1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የናሚቢያዉ ዘር ማጥፋት

ቅዳሜ፣ መጋቢት 17 2014

በቅኝ ገዢዎች ላይ ያመፁ የሔሬሮ ማሕበረሰብ አባላት በ1904 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) በጀርመን ጦር የተደፈለቁበት ዝነኛዉ የዎተርበግ ተራራን የተንተራሰችዉ ኦካካራራ ትንሽ ናት።አንድ የተግባረ-ዕድ ማሰልጠኛ ማዕከል፣ ሁለት የትራፊክ መብራቶች፣ 4 ሺሕ ነዋሪዎች።

DW 77 Sendung
ምስል Johan von Mirbach/DW

የናሚቢያ ዘር ማጥፋት፣ የበዳይ ተበዳዮች ወራሾች ክርክር

This browser does not support the audio element.

የጀርመን ቅኝ ገዢ ጦር እንደ ጎርጎርያኑ አቆጣጠር ከ1904 ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ዓመታት በያኔዋ የጀርመን ደቡብ ምዕራብ አፍሪቃ (በዛሬዋ ናሚቢያ) ሕዝብ ላይ የፈፀመዉ ግፍ ዛሬም ድረስ የተበዳይ-በዳይ  ወራሾችን እያወዘጋበ ነዉ።በአብዛኛዉ በሔሬሮና ናማ ሕዝብ ላይ የተፈፀመዉ ግፍ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንደነበር ጀርመን አምናለች።ለተበዳዮች ወራሾችም ካሳ ለመክፈል ተስማምታለች።ይሁንና ቃል-ስምምነቱ ገቢር አልሆነም።ስምምነቱ ራሱ  የተበዳይ ወራሾችን ብሶት፣ቅሬታና ጥርጣሬን ሊያስወገድ አልቻለም።የዛሬ ትኩረት በአፍሪቃ ዝግጅታችን በ20ኛዉ ክፍለ-ዘመን መጀመሪያ ላይ ስለተፈፀመዉ ግፍ በናሚቢያዉንና በነጭ ሠፋሪዎች መካከል የሚደረገዉን ክርክር ባጭሩ ይቃኛል።ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

የዶቸ ቬለ የአፍሪቃ ክፍል የበላይ ኃላፊ ክላዉስ ሽቴከር  እንደፃፋዉ ለአስተዋዩ መንገደኛ ከርዕሰ-ከተማ ዊንድሆክ ወደ ሰሜን እየራቀ ሲጓዝ ለጀርመኖችና በጀርመኖች ላይ ያለዉ ጥላቻ፣ ቅሬታና ጥርጣሬ እየቀረበ፣እየናረ-እየደደረ ይመጣል።ከዊንድ ሆክ በስተሰሜን 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘዉ ኦካካራራ ከተማ ደግሞ የሔሬሮ ማሕበረሰብ መናኸሪያ፣የቅሬታ፣ ጥላቻ፣ ጥርጣሬዉ መንፀባረቂያ ናት።

በቅኝ ገዢዎች ላይ ያመፁ የሔሬሮ ማሕበረሰብ አባላት በ1904 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) በጀርመን ጦር የተደፈለቁበት ዝነኛዉ የዎተርበግ ተራራን የተንተራሰችዉ ኦካካራራ ትንሽ ናት።አንድ የተግባረ-ዕድ ማሰልጠኛ ማዕከል፣ ሁለት የትራፊክ መብራቶች፣ 4 ሺሕ ነዋሪዎች።በቃ።በያ ሰሞን ያስተናገደችዉ የእርሻ ዐዉደ-ርዕይ በቅርብ ዘመን ታሪኳ በርካታ ሰዉ የተሳተፈበት ትልቅ ድግሷ ነበር።12 ሺሕ ሰዉ።

ምስል Claus Stäcker/DW

የጀርመኑ ዓለም አቀፍ ማሰራጪያ ጣቢያ ዶቸ ቬለ ለአፍሪቃ ወጣቶች የሚያሰራጨዉ 77 ከመቶ ለተባለዉ ዝግጅቱ የአዉራ-ጎዳና ክርክርንም ሰሞኑን አስተናግዳለች።ቅስት መፈክሮቹ፣ትላልቅ ድምፅ ማጉያዎቹ፣ ለካሜራ የተዘጋጀዉ ልዩ ልዩ ምስል ለወትሮዉ ያሸለበች ለምትመስለዉ የወረዳ ከተማ ልዩ ድምቀት ሰጥቷት ነበር።

The Namibian የተሰኘዉ የዕዉቁ ጋዜጣ ባልደረቦች መቅረፀ-ድምፅ፣ ካሜራ፣ ብዕር፣ ደብተራቸዉን ታጥቀዉ በክርክሩ ስፍራ ነበሩ።HiTRadio ከዊንድ ሆክ ተጉዞ እዚያች ከተማ ሰፍሯል።

ለክርክሩ የተጋበዙት ሰዎች ጉምጉምታ፣ የጋዜጠኛ፣አስተናጋጅ፣ ረዳቶቻቸዉ ሽር-ጉድ ካናታቸዉ ላይ የሚሽከረከሩት ካሜራ የተጠመዱባቸዉ  ሰዉ አልባ በራሪዎች ሽክርክርታ የነዋሪዎችን በተለይም የወጣቶችና የሕፃናትን ትኩረት ስቦ ፈዘዝ፣ቀዘዝ፣ ተከዝ ያለችዉን ከተማ አንቅቶ በጥፍሯ አቁሟት ነበር።ግን ያዉ ለጥቂት ዕለታት።

የናሚቢያ አንጋፋ ጋዜጣ-በጀርመንኛ ቋንቋ የሚታተመዉ Allgemeine Zeitung ዘጋቢዎቹን አልካም።ይሁንና ደቼ ቬለ ነዋሪዎችን ያከራከረበትን የዘር ማጥፋት ወንጀልን ርዕሱ አድርጎ የፀሓፊዎችን አስተያየት አስተናግዷል።ዶቸ ቬለ የመረጠዉ ርዕስና ስፍራ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ነዉ።

የጀርመን ማሰራጪያ ጣቢያ፣ ጀርመኖች የፈፀሙትን ግፍ እያነሳ፣ በጀርመን ላይ ቅሬታና ጥርጣሬ ያላቸዉን የሔሬሮና የናማ ማሕበረሰብ አባላትን፣ ከግፈኞቹ ከተጠቀሙ ወገኖች ጋር ለማነጋገር ሔሬሮዎች ከተማ ድረስ መዉረድ በርግጥ ከባድ ነበር።ግን የታሪክ መፀሐፍት «የ20ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን የመጀመሪዉ ዘር ማጥፋት» ስላሉት ግፍ፣ግፍ የተዋለባቸዉና የዋሉ ዉላጆችን ለማነጋገር ዶቸ ቬለ ከባዱን ፈተና ተጋፈጠ።ጠንካራ ቃላት ከጋዜጠኞች ጭምር ይዥጎደጎዱ ገቡ።«ጀርመን በይፋ ይቅርታ ለመጠየቅ ይሕን ያሕል ዘመን ያቅማማችዉ ለምንድ ነዉ?» ጠየቀች- ጋዜጠኛ ቸርማይኔ ንጋትጂሄዩ

«ዛሬ ሁኔታዉ እንዴት ነዉ? የዘር ማጥፋት ወንጀል ነዉ።በዛሬዉ እሳቤ አይደለም።ካሳ ክፈሉ።አዉቃለሁ ይፈራሉ።አንዴ ካሳ ከከፈሉ ከሌሎች ሐገራትም ብዙ ሰዎች ጀርመኖች ላደረሱት በደል ሁሉ ካሳ እንዲከፈላቸዉ ጀርመንን ተጠያቂ ያደርጋሉ ብለዉ ይሰጋሉ።የሔሬሮና የናማ ሰዎች ጥያቄ እንደቀጠለ ነዉ።እርግጥ ነዉ (በአከፋፈሉ) ላይ ልዩነት አለ።ነጥቡ ላይ እስክንደርስ ድረስ ልዩነቱ ይቀጥላል።»

ፀሐፊዉ እንደታዘበዉ እንዲሕ ዓይነቱ አስተያየት በክርክሩ ላይ የተሳተፉት ያብዛኞቹ ሰዎች እምነት ነዉ።ተሳታፊዎቹ ገንዘብ ብቻዉን ሁሉንም ነገር ሊያቃልል እንደማይችል ያምናሉም።

የጀርመን መንግሥት ከ6 ዓመታት ድርድር በኋላ በ30 ዓመታት ዉስጥ 1.1 ቢሊዮን ዩሮ  ካሳ ለመክፈል አምና ከናሚቢያ መንግስት ጋር ተስማምቷል።ጀርመን «ካሳ» የሚለዉን ቃል በይፋ መጠቀም አልፈለገችም።ይልቅዬ የጀርመን መንግስት ገንዘቡን ከመደበኛዉ ርዳታ በተጨማሪ ለናሚቢያ «ዳግም ግንባታና ለዕርቅ የሚዉል።» ብሎ  መጠራቱን ነዉ የፈቀደዉ።

የጀርመን ፕሬዝደንትና የዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ናሚቢያ ሔደዉ በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቁ ተወስኗልም።እስካሁን ግን ክፍያዉም፣ ይቅርታዉም ገቢር  አልሆነም።

አጠቃላይ ስምምነቱም በናሚቢያዉያን ዘንድ ሙሉ ተቀባይነት አላገኘም።የሐገሪቱ ምክር ቤት በስምምነቱ ላይ የጀመረዉ ዉይይት በእንደራሴዎች መካከል ጠብ አጭሮ  ተቋርጧል።

ምስል DW

በተለይ የሔሬሮና የናማ ማሕበረሰብ ተወካዮች በድርድሩ ላይ አልተካፈልንም-አንድ፣ ለካሳ ቃል የተገባዉ ገንዘብ ትንሽ ነዉ-ሁለት፣ ካሳዉ ትንሽም ቢሆን ለተበዳይ ወራሾች በጥሬዉ መከፈል አለበት-ሶስት የሚሉ ምክንያቶችን በመደርደር ስምምነቱን ይቃወሙታል።

በድርድሩ ይካፈሉ  ከነበሩ ሁለት ዕዉቅ የሔሬሮ ማሕበረሰብ ተወካዮች በኮቪድ 19ኝ በሽታ ሞታቸዉ ደግሞ ጉዳዩን ይበልጥ አወሳስቦታል።ጀርመንም በመራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ይመራ የነበረዉ መንግሥት በአዲስ በመቀየሩ የናሚቢያ ጉዳይ በ«ይደር» ተትቷል።

ናሚቢያዉያን በጣሙን የሔሬሮና የናማ ማሕበረሰብ አባላት በጀርመን ላይ የቋጠሩት ቂም፣ ቅሬታና ጥላቻ እልባት ባያገኝም  የዶቸ ቬለ ባልደረቦች ከሔሬሮዎቹ መናኸሪያ ኦካካራራ ከደረሱበት ጊዜ ጀምሮ የተደረገላቸዉ አቀባበል፣ ክላዉስ ሽቴከር እንደፃፈዉ  የ«ወዳጅ»ና «ደማቅ» የሚባል  ነበር።የ18 ዓመቷ የሕግ ተማሪ ቫአሩካ ካአሮንዳ እንዳለችዉ ቤተሰቦችዋ በሙሉ የነጮች ተቀጣሪ ድሆች ናቸዉ።

«ለኛ (ባካባቢዉ) የተረፈ ምንም መሬት የለም።የምንተዳደረዉ በነጮቹ አሰሪዎች ስር ነዉ።በየዕለቱ ሰዎች ሲሰቃዩ ማየት የተለመደ ነዉ።ብዙ ጊዜ የማስበዉና የሚገርመኝ በገዛ መሬታችን ላይ የምንኖር ከሆነ ለምንድነዉ የራሳችን ማሳ የሌለን? ለምንድነዉ ይሕን ያክል የምንቸገረዉ? እያልኩ ነዉ»

ጠየቀች።ባካባቢዉ ተወልዶ ያደገዉ  ነጭ ገበሬ ባካባቢዉ ያለዉን በሺሕ ሔክታር የሚቆጠር መሬት የሚቆጣጠሩት ነጮች ሶስተኛ ትዉልድ ነዉ።ከስሞቹ አንዱ ከዚያ ተራራ የተወረሰ ነዉ።ሐሪ ሽናይደር-ዎተርበርግ (ጀርመኖቹ ቫተርበርግ ይሉት ይሆናል)።ለወጣትዋ ጥያቄ መልስ ያለዉ አስተያየቱ ግን ብዙዎችን ያሳዘነ፣ ጥቂቱን ያበሳጨ፣ ያስቆጣም ነበር።

                              

ምስል Sakeus Iikela/DW

«እዚሕ የመጡት ሰዎች አንዳቸዉም መሬት አልዘረፉም።እዚሕ የመጡት ሰዎች መሬቱን የያዙትን በወቅቱ በነበረዉ መንግስት ሕግ መሰረት ገዝተዉ ነዉ።ከነፃነት በኋላም ቢሆን መሬቱን አሁን ባለዉ ደንብ መሰረት ነዉ የገዙት።»

አስተያየቱ  ያሳዘናቸዉ አጉረመረሙ።የተበሳጩት አንገታቸዉን፣ የተናደዱት ዱላቸዉን ይወዘዉዛሉ።በናሚቢያ ብሔራዊ የወጣቶች ማሕበር የሔሬሮ ወጣቶች ተወካይ ኢሌኒ ሔንጉቫ ግን ጭንቅላቱን ነቅንቆ ዝም አላለም።ጠንካራ አፀፋ ነበረዉ።

                                

«ነገሩን ከስሩ እናንሳ ካልን፣ ነጮች ናሚቢያ ዉስጥ መሬት ያገኙት እንዴት ነዉ?ወታደር ስለነበርክ ለዉለታሕ ሥልተ-ምርት አገኘሕ፣ እሱም መሬት ነዉ።መሬቱን ስለተቆጣጠርክ ላንተ ትዉልዶች አወረስክ።ሕጉም ባለርስቶችን ለመጠበቀ የተዘጋጀ ነበር።»

ክርክሩን በጥሞና ይከታተሉ ከነበሩት አንዷ የThe Namibian ዘጋቢ በንቃት ማስታወሻ ስትወስድ ነበር።በማግስቱ የታተመዉ ጋዜጣዋ «የጀርመን ሰፋሪዎች መሬት ጨርሶ አልወሰዱም» የሚል ርዕስ አዝሎ ወጣ።

ዶቸ ቬለ ያዘጋጀዉ መድረክ በባለጉዳዮች መካከል የተሟሟቀ ክርክር አስነስቷል።ሐሪ ሽናይደር ዎተርበርግ ግን ጋዜጠኛዋ እንደዚያ ዓይነት ርዕስ መስጠትዋን ተችቷል።ይሁንና የሰጠዉ አስተያየት ሰዎችን አስቀይሞ ከሆነ ይቅርታ ጠይቋል።ከወጣቶች ማሕበር ተወካዩ ከኢሌኒ ሔንጉቫ ጋር በክርክሩ ማግስት ተጨባብጠዉ፣ የስልክ ቁጥር ተለዋዉጠዉ፣ ተሳስቀዉ ተለያይተዋል።

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ

 

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW