያይ መሰናዶ ዐቢይ ትኩረት ነው ። በውይይቱ 4 እንግዶች ተሳታፊ ናቸው ።
1-ኤሚሬተስ ፕሮፌሰር ዳንኤል ተፈራ
2-ዶ/ር አብዱልመናን መሃመድ፤ የምጣኔ ሐብት ባለሙያ
3-አቶ ክቡር ገና፤ የፓን አፍሪካ የንግድ እና የኢንድስትሪ ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር
4- አቶ ዓማንይሁን ረዳ፦ የንግድ እና ኤኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ ናቸው ተወያዮች ።
ጉልኅ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ላይ በሚያወሳው በዚህ ውይይት መንግስት ተሳታፊ እንዲመድብ ለጠቅላይ ሚንሥትር ጽ/ቤት ይፋዊ የኢሜል ግብዣ ብንልክም ውይይቱን እስካደረግንበት ጊዜ ድረስ ምላሽ አላገኘንም ።
ሙሉውን ውይይት በድምፅ ማእቀፉ ማድመጥ ይቻላል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ