የኒዠር ነዋሪዎች ምሬትና የስደተኞች ስቃይ
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 28 2015
ኒዠርዋ አጋዴዝ ከተማ ስደተኞች ለብዙ ዓመታት በቴነሬ በረሃ በኩል ወደ ሰሜን አፍሪቃ ብሎም ወደ አውሮጳ የሚያሻገሩባት ማዕከል ነበረች ። በደኅንነት እጦት ምክንያት አጋዴዝ ለቱሪዝም የማትመች ከተማ ከሆነች በኋላ 200 ሺህ ከሚደርሱት የአጋዴዝ ነዋሪዎች አብዛኛዎቹ ቤቶቻቸውን ለስደተኞች በማከራየትና፣እነርሱንም በማጓጓዝ ብዙ ገንዘብ ያገኙ ነበር። ይሁንና በጎርጎሮሳዊው 2015 ስደተኞችን ማጓጓዝን የሚከለክል ሕግ ከወጣ በኋላ ሁኔታው ተለውጧል። በዚህ ስራ ተሰማርቶ የሚገኝ እስከ እስራት የሚደርስ ቅጣት ይጠብቀዋል። ብዙዎች ይህ እገዳ እንዲጣል ያደረገብን የአውሮጳ ኅብረት ነው ሲሉ ያማርራሉ። ይህ ክልከላ ግን ስደተኞችን በሕገ ወጥ መንገድ ማሻገርን አላስቆመም።
አሁን ከቀድሞው የሚለየው ስደተኞች ወደ ሊቢያ ለመሄድ የሚጠየቁት ዋጋ እጅግ መወደዱ ነው። ይህ ብቻ አይደለም ጉዞውም አደገኛ ሆኗል።
ኢሱፉ በሀያዎቹ አጋማሽ የሚገኝ ከአይቮሪ ኮስት የመጣ ስደተኛ ለውሳኔ ተቸግሯል። ብዙ መስዋዕትነት ከፍሎ አጋዴዝ ቢደርስም ከከተማዋ ግን መውጣት አልቻለም።
« ችግሬ የሚጠየቀው ገንዘብ የለኝም። አሁን ጉዞየን ለመቀጠል እየጠበቅኩ ነው። ወደ ዚህ ስመጣ ተዘርፌያለሁ። የነበረኝን ሁሉ ተዘርፌያለሁ። »
በሚገኝበት በአጋዴዝ ለጉዞው የሚያስፈልገውን በቂ ገንዘብ ሰርቶ ማግኘት አይችልም።ከከተማዋወጣብሎ በሚገኝ ስፍራ በአንድ መጠጥና ምግብ ቤት ቤት ውስጥ መጠጥ ይሰራል።
ስፍራው ብዙ ስደተኞች የሚመጡበት ቦታ ነው።ስለቀጣዩ ጉዞ ስደተኞቹን መረጃ ይጠይቃል። የአይሶፉ ስልክ ፋታ የለውም ወዲያው ወዲያው ይደወልለታል። የሚያገኘው ገንዘብ ከምግብ አይተርፍም። ችግሩ ይህ ብቻ አይደለም ይላል።
«አጋዴዝ እንደደረስክ ትታገታለህ።በአንድ በኩል ጉዞህን ለመቀጠል አትፈልግም።ምክንያቱም መንገድ ብዙ መጥፎ ነገሮች ያጋጥማሉ። ወደ ሀገርህ መመለስ ደግሞ ውድቀት ነው የሚሆነው። ሕጋዊው መጓጓዣ መከልከሉም ሌላው ተጽእኖ የሚያደርግብን ነገር ነው። በምንኖርበት ጎስቋላ መንደር ጎረምሶችና ፖሊስ ይዝቱብናል። ጎረምሶቹ ሞገደኛ ናቸው። ብዙ ጊዜይዘርፉናል። ይዘልፉናል። «እዚህ አትፈለጉም ወደመጣችሁበት ተመለሱ ይሉናል።
አማዱ ኦማሩ ከዚህ ቀደም የስደተኞችን ጉዞ የሚያስተባብሩ ሰዎች የተሰባሰቡበት ማኅበር ዋና ጸሀፊ ነበር።
«ስራው ስራ አጥነትን ቀንሶ ነበር። ከአምስት እስከ ስድስት የሚደርሱ መኪናዎች ነበሩኝ ።ገቢዬም ወደ 5 ሺህ ዩሮ ይጠጋ ነበር። »
አማዱ አማሩ አሁን በአጋዴዝ አካባቢያዊ ምክር ቤት የፍልሰት ጉዳዮች አማካሪ ነው። እርሱ እንደሚለው ከዚህ ቀደም በከተማይቱ በትራንስፖርትና በሌሎች ለስደተኞች አገልግሎት በሚሰጡ ስራዎች ተሰማርተው የነበሩት ሌሎች ሰዎች እስካሁን አማራጭ ስራ አላገኙም። ምንም እንኳን በአጋዴዝ እንቅስቃሴዎች ቢገደቡም በከተማይቱ በኩል የሚደረገው ስደት ግን አልቆመም። በየሳምንቱ 150 መኪናዎች ከአጋዴዝ ወደ ሊቢያ ይሄዳሉ። በከተማይቱ ስደት ብዙ ገንዘብ ማግኛ ምንጭ ነው። ከቀድሞው አሁን የተለወጠ ነገር ቢኖር ስደተኞች ወደ ሊቢያ ለመሄድ ሲሄድ የሚጠየቁት ዋጋ መጨመሩ፣ በወታደሮች የማይጠበቀው መንገድ ደኅንነቱ አስተማማኝ አለመሆኑ በጉዞ ላይ ወሮ በሎች ማጋጠማቸው እንዲሁም ሾፌሮች ራሳቸውን ለእስር አጋልጠው ስደተኞችም ሕይወታቸውን ይበልጥ ለሞት አጋልጠው መጓዛቸው ነው አዲሱ ነገር።አማሩ እንደሚለው በረሀው በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መቃብር ሆኗል። በሕይወት የሚገኙት ነዋሪዎችዋም አማዱ እንደሚለው አልደላቸውም።
«የቀድሞው ፕሬዝዳንታችን በየዓመቱ 900 የስራ እድሎችን ለመፍጠር ቃል ገብቶ ነበር። ይሁንና ሕጉንካወጣ በኋላ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች ስራ አጥ ሆነዋል። ይህ ብዙዎችን ተስፋ አስቆርጧል። ሕጉ ኤኮኖሚው እንዲያዘግም ማድረጉ ብቻሳይሆን ሌሎች አደገኛ መዘዞችንም አስከትሏል።»
ከአካባቢው ወጣቶች ምክር ቤት ዋዴል አቡበከር ሕጉ በተለይ ወጣቱን ጎድቷል ብለዋል።
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር