የዘር ማጥፋት ካሣ የምትፈልገው ናሚቢያ አዲስ ስምምነት እንዲረግ እየጠየቀች ነው።
ዓርብ፣ መስከረም 13 2015
የናሚቢያ ተቃዋሚዎች ከጀርመን ጋር በሚያወዛግበው የዘር ማጥፋት ጉዳይ ከስምምነት ለመድረስ እንደገና ድርድር እንዲደረግ እየጠየቁ ነው። እነዚህ ወገኖች ጀርመን ሀገሪቱን በቅኝ ግዛት በያዘችበት ወቅት ሄሬሮ እና ናማ ህዝቦች ላይ ተፈጽሟል ለሚሉት የዘር መጥፋት ተገቢና ተመጣጣኝ ካሣ እንዲከፈል አጥብቀው ያሳስባሉ። በጉዳዩ ላይ በጀርመን መንግሥት እና በናሚቢያ በኩል የተደረገው ስምምነት ለውዝግቡ እልባት ያበጅለታል ተብሎ ቢታሰብም አሁንም የሚጠብቁ እንዳልሆነ ለናሚቢያ የሚሟገቱን ወገኖች ይገልጻሉ። ከሰሞኑም በናሚቢያ ምክር ቤት የጦፈ ክርክር አስነስቷል። በተለይም ከአዲሱ የጀርመን መንግሥት የተሻለ ነገር ጠብቀው እንደነበር ሆኖም አሁን የገመቱት እንዳልሆነ ቅሬታቸውን ይፋ አድርገዋል። የጀርመኑ አረንጓዴ ፓርቲ ለረጅም ግዜ ወዳጆቻችን ይመስሉን ነበር ያሉት ናንዲሶራ ማዚንጎቨር የሄሮ የዘር ማጥፋት ተቋም ሊቀመንበር ቅሬታቸውን ከገለጹት አንዷ ናቸው።
«ለጉዳያችን ትኩረት ይሰጣል፤ ወዳጃችንም ነው ብለን ከገመትነው አረንጓዴ ፓርቲ ጋር ለረዥም ጊዜ አብረን ተጉዘናል። አሁን በመንግሥት ሥልጣን ላይ ናቸው። ግን ምን ያደረጉት ነገር የለም። እንደውም እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን ማንሳት በጀርመን ፖለቲካ ውስጥ ተሰሚነትና ሥልጣን ለማግኘት መጠቀሚያ ነው የሚለውን እንድናምን እየገፉን ነው። በመሠረቱ እንደው ወሬ ብቻ ነው ።
ከጀርመን መንግሥት ጋር የተገባውን ስምምነት በሚመለከት ቀዳሚው ሰነዱ እነሱ የሚሉትን ዋና ጉዳይ እንደማያነሳ የሚናገሩት ናንዲሶራ ማዚንጎቨር ከዚህ ሌላ ደግሞ በካሣ ለመስጠት ቃል የተገባው የገንዘብ መጠን በውቅያኖስ ላይ የሚደረግ ጠብታ ያህል ነው ይላሉ። ሁለተኛ ዙር ድርድር ያስፈልጋል የሚሉት ለዚህ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።
« አንዳንድ ሰዎች ለዚህ ጥያቄ እልባት በመስጠት ታሪክ ትተው ለማለፍ ስለሚፈልጉ ብቻ ቁንጽል እና የሐሰት ውሎችን አንፈርምም። ወይም ደግሞ አንዳንድ የጀርመን መንግሥታት ባለስልጣናት በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥሩ መስለው መታየት ይፈልጋሉ ይኾናል፤ በፍጹም ለሚቀጥሉት 100 አመታት በያዝነው አቋም በፅናት መቆየት እንችላለን። አሁን አረንጓዴ ፓርቲ እንዲሁም የደቡብ-ምዕራብ አፍሪካ ህዝብ ድርጅት አብዛኛውን የመንግሥት አስተዳደር ይዘዋል። ነገር ግን ለዘለዓለም መንግስት ሆነው አይቀጥሉም። ይህን መንግሥት እናስወግደዋለን ። በቀጣዩ 100 አመታት ውስጥ የሚመጡ መንግሥታትንም እናልፋለን፤ ምንያቱም እኛ ትክክለኛውን ታሪክ ይዘናል፤ ከእውነት ጎን ነን፤ መነሻችን ደግሞ ፍትህ ነው። »ሲሉ
በተቃራኒው በናሚቢያ የሚገኙ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ኤሊኒ አቨንጋ አረንጓዴ ፓርቲ ተስፋ አለን ባይ ናቸው
«እንደ ሀላፊነታችን እና ማህበረሰቡን እንደመወከላችን ዲያስፖራውን ጨምሮ በአንድ አገር ስለሚኖሩ ይህንን ግንዛቤ ውስጥ መክተት አለብን »
የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ምንም አይነት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።
እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር ከ1884 እስከ 1915 ድረስ የደቡብ ምዕራብ አፍሪካ ተብላ ትጠራ በነበረችው ያሁንዋ ናሚቢያ በጀርመን አገር ቅኝ ግዛት ስር ቆይታለች ።
ማህሌት ፋሲል
ሽዋየ ለገሰ