1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባኤ ጥሪ

ሰኞ፣ ነሐሴ 15 2015

የምሁራን መማክርት ጉባኤው ወቅታዊ ጉዳይ በማስመልከት ሲል ባወጣው መግለጫ፤ በአማራ ክልል የተፈጠረውን የፖለቲካ፣ አስተዳደራዊ እና የጸጥታ ቀውስ በሠላማዊ መንገድ መፍትሄ እንዲያገኝ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረኩ እገኛለሁም ብሏል፡

ፎቶ ከማሕደር፤ ጎንደር ከተማ
የመማክርት ጉባኤው በአማራ ክልል የተፈጠረውን የፖለቲካ፣ አስተዳደራዊ እና የጸጥታ ቀውስ በሠላማዊ መንገድ መፍትሄ እንዲያገኝ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑንም ገልጿል። ፎቶ ማሕደር፤ ጎንደር ከተማምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

የጸጥታ ቀውስ በሠላማዊ መንገድ መፍትሄ እንዲያገኝ ጥረት እየተደረገ ነዉ

This browser does not support the audio element.

አማራ ክልል ውስጥ የሚደረገው በመሳሪያ የተደገፈ ግጭት ቆሞ አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ ሲል የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባኤ ጠይቋል፡፡

የምሁራን መማክርት ጉባኤው ወቅታዊ ጉዳይ በማስመልከት ሲል ባወጣው መግለጫ፤ በአማራ ክልል የተፈጠረውን የፖለቲካ፣ አስተዳደራዊ እና የጸጥታ ቀውስ በሠላማዊ መንገድ መፍትሄ እንዲያገኝ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረኩ እገኛለሁም ብሏል፡፡

የምሁራን መማክርት ጉባኤው መግለጫ በአማራ ክልል የተፈጠረው ችግር መሰረታዊ ምክኒያቱ የአማራ ህዝብ ላይ የደረሰው ግፍና መደል ነው ይላል፡፡ የምሁራን መማክርት ጉባኤው ችግሩን በኃይል እነ በመገዳደል ለመፍታት መሞከር የከፋ ሰብኣዊና ቁሳዊ ጉዳት ከማድረስ አልፎ ችግሩን ያወሳስበው ካልሆነ በቀር ዘላቂ መፍትሄ አያስገኝም ብሏልም፡፡

ጉባኤው አክሎም በክልሉ የተፈጠረውን ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊ እና የፀጥታ ቀውስ በዘላቂነት ለመፍታት ለተፈጠረው ችግር ስረምክኒያት የሆኑትን ስርዓታዊ በደሎች እና ጥፋቶች ለይቶ በቅንነትና በፍትሃዊነት መርህ ችግሮችን በውይይት እና በንግግር ለመፍታት ከልብ አምኖ ለተግባራዊነቱም በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ነውም ብሏል፡፡

የመማክርት ጉባኤው ጽህፈት ቤት ኃላፊ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ እንዳመለከቱትም፤ አሁን በአማራ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ የተከማቹ ያሏቸው ችግሮች የፈጠሩት ነው፡፡ “ህዝቡ ላይ የደረሱ ችግሮች ከነመንስኤዎቻቸው በመረዳትና መለየት ችገረሩን በውይይት መፍታት ይገባል” ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

አማራ ክልል ውስጥ የሚደረገው በመሳሪያ የተደገፈ ግጭት ቆሞ አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ ሲል የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባኤ ጠይቋል፡፡ምስል፦ Privat

የመማክርት ጉባኤው በመግለጫው፤ በተለያዩ ጊዜያት በፖለቲካ ምክኒያት ታሰሩ ያሏቸው ምሁራን፣ ፖለቲከኞች እና የፖለቲካ አንቂዎች እንዲሁም ከሰሞኑ አዲስ አበባ ውስጥ በማንነታቸው በጅምላ የታሰሩ ያሏቸው እንዲፈቱ ጠይቋል፡፡ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ዶ/ር ዳዊት አክለው በሰጡት ማብራሪያም፤ “ግጭትን የሚያባብሱ ፍረጃዎች እና ቅስቀሳዎች እንዲሁም ህዝብ በህዝብ ላይ እንዲነሳ የሚያደርጉ የጥላቻ ንግግሮች በአስቸኳይ እንዲቆሙም ጥሪ ቀርቧል፡፡ ህዝብን በጅምላ መፈረጅ ችግሩን ሊያባብስ ይችላል፡፡ የችግሩን ስረመሰረታዊ በመረዳት ለእልባል መስራት ይበጃልም” ብለዋል፡፡

በኃይል ዘላቂ መፍትሄ አይገኝም ያለው የምሁራኑ መማክርት ጉባኤ ሁሉም ተፋላሚ ኃሎች እና የክልሉ ህዝብ በሚሳተፉበት ውይይት ማድረግ ያለውን ተገቢነትም አስረድቷል፡፡ በግጭቱ የደረሰው ሰብኣዊ እና ቁሳዊ ጉዳት በኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን ተጣርቶ ለህዝብ ይፋ እንዲሆንም የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባኤው በዚሁ መግለጫ ጥሪውን አሰምቷል፡፡

የምሁራኑ መማክርት ጉባኤው በመግለጫ ስላቀረበው ጥሪ ከመንግስት ወገን ምላሽ ለማግኘት ለመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ብንደውልም ስልካቸው ባለመነሳቱ አስተያየታቸውን ማካተት አልተቻለም፡፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በበኩሉ ከአማራ ክልሉ ግጭት ጋር በተያያዘ ደረሱ የተባሉትን የሰብኣዊ እና ቁሳዊ ውድመቶችን ለማጥናት ባለሙያዎቼን እያሰማራሁ ነው ብሏል፡፡ በኮሚሽኑ የሰብዓዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ክፍል ዋና ኃላፊ ዶ/ር ሚዛኔ አባቴ ለዶቼ ቬለ እንዳሉት የአዳዲስ መረጃዎች ጥንቅር እንዳለቀ ለህዝብ ይፋ ይሆናል፡፡ 

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW