የአማራና ትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች ውሎ
ዓርብ፣ ጥቅምት 27 2013
በአማራ ክልል ጠገዴ ወረዳና በትግራይ ክልል ፀገዴ ወረዳ አዋሳኝ ቦታዎች የነበረውን ግጭት የመከላከያ ሠራዊት ቢቆጣጠረውም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሥራ እንዳልጀመሩ ነዋሪዎች አመለከቱ። ነዋሪዎች እንደሚሉት። በአላማጣና በቆሞቦ ከተሞች ያለው መደበኛ የህዝብ መጓጓዣ እንቅስቃሴ ተቋርጧል። አንድ የጠገዴ ወረዳ ቅርቃር ከተማ ነዋሪ ለዶቼ ቬለ እንደተናገሩት በአካባቢው የጥይት ድምፅ አይሰማም። ሰዎችም በከተማዋ እየተዘዋወሩ ነው። ይህ በአንዲህ እንዳለ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ከተማና በትግራይ ክልል አላማጣ ከተማ መካከል መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎት መቋረጡን አንድ የቆቦ ተማዋ ነዋሪ ገልጸዋል። ህብረተሰቡ ባልተረጋገጡ ወሬዎች እንዳሸበር ያመለከቱት እኚሁ አስተያየት ሰጪ አሁን ቆቦና አካባቢው ሰላም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ እንዳሉት ደግሞ የትግራይ ልዩ ኃይልና የመንግስት ታጣቂዎች ማዶ ከማዶ ከመተያየት በዘለለ ምንም የተፈጠረ ነገር እንደሌለ አመልክተዋል፣ ሆኖም ህብረተሰቡ ግጭት ከተፈጠረ ምን ይዞ መጣ ይሆን? የሚል ሰጋት እንዳለው ተናግረዋል፡፡ የቆቦ ከተማ አስተዳደር አፈጉባዔ አቶ አበበ ይመር በሰጡት አስተያየት ከባንክ አገልግሎት ውጪ ሌሎች የመንግስት ተቋማት በስራ ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ በተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ በህብረተሰቡ ዘንድ መደናገጥ ቢኖርም የማረጋጋት ስራ እየተሰራ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
ዛሬ የቆቦ የገበያ ቀን እንደሆነ ያመለከቱት ነዋሪዎቹ እንደበፊቱ የደመቀ ባይሆንም ገበያተኞች እየተገበያዩ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ዓለምነዉ መኮንን
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ