እውን ያልሆነው የኔልሰን ማንዴላ ራዕይ
ረቡዕ፣ ሐምሌ 11 2010ደቡብ አፍሪቃ በወቅቱ የምትገኝበት ሁኔታ የቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዚደንት እና የዘር አድልዎ አመራር ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ እውን ሊያደርጉት ካሰቡት እጅግ የተለየ እና ቅር ሊያሰኛቸው የሚችል ነው ብለው እንደሚገምቱ የፕሪቶርያ ዓለም አቀፍ የፀጥታ ጥናት ተቋም ዋና ስራ አስኪያጅ ጃኪ ሲልየ ገልጸዋል።
« ደቡብ አፍሪቃ በ2018 ዓም የምትገኝበት ሁኔታ ኔልሰን ማንዴላን አብዝቶ ያሳስባቸው ነበር። »
ብዙ የፖለቲካ ተንታኖችም የሲልየን አስተያየት ይጋራሉ። በዛሬው ዕለት የሚታሰበውን የኔልሰን ማንዴላ 100ኛ ዓመታቸውን ምክንያት በማድረግ በሳቸው ስም የሚጠራው ተቋም እና ገዢው የአፍሪቃውያን ብሔረተኞች ኮንግረስ፣ ኤኤንሲ በመላይቱ ሀገር ለክብራቸው ልዩ መታሰቢያ ዝግጅቶችን እያካሄዱ ነው። ይሁንና፣ ትልቅ ክፍፍል የገጠመው ፓርቲያቸው ቀድሞ የነበረውን ትርጓሜ አጥቷል። የአሁኗ ደቡብ አፍሪቃ ለውጥ በመሻት ላይ ስትሆን፣ ሀገሪቱ የመጀመሪያው ጥቁር ደቡብ አፍሪቃዊ ፕሬዚደንት ስልጣን ከያዙ ዛሬ ከ24 ዓመታትም በኋላ የተሻለ እድል ፍለጋ ስትጥር ትታያለች። በዚህም የተነሳ ኔልሰን ማንዴላ በደቡብ አፍሪቃ የተለያዩ ዘሮች በጋራ የሚኖሩበት ማህበረሰብ ለመፈጠር የወጠኑት እቅዳቸውም፣ በተለይ ስማቸው ከሙስና ቅሌት ጋር በተያያዘ አዘውትሮ የሚነሳው የቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ ተጠያቂ እንደሆኑ ነው ጃኪ ሲልየ የሚናገሩት።
«ጄኮብ ዙማ በፕሬዚደንትነት በቆዩባቸው ዓመታት በሀደሪቱ ላይ ብዙ ጉዳት አድርሰዋል። ሀገሪቱ በተለይ በብሔራዊው አንድነት ላይ ትልቅ ጉዳት ደርሶባታል። ዛሬ ደቡብ አፍሪቃ ተከፋፍላለች፣እርግጥ፣ የወደፊት ሁኔታዎች አዎንታዊ ናቸው። ግን፣ ደቡብ አፍሪቃ ጄኮብ ዙማ በሙስና፣ ዘመድ አዝማድ በመጥቀሙ አሰራራቸው እና በዘገምተኛው የኤኮኖሚ እድገት ካደረሱባት ጉዳት እስክታገግም ድረስ ብዙ ዓመታት ያስፈልጓታል። »
ካለፈው የካቲት ወር፣ 2018 ዓም ወዲህ ሀገሪቱን በመምራት ላይ ያሉት የማንዴላ ታማኝ የሚባሉት ሲሪል ራማፎዛ የማንዴላን ከዘረኝነት የጸዳ ማህበረሰብ የመፍጠሩን ራዕይ እውን ማድረግ ሊሳካላቸው እንደሚችል ጃኪ ሲልየ ይገምታሉ። ማንዴላ ለተተኪነት ያሰቧቸው ራማፎዛ የሀገሪቱ ለዘብተኛ እና ዘመናይ ሕገ መንግሥት በተረቀቀበት ስራ ላይ ተሳታፊ ነበሩ። ሲልየ በዘረኝነት በተከፋፈለው ማህበረሰብ መካከል እርቅ በመፍጠሩ ተግባር ላይ አትኩረዋል ያሏቸው ማንዴላ በሀገሪቱ የተጓደለውን ማህበራዊ እኩልነት፣ አሁንም፣ በጥቂት n።ጮች እጅ የሚገኘውን መሬት ክፍፍልን፣ መሬታቸው የተወሰደባቸው ነጮች ገበሬዎችን ካሳ መስጠትን ለመሳሰሉ ጥያቄዎች መፍትሄ ፍለጋውን ወደጎን መተዋቸው ዛሬም በሀገሪቱ ትልቅ ችግር እንደደቀኑ ይገኛሉ፣ ለዚህ ግን ማንዴላ ብጸናው ተጠያቂ አይደሉም ባይ ናቸው። ችግሩ በዘጠኝ ዓመቱ የዙማ አመራር ዘመን ተባብሷል። ይሁንና፣ ማንዴላ በስልጣን በቆዩባቸው አምስት ዓመታት የታዩትን የአዲሷን ደቡብ አፍሪቃ ችግሮች በሚገባ አልታገሉም በሚል ብዙ ወጣት ደቡብ አፍሪቃውያን ያሰሙትን አስተያየት በማጣጣል፣ በነጮች እና በጥቁሮች መካከል የርስበርስ ጦርነት እንዳይነሳ ማከላከል የተሰኘውን ዋነኛ ዓላማቸውን ገሀድ ማድረጋቸውን አድንቀዋል። ይህንኑ የጃኪ ሲልየ አስተያየት የሚጋሩት በፕሪቶርያ የሚገኘው የዊትዎተርስራንድ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚደንት አዳም ሀቢብ ማንዴላ የሰሯቸውን ስህተቶች ለመቀበል እንደማይቸገሩ አስታውቀዋል።
« የአሁኗ ደቡብ አፍሪቃ ሁኔታ ማንዴላን ቢኖሩ ኖሮ እንደሚያሳስባቸው አምናለሁ፣ ይሁን እንጂ፣ በአስተዳደራቸው ዘመን አንዳንድ ስህተቶች መሰራታቸውን ፣ ለምሳሌ፣ ወግ አጥባቂውን የኤኮኖሚ መርሀግብር መከተላቸውን የማህበራዊ እኩልነት መጓደልን እንዳባባሳው አምነዋል። ይህ ስህተት በህብረተሰቡ ዘንድ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ክፍፍል አስከትሏል። ይህ ግን በሌላው የዓለም አካባቢም የሚታይ ክስተት ነው። »
አርያም ተክሌ /ማርቲና ሺቭኮብስኪ
አዜብ ታደሰ