1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሊባባ የግብይት ማዕከል ለኢትዮጵያ ምን ጥቅሞች አሉት?

ረቡዕ፣ ኅዳር 17 2012

የቻይናው አሊባባ ግሩፕ የዓለም አቀፍ የኤሌክትሮኒክስ የግብይት ማዕከልን በኢትዮጵያ ለመመስረት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር ህዳር 15 ተፈራርሟል። “ንግድና ዲጂታል ኢኮኖሚን የሚያበረታታ ነው” የተባለለት ማዕከሉ የላቀ ቴክኖሎጂ፣ መሰረተልማት፣ አገልግሎት አሰጣጥና የቁጥጥር ማዕቀፍ እንደሚኖረው ተገልጿል።

Äthiopien Unterzeichnung eWTP Hub
ምስል DW/Y. Gebrezihaber

የአሊባባ የግብይት ማዕከል ለኢትዮጵያ ምን ጥቅሞች አሉት?

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያ እና የቻይናው አሊባባ ግሩፕ በኢትዮጵያ ዲጂታል የግብይት ማዕከል ለመገንባት ባለፈው ሰኞ ህዳር 15 ቀን 2012 የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመዋል። ስምምነቱ ሲፈረም ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ፣ የአሊባባ ግሩፕ ተባባሪ መሥራች ጃክ ማ እና የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኤሪክ ጂንግ ተገኝተዋል።

"ዓለም አቀፍ ኤሌክትሮኒክ ትሬድ ፕላትፎርም" የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ማዕከል የድንበር ተሻጋሪ ንግድን ለማጠናከር፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍ፣ የኢትዮጵያ አነስተኛ እና መካከለኛ ተቋማት የቻይናንና ሌሎች ገበያዎችን እንዲደርሱ ለማገዝ ያለመ መሆኑን አሊባባ ግሩፕ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ከዚህ በተጨማሪም ማዕከሉ "የክኅሎት ሥልጠና ለማቅረብ ያስችላል" ብሏል ኩባንያው።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ የዲጂታል የግብይት እና ስልጠና ማዕከሉ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት «ኢትዮጵያን በመጪው አስር ዓመት ውስጥ በአፍሪካ የኢኮኖሚ ቀዳሚነትን ከያዙ አምስት ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ ዓይነተኛ እርምጃ ነው» ብለውታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማዕከሉ በኢትዮጵያ መቋቋም ለአነስተኛና መካከለኛ የንግድ ሥራዎች የንግድ ምህዳርን ለማስፋት እንደሚያግዝም አክለው ገልጸዋል።

ምስል DW/Y. Gebrezihaber

"ዓለም አቀፍ የኤሌክትሮኒክ ትሬድ ፕላትፎርም" አሊባባ ግሩፕ ቴክኖሎጂ እና ፖሊሲን በማጣመር ለጥቃቅናን እና አነስተኛ ተቋማት፣ ሴቶች እና ወጣቶች የተሻለ ዕድል የሚሰጥ አካታች ዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓት ለመፍጠር የሚያቀነቅነው ዓለም አቀፍ ጥረት ነው። ኢትዮጵያ ከሩዋንዳ ቀጥሎ በአፍሪካ ይህንን ተቋም በማቋቋም ሁለተኛ አገር ትሆናለች። በመንግሥት እና በግሉ ዘርፍ ውይይት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ የሚነገርለት "ዓለም አቀፍ የኤሌክትሮኒክ ትሬድ ፕላትፎርም" ባለፉት ሁለት አመታት በቻይና፣ ማሌዥያ እና ቤልጅየም ሥራ ጀምሯል። 

የዲጂታል ግብይት እና ስልጠና ማዕከሉን ወደ ኢትዮጵያ ያመጣው የአሊባባ ግሩፕ ተባባሪ መስራች ጃክ ማ እየተገባደደ ባለው የጎርጎሮሳዊው 2019 ዓመት በቻይና በሐብት መጠን አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። የ55 ዓመቱ ቱጃር 39·7 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ጥሪት እንዳላቸው ፎርብስ መጽሔት አስታውቋል። ይህም በዓለም የቱጃሮች ዝርዝር 21ኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጡ እንዳደረጋቸው የፎርብስ መረጃ ይጠቁማል። ጃክ ማ ባለፈው መስከረም ከአሊባባ ዋና ሊቀመንበርነታቸው መልቀቃቸው ይታወሳል።

የዓለም አቀፍ የኤሌክትሮኒክስ የግብይት ማዕከል በኢትዮጵያ ስለሚያስገኘው ጥቅም እና ሊያጋጥመው ስለሚችለው ተግዳሮት ባለሙያዎች የሰጡትን ትንታኔ ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ዮሃንስ ገብረእግዚያብሔር

ተስፋለም ወልደየስ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW