1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአል ማሊኪ ስንብት ኢራቅና የአውሮፓ ህብረት

ዓርብ፣ ነሐሴ 9 2006

የኢራቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ኑሪ አል ማሊኪ ስልጣናቸውን ለሽአቱ ለሃይደር አል አባዲ በማስረከብ ትናንት በይፋ ተሰናበቱ። ላለፉት 8 ዓመታት ኢራቅን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩት አልማሊኪ ከሚያዚያው ምርጫ በኋላ ስልጣን እንዲለቁ ከሱኒዎች፣ ከኩርዶች እንዲሁም ከሺአዎች ከኢራንና ከዩናይትድ ስቴትስ በኩል ከፍተኛ ግፊት ሲደረግባቸው ቆይቷል።

Nouri al-Maliki und Haider al-Abadi PK 14.08.2014
ምስል picture alliance/AP Photo

ሆኖም ማሊኪ በሚያዚያው የምክር ቤታዊ ምርጫው ውጤት መሠረት አዲስ መንግሥት የመመሥረት መብት አለኝ በማለት ሥልጣኑን የሙጥኝ ብለው ነበር። ይሁንና ትናንት በሰጡት መግለጫ ሥልጣናቸውን ለሃይደር አል አባዲ ማስተላለፋቸውን አስታውቀዋል።

«የተከበራችሁ የኢራቅ ህዝቦች ልነግራችሁ የምችለው ምን ዓይነት ሥራ አልፈልግም። ሆኖም ትልቁ ሥራዬ እናንተ በኔ ላይ ያላችሁ መተማመን ነው። እናም ዛሬ ከፊታችሁ ቆሜ የፖለቲካውን ሂደት ለማመቻቸትና አዲስ መንግሥትም እንዲመሰረት ለሚስተር ሃይደር አል አባዲ እንቅፋት ላለመሆን በተለይ ደግሞ ለሃገራችን ሉዓላዊ ጥቅም ስል ራሴን ከእጩነት አግልያለሁ። ኢራቅንና ህዝቧን ከጥቃት ለመከላከል ለተጨቆኑ ህዝቦች በመቆም አሸባሪነትን የኢራቅን መከፋፈል በመቃወም እንዲሁም ለኢራቅን አንድነት ሉዓላዊነትና ነፃነት ተዋጊ ወታደር ሆኜ እቆያለሁ።»

ምስል Reuters

አል ማሊኪ ከሥልጣን መውረዳቸውበዩናይትድ ስቴትስና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወዲያውኑ ተወድሷል። የዩናይትድ ስቴትስ ብሄራዊ የፀጥታ አማካሪ ሱዛን ራይስ የማሊኪ መሰናበት ሃገሪቱን አንድ የሚያደርግ ትልቅ እርምጃ ብለውታል። የተመድ ዋና ፀሃፊ ባን ኪሙን በበኩላቸው አል ማሊኪ ራሳቸውን ማግለላቸው ወሳኝ የሆነው የአዲስ መንግሥት ምስረታ እንዲፋጠንና በህገ መንግሥቱ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ መሰረት እንዲከናወን የሚያደርግ ይሆናል ሲል አስታውቀዋል። ሁለአቀፍ ሰፊ መሠረት ያለው መንግሥት እንዲመሰረትም ጥሪ አቅርበዋል።

ምስል Reuters

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአውሮፓ ሕብረት አባል ሃገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ዛሬ ብራሰልስ ቤልጂግ ውስጥ ባካሄዱት አስቸኳይ ስብሰባ ፣ ለኢራቅ ኩርድ ራስ ገዝ አስተዳደር የጦር መሣሪያ ለማቅረብ ተስማሙ። ሰብአዊ እርዳታ ለመስጠትም ቃል ገቡ፤ ሆኖም የህብረቱ አባል ሃገራት በሙሉ የጦር መሣሪያ እንደማይሰጡ የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ተናግረዋል። ሽታይንማየር እንዳሉት አንዳንድ አባል ሃገራት ህጋቸው በሚያስቀምጠው ገደብና በአቅም ውሱንነት ምክንያት ለኩርዶች የጦር መሣሪያ አይሰጡም። የምሥራቅ አውሮፓ የህብረቱ አባል ሃገራት ጥይትና የመሳሰሉትን ሳይሰጡ እንደማይቀሩ አመልክተዋል። ፈረንሳይ ኩርዶችን እንደምታስታጥቅ ያሳወቀች ሲሆን ፣ ብሪታኒያ ደግሞ የምሥራቅ አውሮፓ ሃገራት የሚሰጧቸውን ጥይቶችና ወታደራዊ ቁሳቁሶች እንደምትልክ በበኩሏም ተጨማሪ የጦር መሣሪያ የመስጠትን ጉዳይ እንደምታስብበት ተናግራለች። ጀርመን ኔደርላንድስና ሌሎች አባላት ደግሞ ኩርዶች እንዲያስታጥቋቸው ያቀረቡዋቸውን ጥያቄዎች እንደሚያጤኑ አስታውቀዋል።

ጀርመን ዛሬ ወደ ሰሜናዊ ኢራቅ ሰብዓዊ እርዳታ መላከች ጀመረች። 5 የጀርመን አየር ኃይል አውሮፕላኖች ዛሬ ማለዳ ለሰላማዊ ሰዎች እርዳታ የሚውል 36 ቶን ክብደት ያለው ሰብዓዊ እርዳታ ይዘው ወደ ሰሜን ኢራቅ በርዋል። መድሐኒቶች ምግብና ብርድ ልብስ የጫኑት እነዚሁ አውሮፕላኖች ወደ ኢራቅ ኩርድ ራስ- ገዝ መስተዳድር ዋና ከተማ አርቢል ማቅናታቸው ተገልጿል። ሌሎች እርዳታዎችን ወደ ኢራቅ መላኩ እንደሚቀጥልም የጀርመን መከላከያ ሚኒስትር ዑርዙላ ፎን ዴር ላየን ተናግረዋል።

«እርግጥ ነው ይህ የመጀመሪያው ነው። አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ተጨማሪ እርዳታዎችን ለመላክ ጠንክረን እየሠራን ነው። ተጨማሪ እርዳታዎችን የማጓጓዙ አስፈላጊነት የማይቀርና የሚታይ ነው። ለመከላከያ የሚውሉ ቁሳቁሶች አስፈላጊ ስለ መሆን አለመሆናቸው የሚቀርቡ ጥያቄዎችንም እያጠናን ነው። የብረት ቆቦች የጥይት መከላከያ ሰደርያዎች ና ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች በሚቀጥሉት ቀናት በተጨባጭ እንዲቀርብ ይደረጋል። እነዚህ አሁን በመከናወን ላይ ያሉ ቀጣይ እርምጃዎች ናቸው።»

ኂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW