የአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች ለአስከፊ ድርቅ መጋለጣቸውን ከንቲባው አመለከቱ
ሰኞ፣ ኅዳር 7 2019
ከተደጋጋሚ ጦርነት እስከ አስከፊ ድርቅ፡ የራያ አላማጣና አካባቢዉ ማህበረሰብ ፈተናዎች
ከተደጋጋሚ ግጭቶችና ጦርነቶች ገና ያላገገመዉ የራያ አላማጣ ከተማና አካባቢው፣ የክረምት ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ አለመገኘትና የጦርነት አውዳሚነት ተደምረው ማህበረሰቡን ለከፋ የድርቅና የረሃብ አደጋ መዳረጋቸውን ነዋሪዎችና የስራ ሃላፊዎች ገለጹ። በአካባቢው የተከሰተው አስከፊ የምግብ እጥረት የዕለት ተዕለት ኑሮን ከማክበዱም በላይ ወሮበላነትና ዝርፊያ እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል ተብሏል።
የምርት እጥረትና የኢኮኖሚ ውድቀት
ከ2013 ዓመተ ምህረት በኋላ ተደጋጋሚ ጦርነቶችን ሲያስተናግድ የቆየው የራያ አለማጣ ከተማና አካባቢው፣ ባለፈው ክረምት ወቅት የክረምቱን ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ አለመጣል በእርሻ ጊዜ ወቅት በአካባቢው ላይ የነበረው ጦርነት የምርት ሂደቱ ላይ ባደረሰው ተጽዕኖ አካባቢው ለድርቅ መዳረጉን ነዋሪዎች ተናገሩ።
በአካባቢው ይመረት የነበረ ማሽላና ጤፍ በዝናብ እጥረት ምክንያት አለመመረቱ ለከፋ ችግር እንደዳረጋቸው ስማቸውን ያጠቀሱ አርሶ አደሮች ይናገራሉ።
«የራያ አለማጣ ራያ አላማጣ ይዘህ አብዛኛው ቀለቡ ምንድነው? ማሽላ ነው። ማሽላ ደግሞ በዝናብ እጥረት ምክንያት የለም። ጤፍ ደግሞ ዝናብ አጠረው ጤፍም አላመረተም። ማሽላና ጤፍ አላመረተም ማለት፣ የሚበላው የለም ማለት ነው።
በጥቅሉ ግን ምርቱ የለም ራያ ላይ ማለት ነው። በእኔ ልንገርህ እና እኔ የዛሬ ምናምን ዓመት ሽሮ፣ በርበሬ፣ ምናምን ነገር አላስብም ነበር። ያንን ተሻግሬአለሁ ወደ ሌላ ነገር የማስበዉ አሁን ግን ስለሽሮ፣ ስለበርበሬም በርበሬው እንዴት አድርጌ ነው የምገዛው ብሎ ነው የምጨነቀው አሁን ያለበት ሁኔታ ማለት ነው። ኢኮኖሚካሊ ደቋል ማህበረሰቡ ጦርነቱ በጣም ይሄ የስምንት ዓመት ቀውሱ በጣም አድቋል ማህበረሰቡን»
በራያ አለማጣ ከተማና አካባቢው ላይ አሁን ያለው ኢኮኖሚያዊ ሁኔታየስራ እድል መፍጠር የሚችል ባለመሆኑ ምግብ ሰርተው መብላት ያልቻሉ ሰዎችን ተመልክተናል የሚሉት ሌላኛው አስተያየት ሰጭም ችግሩ የከፋ መሆኑን ይገልጻሉ።
«በጣም አስከፊ ነው ያለው። ስራ የለ የቀን ሰራተኛ የሚባል የለም። ሳይበሉ የሚያድሩ ወጣቶች አሉ። እመጫቶችም እንደዛ እንደውም በአይኔ አየኋት አስፋልት ላይ የሆነች ሴት እርቦት መንገድ ላይ ልጇን አዝላ ወድቃለች። በአይኔ ያየሁትን ነው የማወራህ።»
የፖለቲካዊ ቀውሶች እና የጸጥታ ስጋት
በራያ አለማጣ ከተማና አካባቢው ላይ ካለው ድርቅ ይልቅ ውስብስብ የሆነው የአካባቢው ፖለቲካዊ ሁኔታ ጎድቶናል የሚሉትየአለማጣ ከተማ ነዋሪም አሁንም ማህበረሰቡ በአካባቢው ለሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ድርጎ እየተጠየቀ ነው ይላሉ።
«አሁን ማህበረሰቡ ያገኛትንም ወደ አፉ እንዳያደርግ ቀለብ ለሰራዊ አዉጣ አለ። ይሄ ማህበረሰብ ምንድን ነው የሚያስፈልገው? ፎይታ ያስፈልገዋል ያለውችው ተበዳድሮ ተካፍሎ በልቶ ሰላም ወጥቶ ሰላም የሚገባበት መንገድ መፍጠር አለበት። ስለዚህ ድርቁ ሳይሆን እኛን አሸንፎን ያለው ከድርቁ በላይ ፖለቲካው ድርቅ ሆኖብናል።»
ከአንድም ሶስት አራት ጊዜ አካባቢው ተደጋጋሚ ጦርነቶችን አስተናግዷል የሚሉት በትግራይ ክልል ጊዜያዊ ባላደራ አስተዳደር የአላማጣ ከተማ ከንቲባ አቶ ዝናቡ ደስታ ድርቅና ጦርነት ማህበረሰቡ ላይ የከፋ ተጽዕኖ መፈጠሩን ይናገራሉ ።
«በትግራይ አብዛኛዎቹ ቦታዎች በደቡብ ትግራይ አካባቢ ደግሞ እኛ ያለንበት አካባቢ በተለይ ደግሞ በድርቅ የተጠቃ አካባቢ ነው ያለው። ማህበረሰቡ ደግሞ በብዛት ያው እርሻና ከእርሻ ውጤቶች ጋር ተያይዞ የሚጠቀም ስለሆነ ትልቅ የሆነ የድርቅ ሁኔታና የረሃብ ሁኔታ አለ። ሁለተኛውጦርነቱ የወለደው ሁኔታም አለ። ሰው ገዳዮ አይታወቅም ሞቶ ይገኛል፣ አፋኙ ይታወቅም ይታፈናል፣ ይዘረፋል፣ ይቀጠቀጣል ሁሉም ነገር ነው። ይሄ በመሆኑ ያው ኢኮኖሚውን ሊሰራ ቀርቶ የመኖሩ ትልቅ ጥያቄ ስለነበር በዚህም ምክንያት ኢኮኖሚው ደህና አድርጎ እንዲደቅ አስተዋጽኦ አድርጓል»
የኃላፊዎች አስተያየትና የአስቸኳይ ድጋፍ ጥሪ
በራያ አለማጣና አካባቢው የተፈጠረው ድርቅ ትኩረት ሳያገኝ ማህበረሰቡም ለረሃብ ተጋልጠዋል ያሉት አቶ ዝናቡ ደስታ በዚህም ምክንያት በአካባቢው ወሮበላነት እየተስፋፋ ነው ብለዋል።
«አስቸኳይ የሆነ የምግብና የሌሎች ድጋፍ ማድረግ ነበረበት። በሚያሳዝን መንገድ ግን እስከአሁን ምንም የተደረገ ድጋፍ የለም። ሕዝቡ በጣም አስቸጋሪ በሆነ ደረጀ ላይ ነው ያሉት። ልጆች ወደ ትምህርት የሚሄዱት በባዶ ሆዳቸው ነው። ህብረተሰብም ይችን ሰላም ስላገኘሰላሟን በማጣጣም ነው እንጂ ያለው የረሃብ ጉዳይ በጣም አስቸጋሪ ነው።
ከዚህ የተነሳም የሌብነት፣ የዝርፊያ፣ የመቀማት እንደዚህ አይነት ነገሮች እንዲበረከቱ ምክንያት ሆኗል ማለት ነው። እና ይሄን የፌዴራል መንግስትም ይሁን የክልሉ መንግስት ይሄን በአጽንኦት ተመልክቶ ቶሎ ብሎ አስቸኳይ ድጋፍ መደረግ መቻል አለበት የሚል ሁኔታ አለኝ ማለት ነው።»
ኢሳያስ ገላው
ታምራት ዲንሳ
እሸቴ በቀለ