1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችአፍሪቃ

የአማራና የትግራይ ክልሎች የወሰን ውዝግብ

ሐሙስ፣ መጋቢት 19 2016

ከትግራይ ክልል የተነሱ ታጣቂዎች በራያ አላማጣ ወረዳ አንዳንድ ቀበሌዎች ሰሞኑን ጥቃት ማድረሳቸውን የአካባቢው ነዋሪዎችና አስተዳደሩ ተናገሩ። በግጭቱ የሰዎች ሕይወት መጥፋቱን ንብረት መውደሙንም ናዋሪዎቹና የአካባቢው ነዋሪዎች ለዶቼ ቬሌ ገልጸዋል።

ፎቶ ከማኅደር፤ ራያ አላማጣ
የቀጠለው የአማራና የትግራይ ክልሎች የወሰን ውዝግብ ፎቶ ከማኅደር፤ ራያ አላማጣምስል Alemenew Mekonnen Bahardar/DW

የአማራና የትግራይ ክልሎች የወሰን ውዝግብ

This browser does not support the audio element.

የአማራና የትግራይ ክልል አዋሳኝ በተባሉ አካባቢዎች ሰሞኑን ደም ያፋሰሰ ግጭት መከሰቱን የራያ አላማጣ ነዋሪዎችና አስተዳደሩ አመልክተዋል። ነዋሪዎቹ ከሦስት ቀናት በፊት በራያ አላማጣ በር ተክላይ በሚባል አካባቢ ከትግራ ክልል የተሸገሩ ታጣቂዎች ጥቃት ከፍተው ጉዳት አድርሰውብናል ብለዋል።

የወሎ አማራ የወሰንና ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባልና የአላማጣ ከተማ አስተዳደር ሲቪል ሰርቪስ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መንገሻ ቸሩ በበኩላቸው ሰላምና መረጋጋት በምንፈልግበት ወቅት በርካታ ቁጥር ያለው የትግራይ ተዋጊ ኃይል አካባቢው ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ተናግረዋል።

«አገር ሰላም ነው ብሎ ህዝባችን ሕገ መንግሥታዊ  ውሳኔ የሚሰጠው ነው ጉዳያችን፣ ከአፈሙዝ ነፃ በሆነ መንገድ ሰላማዊ በሆነ መልኩ ፍትህ እንፈልጋለን፣ መልካም አስተዳደር እንፈልጋለን ብልን ባለንበት ሰዓት በሦስት ተሳቢ ተሸከርካሪ የታጠቀ ኃይል በራያ አላማጣ በራሳችን አካባቢ መጥተው በኃይል አጥቅተውናል።» አቶ መንገሻ አያይዘውም ሰሞኑን በነበረው ግጭት የሰው ሕይወት መጥፋቱን የአካል ጉዳት መድረሱንና ንብረት መውደሙንም ለዶይቼ ቬሌ በስልክ አስረድተዋል።

የፌደራል መንግሥት ዘላቂ ሰላም በአካባቢው እንዲያሰፍን የጠየቁት አቶ መንገሻ የሁለቱን ክልል ህዝቦች ወደ ጦርነት የሚገፉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እንዲደረግም አሳስበዋል። የአላማጣ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሀይሉ አበራ በበኩላቸው የትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት ትንኮሳውን እያደረገ ያለው አሁን የአማራ ክልል ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ነው ባይ ናቸው። ድርጊቱም የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምምነት ተግባራዊ እንዳይደረግ የሚደረግ ሥራ እንደሆነም ነው የተናገሩት።

የአማራ ክልላዊ መንግሥት ዛሬ ባወጣው መግለጫ «የትግራይ ተዋጊዎች ከነበሩባቸው አካባቢዎች በመንቃሳቀስየራያአላማጣ ወረዳ ቀሌዎችን በመያዝ ነዋሪዎችን በመግደልና በማሰቃየት ላይ ይገኛሉ» ብሏል። የአማራ ክልላዊ መንግሥት ከዚህ በተጨማሪም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሰሞኑን «የአማራ ክልል የትምህርት ስርዓት የተሳሳተ ካርታ ሰርቷል» ሲል ያወጣውን መግለጫ ውድቅ አድርጓል። የአማራ ክልላዊ መንግሥት ባወጣው በዚህ መግለጫው « የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለሀገሪቱ ቋሚ የቀውስ ምንጭ ከሚያደርጉት ተግባራት እንዲታቀብ፣ ሀገራችንንና ሁለቱን ክልሎች ወደ ቀውስ ከሚያስገቡ ተግባራት በመቆጠብ ከአጓጉል የካርታ ፖለቲካ ጨዋታ እንዲወጣና የህዝብን ፍላጎት ማዕከል ባደረጉ ውይይቶች ላይ እንዲያተኩር እንመክራለን» ብሏል።

ዶቼ ቬለ ከአማራም ሆነ ከትግራይ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎች ተጨማሪ አስተያት ለማካተት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW