1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሙሩ ወረዳ ተፈናቃዮች ሮሮ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 10 2015

በሆሮ ጉድሩና ምስራቅ ወለጋ ዞን አጎራባች ወረዳዎች የሚኖሩ የአማራና ኦሮሞ ተወላጆች በአካባቢአቸው በተደጋጋሚ ለሚደርሱት ጥቃቶች በተለያየ ስም የሚንቀሰቃሱ ቡድኖችን ተጠያቂ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡በወረዳው ከተማ ላይ ከሚገኙ ተፈናቃዩች በተጨማሪም በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ወደ አጎራባች አማራ ክልል መፈናቃላቸውን ያነጋርናቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

IDPs from Horo guduru wollega
ምስል Seyoum Getu/DW

የኡሙሩ ወረዳ ተፈናቃዮች ሮሮ

This browser does not support the audio element.

ከሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ በነሐሴ 24 /2014 ዓ.ም የተፈናቀሉ በወረዳው ከተማ እና አጋምሳ በተባለ ቦታ የሚገኙ ዜጎች ባለፉት 3 ወራት ምንም ዓይነት ድጋፍ እንዳላገኙ ተናግረዋል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከገጠራማ ስፍራዎች በመሸሽ በወረዳው ከተማ ተጠልለው እንደሚገኙ ከነዋሪዎች ለማወቅ ተችሏል፡፡ የአካባቢውን ሠላም በዘላቂነት በማስፈን መንግስት ወደ ቀያአቸው እንዲመልሳቸውም ጠይቀዋል፡፡  በጉዳዩ ላይ ከወረዳው እና ከዞኑ አስተዳደር እንዲሁም ከክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ወይም (ቡሳ ጎኖፋ) በስልክ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ዶቼቬለ  ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡  ባለፉት ወራት በአካባቢው ስለተፈጸሙት ጥቃቶችና በማህበረሰቡ ላይ ስለደረሱት ጉዳቶች በክልሉ መንግስት በኩል እስካሁን በዝርዝር የተገለጸ ነገር የለም። ነጋሳ ደሳለኝ ከአሶሳ ተጨማሪ ዘገባ ልኮልናል።
ከሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ከተማ ሻምቡ በ92 ኪ.ሜ  ገደማ ርቀት ላይ የምትገኘው አሙሩ ወረዳ የጸጥታ ችግር በተደጋጋሚ ከተከሰባቸው የዞኑ ወረዳዎች አንዷ ናት። ከነሐሴ ወር 2014 ዓ.ም አንስቶ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከወረዳዋ የተለያዩ  ቀበሌዎች ተፈናቅለው አጋምሳና የወረዳው ከተማ ላይ ተጠልለው እንደሚገኙም ተገልጸዋል፡፡ ነሐሴ 24/2014 ዓ.ም በነበረው ግጭት ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን የነገሩን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ነዋሪ ባለፉት ሶስት ወራት ምንም ዓይነት ሰብአዊ ድጋፍ እንዳላገኙ አብራርተዋል፡፡ አጋምሳ የተባለ ከተማ ላይ ከ14 ሺ በላይ የተፈናቀሉ ዜጎች ተመዝገበው እንደነበርም ተናግረዋል፡፡ 
በወረዳው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንገድ መዘጋቱንና አሁንም ጸጥታ ስጋት እንዳለ የነገሩን ሌላው ነዋሪም ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርሳቸው እና የጸጥታ ችግሩም በዘላቂነት እንዲፈታ ጠይቀዋል፡፡ የህክምና ተቋማት አገልግሎት እየሰጡ ባለመሆናቸው ለከፋ ችግር እየተጋለጡ እንደሚገኙም ጠቁሟል፡፡ የከዚህ ቀደሞቹ ጥቃቶችም መልካቸውን እየቀየሩ አርሶ አደሩ እህል ለመሰብሰብ  በተናጠል በሚሰማራበት ወቅት እገታ እና ሌሎች ጥቃቶች እየደረሰባቸው እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ የአካባቢውን ሠላም ለማስጠበቅ በቂ የሆነ የጸጥታ ሐይል እንዲመደብላቸው እና መንግስት ወደ ቀያአቸው እንዲመልሳቸውም ጠይቀዋል፡፡ 
በሆሮ ጉድሩ እና ምስራቅ ወለጋ ዞን አጎራባች ወረዳዎች ላይ የሚኖሩ የአማራ እና ኦሮሞ ተወላጆች በአካባቢአቸው በተደጋጋሚ ለሚደርሱት ጥቃቶች በተለያዩ ስም የሚንቀሰቃሱ ቡድኖችን ተጠያቂ ሲያደርጎ ቆይተዋል፡፡ በወረዳ ከተማ ላይ ከሚገኙ ተፈናቃዩች በተጨማሪም በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ወደ አጎራባች አማራ ክልል መፈናቃላቸውን ያነጋርናቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን  ህዳር 28/2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በሆሮ ጉደሩ ወለጋ አራት ወረዳዎች ውስጥ በተለይም በአሙሩ ወረዳ 10 ቀበሌዎች ውስጥ ጉዳቶች መድረሱን ጠቁሟል፡፡ የሰብአዊ እርዳታና የመሰረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት አለመኖር፣ እንዲሁም በግጭቱ ሳቢያ የሚቋረጡ መንገዶች፣ የምርት ሥራዎች፣ የጤና እና ሌሎች አገልግሎቶች በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎችን ለከፍተኛ ችግርና እንግልት መዳረጋቸውን ኮሚሽኑ በዘገባው ጠቅሷል፡፡  

ምስል Seyoum Getu/DW

ነጋሳ ደሳለኝ

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW