1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኖርድ ስትሪም የጋዝ ማስተላለፊያ መስመር ውዝግብ

ዓርብ፣ መስከረም 20 2015

ከሩሲያ ወደ ጀርመን ጋዝ የሚያስተላልፉት ኖርድ ስትሪም 1 እና 2 የተባሉት ቧንቧዎች መሸንቆር ከሞስኮ ጋር ውዝግብ ውስጥ ለገባው ምዕራቡ ዓለም ሌላ መነታረኪያ ምክንያት ሆኗል። በባልቲክ ባሕር ሥር የተዘረጉት ሀገር አቋራጭ የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧዎች ሰኞ ዕለት ነበር ሦስት ቦታ መሸንቆራቸው የተሰማው።

Infografik - Gaslecks an Nord Stream 1 und 2 - EN

ኖርድ ስትሪም 1 እና 2

This browser does not support the audio element.

ከሩሲያ ወደ ጀርመን ጋዝ የሚያስተላልፉት ኖርድ ስትሪም 1 እና 2 የተባሉት ቧንቧዎች መሸንቆር ከሞስኮ ጋር ውዝግብ ውስጥ ለገባው ምዕራቡ ዓለም ሌላ መነታረኪያ ምክንያት ሆኗል። በባልቲክ ባሕር ሥር የተዘረጉት ሀገር አቋራጭ የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧዎች ሰኞ ዕለት ነበር ሦስት ቦታ መሸንቆራቸው የተሰማው። በዚህም ምክንያት በሺህዎች ኪዩቢክ ሜትር የተገመተ ጋዝ ከባሕር ጠለል በታች 70 ሜትር መፍሰሱ ተገልጿል። ሁሉም ወገኖች አሁን መንስኤውን ለማጣራት ምርመራ እንዲካሄድ እየጠየቁ ነው። ሸዋዬ ለገሠ ዝርዝሩን አጠናቅራለች።

ኖርድ ስትሪም 1, እና ኖርድ ስትሪም 2 የተሰኙት የጋዝ ማስተላለፊያ ባንቧዎች ምንም እንኳን አሁን ያንን ተግባር በስጠት ላይ ባይሆኑም በውስጣቸው ጋዝ ተሸክመዋል። ሐሙስ ዕለት ደግሞ የስዊድን የባሕር ወደብ ጠባቂዎች ተጨማሪ አራተኛ ሽንቁር አግኝተዋል። ሦስት ቦታ የተሸነቆረው የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ በዴንማርክ አቅራቢያ የሚገኝ ሲሆን የተከሰተው በአሻጥር ነው የሚለው ጥርጣሬ ከጀርመንና ከሌሎች የምዕራብ አውሮጳ ሃገራት እየተነገረ ነው። ስዊድን ቀደም ብላ ድርጊቱ ሆን ተብሎ የተፈጸመ ሻጥር ነው ስትል ዴንማርክን ዋቢ አድርጋ ገልጻለች። የስዊድን ጠቅላይ ሚኒስትር ማግደሊና አንደርሰን፤

«የስዊድን የስለላ መረጃ አለን፤ ሆኖም ከዴንማርክም መረጃ ደርሶናል። በዚህ ላይ በመመርኮዝም ምናልባት ሆን ተብሎ የተፈጸመ ድርጊት ነው ወደሚለው ድምዳሜ ደርሰናል። ምናልባትም ሻጥር ይሆናል።» ነው የሚሉት።

ዴንማር አቅራቢያ በባልቲክ ባሕር ላይ የታየው መታወክምስል Danish Defence Command/AP/picture alliance

የአብዛኞቹ ጥርጣሬ ሩሲያ ሆን ብላ በፍንዳታ ጉዳት አድርሳበታለች የሚለው ቢሆንም እስካሁን ለአደጋው መንስኤ የሆነው ነገር ተረጋናግጦ አልተገለጸም ወይም በተጨባጭ መረጃ አልቀረበበትም። ሐሙስ ዕለት የተሰማው ችግሩ ከመታወቁ አስቀድሞ ባልቲክ ባሕር በፍንዳታ ተናውጧል የሚለው የርዕደ መሬት ተመራማሪዎች ፍንጭ ግን የሁለቱ የጋዝ ቧንቧዎች ጉዳት በሻጥር ተፈጽሟል የሚለውን ጥርጣሬ አጉልቶታል። ሩሲያ በበኩሏ የጋዝ ቧንቧዎቹ የአሸባሪ ጥቃት ሰለባ ሳይሆኑ አይቀሩም ባይ ናት። የክሪምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ጉዳዩን አስመልክተው ሐሙስ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መንስኤውን ለመመርመር ሩሲያ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ለመተባበር የሚያስችላት መንገድ አለመኖሩን ገልጸው በሞስኮ በኩል ያለውን ጥርጣሬ ይፋ አድርገዋል።

«ይኽ ክስተት ነው፤ ምንነቱን ለመግለጽ ገና ነው። ሆንም የጥፋቱ ይዘት የሆነ ድርጊት መፈጸሙን ያመላክታል። እንዲህ ያለ የአሸባሪ ድርጊት  ደግሞ ያለ አንድ መንግሥት ትብብር ይፈጸማል ብሎ ለመገመት በጣም ያዳግታል።»

ፖስኮቭ እጅግ አደገኛ ያሉትን ይኽን ድርጊት ለማጣራትም ባስቸኳይ ምርመራ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ጀርመን ግዛት የሚገኘው የኖርድ ስትሪም 1 የጋዝ ቧንቧምስል Stefan Sauer/dpa/picture alliance

ዩናይትድ ስቴትስ በፍንዳታ ጉዳት የደረሰባቸው የኖርድ ስትሪም 1 እና 2 የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧዎች እና የሚፈሰው ጋዝ ጉዳይ ያሳስበኛል ብላለች። የኋይትሃውስ ቃል አቀባይ ካሪን ጂን ፒየር ሀገራቸው ከአውሮጳ አጋሮቿ ጋር በቅርበት ጉዳዩን እየመረመረች ነው ብለዋል። «የጋዝ ቧንቧዎቹን ሻጥር በተመለከተ ከአውሮጳ አጋሮቻችን ጋር በቅርበት እየተወያየን ነው። ይኽን ለመመርመር አውሮጳ የሚያደርገውን ጥረት እየደገፍን ነው። እንደገለጹኩት ጉዳዩ ምርመራ ላይ ነው። ሁላችሁ እንደምታውቁት እነዚህ ቧንቧዎች ወደአውሮጳ ጋዝ የሚያስተላልፉ ነበሩ፤ ማለቴ ይቅርታ አሁን እያስተላለፉ አይደለም። ኖርድ ስትሪም 2 እንደውም በሥራ ላይ አልነበረም። ኖርድ ስትሪም አንድም ቢሆን ሩሲያ የኃይል ምንጭን ለጦር መሳሪያነት በመጠቀሟ ምክንያት ከሳምንታት በፊት ተዘግቷል።»

ምስል Stefan Sauer/dpa/picture alliance

የአውሮጳ ሕብረት ለአባል ሃገራት ጋዝ የሚያስተላልፉት ቧምቧዎችን ከተጨማሪ ጉዳት ለመከላከል ጥበቃውን አጠናክራለሁ ብሏል። የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ኔቶም 30 በሚሆኑት የአባል ሃገራቱ መሠረተ ልማት ላይ ጉዳት ባደረሰው አካል ላይ የአጸፋ ጥቃት እንደሚወስድ ዝቷል። ኖርድ ስትሪም 1 እና ሁለት የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧዎች ለፊንላንድ ከምትቀርበው ከሰሜናዊ ምዕራብ ሩሲያዋ ከተማ ፋይቦርግ በመነሳት በሰሜናዊ ምሥራቅ የጀርመን ግዛት ሜከለንቡርግ ፎርፐመርን ድረስ የተዘረጉ ናቸው። የእያንዳንዱም ርዝመት 1,200 ኪሎ ሜትር እንደሚደርስ መረጃዎች ያመለክታሉ።  

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW