የነዳጅ ዘይት የዋጋ ንረት በጋምቤላ ክልል
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 13 2017
በጋምቤላ ክልል በሚገኙ ነዳጅ ማደያዎች በቂ የነዳጅ ዘይት ባለመገኘቱ በጥቁር ገበያ የሚሸጥ ነዳጅ ዘይት ዋጋ ከመደበኛው በእጥፍ መጨመሩን ነዋሪዎች አስታውቁ፡፡ የዋጋዉ ንረት በተጠቃሚው ላይ ጫና ማሳደሩን እና ነዳጅ በመደበኛነት ከማደያዎች የሚገኝበትን ስርዓት መፍትሄ እንደሚበጅለት ሀሳብ አቅርበዋል፡፡የአንድ ሊትር ቤንዚን መደበኛ ዋጋ 130 ብር ሲሆን በጥቁር ገበያ ግን በእጥፍ ዋጋ ለመግዛት መገደዳቸዉን ነዋሪዎቹ ገልፀዋል። ብዙ ጊዜ ከማዳያ ነዳጅ እንደማይገኝ የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎች ማደያዎች በአግባቡ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚመለከተው ተቋም ትኩረት እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ የክልሉ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ቢሮ በበኩሉ ነዳጅ በማደያ ለተፈቀደላቸው ግለሰቦች ለችርቻሮ እንደሚሸጥ ገልጾ በጥቁር ገበያ ይሸጣል በተባለው ጉዳይ በድርጊቱ ላይ የተሳተፉ አካላት ካሉ ክትትል እንደሚያደርግ እና እርምጃ እንደሚወስድ አመልክተዋል፡፡
በጥቁር ገበያ አንድ ሊትር ቤንዚን ከ250 እስከ 300 ብር ይሸጣል
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጋምቤላ ነዳጅ ከመደበኛ ማደያ ለማግኘት እየተቸገሩ እንደሚገኙ ከከተማው ያነጋርገናቻው ነዋሪዎች አመልክተዋል፡፡ ከማደያ ይልቅም በድቀብ ከሚሸጠው ጥቁር ገበያ ነዳጅ ማግኘት እንደሚቀል የገለጹት ነዋሪዎቹ የነዳጅ ዋጋ በጥቁር ገበያው በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በዛሬው ዕሌት በከተማው ውስጥ በሚገኘው ኖክ የተባለ ማደያ ቤንዚንም ሆነ ናፍጣ በማደያው አለመገኘቱን ለማረጋገጥ ችለናል፡፡ በተለያዩ ቦታዎች ደግሞ በሊትር ከግለሰቦች በህገወጥ መንገድ አንድ ሊትር በ250 ብር እና ከዛም በላይ በሚሆን ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ ተገልጸዋል፡፡
አንድ አንድ ጊዜ ነዳጅ በማደያ በሚገኝበት ወቅት ረጃጅም ሰልፎችን ማስተናገድ እንደሚጠበቅባቸው የተናገሩት ሌላው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የከተማው ነዋሪም ከነዳጅ ማደያዎች በህገ ወጥ መልኩ ከሚሸጡ ግለሰቦች ጋር በመመሳጠር ነዳጅ የሚያሸሹ ባለሀብቶች እንዳሉ አመልክተዋል፡፡ በጥቁር ገበያ የሚሸጠው ነዳጅ ከዋጋ አንጻር ከመደበኛው በእጥፋ የጨመር በመሆኑ በተጠቃዎች ላይ ጫና እያሳደረ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ በድብቅ ከሚሸጡ ግለሰቦች ቤንዚን ከ250 እስከ 300 ብር እንደሚሸጥ የተናገሩት ነዋሪው ይህ ድርጊት አሁን አሁን እየተለመደ መምጣቱን አክለዋል፡፡
‹‹በህግ ወጥ ንግድ ላይ የተሳተፉ አካላትን ለመቆጣጠር ክትትል ይደረጋል››
የጋምቤላ ክልል ንግድ እና ኢንዱስትሪቢሮ በበኩሉ ህገ ወጥ ንግድ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ለመቆጣጠር እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡ የክልሉ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ኃላፊ የሆኑት አቶ ኦሌሮ አፊዮ ነዳጅን በተመለከተ በማደያዎች በከሉል ፈቃድ ላላቸው ግለሰለቦች በበርሚል እንደሚሰጣቸው ገልጸው በአካባቢው ፈቃድ የተሰጣቸው ግሰቦች በኩል፣ ማደያን ጨምሮ ነዳጅ እንደሚሸጥ አብራርተዋል፡፡ በከተማው በህግ ወጥ መንገድ ዋጋ በመጨምር ስለሚሸጡ ግለሰቦች ክትትል በማድረግ እርምጃ እንደሚወሰድ አቶ ኦለሮ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በጋምቤላ ከስድስት በላይ የነዳጅ ማደያዎች የሚገኙ ሲሆን በተለያዩ ወቅቶች የሚመጣው ነዳጅ ከተጠቃሚው ብዛት አንጻር በቂ አለመሆኑን የማደያ ባለ ንብረቶች ይገልጻሉ፡፡ ነገር ግን ተጠቃዎች እንደሚሉት ደግሞ ከመደበኛ ዋጋ በላይ በእጥፋ ለመሸጥ ሲባል በህግ ወጥ መንገድ ነዳጅ እንደሚሸጥ እና በኑሮ ላይ ጫና እያሳደረ ይገኛል፡፡
ነጋሳ ደሳለኝ
ነጋሽ መሐመድ
ልደት አበበ