የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ«የሕግ መርሆዎችን የሚጥስ ነው »መባሉ
ረቡዕ፣ ሰኔ 12 2016ሰሞኑን ለኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ፣ ከውጪ በተላከ ገንዘብ ሃብት አፍርቶ የተላከበትን ደረስኝ ያላቀረበ ሰው ወይም ሊታወቅ ከሚችል ገቢው በላይ ሃብት አፍርቶ ምንጩ ሕጋዊ መሆኑን ማረጋገጥ ያልቻለ ሰው ንብረት፣ በመንግስት እንዲወርስ የሚፈቅድ ድንጋጌ መያዙ ተመልክቷል። ይኸው ረቂቅ አዋጅ የሚጸድቅ ከሆነ፣10 ዓመት ወደኃላ ተመልሶ ተፈጻሚ ይሆናል ነው የተባለው።
አዋጁ የፈጠረው ስጋት
ዶይቸ ቨለ ያነጋግራቸዉ የአትላንታ ነዋሪው ፕሮፌሰር ጸሐይ አለማየሁ፣ረቂቅ አዋጁ ስጋት ፈጥሮባቸዋል። "በሃገር ውስጥ ከፍተኛ የቤት እጥረት እንዳለ እየታወቀ፣ በከፊልም ቢሆን ይሄን የቤት እጥረት መልስ ለመስጠት የሚችሉ ወገኖች፣ዜጎችም ሆኑ በዲያስፖራ ያሉ ሰዎች፣ የሚያስቡትን ከመፈፀም ወደ ኋላ የሚጎትታቸው ይሆናል።ወደሃገር ውስጥ የውጭ ኢንቨስትመንት እንዳይገባ የሚያስደርግ፣ የሚያስደነግጥ ይሆናል።እና መቼም ሲውል ሲያደር ምን እንደሚመጣ ባናውቀውም፣በአሁኑ ሁኔታ ይህ ነው በጎ ዐሳቡ የሚባል ነገር የለውም በውስጡ።"
ፒቲ ኦፊሰር አበበ መለሰ በበኩላቸው፣የፕሮፌሰር ፀሐይን ስጋት የሚጋሩ ሲሆን፣ "ረቂቅ አዋጁ ጥናት የተደረገበት አይመስለኝም" ብለዋል። "ምክንያቱም በውጭ ያለው ዲያስፖራ፣ ወደ አራት ቢሊዮን ዶላር ወደ አገር ውስጥ እየላከ፣ መንግስት ከዚህ በርካታ ጥቅሞችን ያገኛል፤ ይህንን ህዝብ ማስኮረፍ ማለት ነው።"
ረቂቅ አዋጁ ከሚጸድቅበት ጊዜ አንስቶ፣ ወደ ኋላ 10 ዓመት ተመልሶ ተፈጻሚ እንደሚሆን ረቂቅ አዋጁ ላይ መጠቀሱ፣ በኢትዮጵያ ባለው የሰነድ አያያዝ ሁኔታ፣ አስቸጋሪ መሆኑንም ጠቆመዋል። ለምክር ቤት የቀረቡት ሁለት ረቂቅ አዋጆች ጭብጥ
"ስንቱ ሰው ነው ተጠንቀቆ ደረሰኝ የሚይዘው ለእዚህ፣ ስንት ሰው ሰነድ በዚህ ያለው አሁን?"
ስለ ረቂቅ አዋጁ የሕግ ባለሞያ አስተያየት
ስለጉዳዩ ዶይቸ ቨለ ያነጋገራቸው በዩናይትድ ስቴትስ ቨርጂኒያ ግዛት የሕግ ባለሙያው ዶክተር ፍጹም አቻምየለህ፣ለምክር ቤቱ የቀረበው ይኸው ረቂቅ ህግ፣ የሀገሪቱን ሕገ መንግስትንና ዓለም አቀፍ የሕግ ድንጋጌዎችን የሚጥስ እንደሆነ ያስረዳሉ።
"ሕገ መንግስቱ ንብረት የማፍራትን መብት ከዛም አልፎ ደግሞ፣ አንድ ሕግ ወደ ኋላ ሄዶ እንዳይተረጎም ያዛል። ከእዛም ውጭ ደግሞ እያንዳንዱ ኢትዮጵያ የምታወጣው ሕግ በዓለም አቀፍ መስፈርት ያቀፈ ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን የዓለም አቀፍ ህጎችን ግምት ውስጥ ያስገባ እነሱን ያማከለ ነው የሚሆነው።"የኢትዮጵያ የተወካዮች ምክር ቤት ውሎ እና የቀረቡ አዳዲስ ረቂቅ ሕጎች
እንደ የህግ ባለሙያው ማብራሪያ፣ረቂቅ ሕጉ ሌሎችም መዘዞች ሊያስከትል ይችላል። "ይህ ሕግ የውጭ ዕርዳታን በተመለከተ የወጣውን፣የ1961 ዱን የውጭ ዕርዳታ ደንብ ላይ ተጨማሪ ማሻሻያ የተደረገበት አንቀጽ 620 e1 ማሻሻያ እርሱ ራሱ፣ ንብረትን የሚወርሱ ሃገሮች የአሜሪካን የውጭ ዕርዳታ እንዳያገኙ የሚል አንቀጽ አለው። እናም ይህም ራሱ አሜሪካውያን የሆኑ ሰዎች፣ ኢትዮጵያ ዕርዳታ እንዳታገኝ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ፣በUSAID በኩል ዕርዳታ እንዲቆም ሁሉ ሊያደርጉ ይችላሉ እና ብዙ ብዙ መዘዞች አሉት ብዬ ነው የማስበው።"ብለዋል።
ታሪኩ ኃይሉ
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ