የአል ጀዚራ ስርጭት እና ኤርትራ
ማክሰኞ፣ ጥር 28 2005 ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ድርጅት ትናንት ባወጣው ዘገባው፣ የአልጄዚራ ቴሌቪዥን ሰሞኑን ኤትርራውያን በተለያዩ ሀገራት ያሰሙትን ተቃውሞና በቅርቡ በታየውን የወታደሮች አመጽን በመዘገቡ ያልተደሰተው የኤርትራ መንግስት፣ ጣቢያውን እንዳይታይ ከልክሏል። በድንበር የለሽ ጋዜጠኞች ድርጅት የአፍሪቃ ክፍል ኃላፊ አምብሯይዝ ፒየር፣
«የአስመራ መንግስት አልጀዚራ በኤርትራ እንዳይታይ ለማገድ ወስኗል። ምክንያቱም ስለኤርትራ የአልጄዚራ ዘገባ በግልጽ መንግስትን አላስደሰተውም። ይህ ጣቢያ እስካሁን ሳይነካ ቢቆይም በዚህች ሀገር አሁን ተዘግቷል።»
ድንበር የለሽ ጋዜጠኞች እንደዘገበው ኤርትራውያን አልጄዚራን አንዳይመለከቱ የተከለከሉት ባለፈው ዓርብ የኤርትራ መንግስት የኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር ያወጣውን አዋጅ ተከትሎ ነው። የኤርትራ መንግስት ግን ይህን ክስ አጣጥሎታል። ስለጣቢያው መታገድ የኤርትራ ፕሬዚዳንት ቃለ አቀባይ አቶ የማነ ገብረ መስቀል ለዶቼቬሌ እንዲህ ብለዋል፤
«ይህ ውሸት ነው። በጭራሽ ውሸት። እነ ራሴ አልጄዚራን ከሰባት ሰዓት እስከ ስምንት ሰዓት ለዜና ስከታተል ነበር። በአስመራ ወይም በኤርትራ ያለውን ማንኛውንም ሰው ጠይቅ። ጣቢያው አሁንም እየተሰራጨ ነው። እንዲህ ዓይነቱን አዋጅ ሚኒስቴሩ በጭራሽ አላወጣም።
ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ኤርትራን በፕሬስ ነጻነት አያያዟ ደጋግሞ ከሷታል። ትናንትና ከዚያም በፊትም የወጡ የድርጅቱ መግለጫዎች ከኤርትራ መንግስት የሚሰጠውን ምላሽ አላጠቃለሉም። የመንግስት ወገንን ያላጠቃለለ ዘገባ ለምን አላቀረባችሁም ብሎ ዶቼ ቬሌ ላቀረበው ጥያቄ አምብሯይዝ ፕየረ የኤርትራ መንግስት ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለም ብለዋል፤
«መንግስት ከድንበር የለሽ ጋዜጠኞች የሚቀርቡለትን ጥያቄዎች አይመልስም ምክንያቱም ድርጅታችንን እንደ ኤርትርራ ጠላት፣ እንደ ምዕራባውያን አጋር፣ ሌሎችም አድርጎ ነው የሚወስደው። »
ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ከጥቂት ቀናት በፊት ባወጣው መግለጫው ኤርትራ በፕሬስ ነጻነት አያያዝ ከዓለም ሀገራት የመጨረሻ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል። በኤርትራ በአሁኑ ጊዜ 30 ጋዜጠኞች በእስር እንዳሉም ተናግሯል።
ገመቹ በቀለ
ተክሌ የኋላ