1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የአማራ ክልሉ የድሮን ጥቃት አንድምታ እና የትግራይ ክልል ጊዜያያዊ አስተዳደር አዲሱ ካቢኔ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 16 2017

የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በፈጸማቸው የድሮን ጥቃቶች እና የተገደሉ ሰዎች አንድምታ፤ አዲሱ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አሰተዳደር ፕሬዚዳንት ታደሰ ወረደ አዲስ ካቢኔ ካዋቀሩ በኋላ ተቃዉሞ ገጥሟቸዋል። አስተዳደርዎ አካታች አይደለም የሚል ክስ መቅረቡ ተሰምቷል።

Akinci Drohne
ምስል፦ IMAGO/Pond5 Images

የሚያዝያ 16 ቀን 2017 ዓ/ም የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ዝግጅት

This browser does not support the audio element.

ሰላም ጤና ይስጥልን አድማጮቻችን የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በፈጸማቸው የድሮን ጥቃቶች እና የተገደሉ ሰዎች ማንነት፤ አዲሱ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አሰተዳደር ፕሬዚዳንት ታደሰ ወረደ አዲስ ካቢኔ ካዋቀሩ በኋላ ተቃዉሞ ገጥሟቸዋል። አስተዳደርዎ አካታች አይደለም የሚል ክስ ማስተናገዱን በተመለከተ የተሰጡ አስተያየቶችን ተሰባስበዋል።
። 
የመከላከያ ሠራዊት ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ፈጸመ በተባለ የድሮን ጥቃት በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል። የመከላከያ ሠራዊት በበኩሉ በክልሉ ሰሜን ሸዋ እና ጎጃም ወሰድኩ ባለው ወታደራዊ እርምጃ በመቶዎች የሚቆጠሩ እና «ጽንፈኛ» ያላቸውን ታጣቂዎች መግደሉን አስታውቋል። የመከላከያ ሠራዊት ምንም እንኳ በወታደራዊ ዘመቻው ድሮን ስለመጠቀሙ ያለው ነገር ባይኖርም በተለይ ጎጃም ውስጥ በተፈጸመ ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸው ተሰምቷል። የጥቃቱን መድረስ እና የተጎጂዎችን ማንነት በተመለከተ ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጫ ማግኘት አስቸጋሪ ቢሆንም የዉጊያ ጥቃት መቀጠል ያስከለውን ማኅበራዊ መቃወስ በተመለከተ በማኅበራዊ ዘዴዎች  በርካቶች አስተያየታቸውን አጋርተዋል።

በአማራ ክልል የሚደረገዉ ግጭት በጤና ባለሙያዎች ስራ ላይ ያደረሰዉ ጫና
ጌታቸውሢሣይ የትኛውም ጥቃት የሚያስከትለውን አንድምታ ባጋሩበት አስተያየታቸው 
«አንድ ሰው በአማካይ በእናትም በአባትም በኩል ያሉ የቅርብ ዘመዶቹ 5 ወንሞችና እህቶች ፣ 5 አጎቶችና አክስቶች ቢኖሩት ፣ እነርሱም እየአንዳንዳቸው 5 ልጆች ቢኖራቸው ፣ በአጠቃላይ 75 ሰዎች ይሆናሉ ። ስለዚህ አንድ ሰው ሲገደል በትንሹ ከ75 ሰዎች ጋር ደም ተቃባን ማለት ነው። ብዙ ሰዎች በተገደሉ ቁጥር ብዙ ሰዎች ጋር ጠላትነት ፣ ተበቃይነት ፈጠርን ማለት ነው ። ብዙ ተበቃዮች በበዙ ጊዜ ደግሞ የበለጠ ጥላቻ ፣ ገዳዮች ፣ አፈናቃዮችና ጨፍጫፊዎች ፈጠርን ማለት ነው ። ሲጠቃለል ሰዎች ከመግደል በፊት ሌሎች ሰላማዊ አማራጮች እስከ መጨረሻው ድረስ መጠቀም የተሻለ ነው ማለት ነው።»
 ጋያ ጋላጌር በሚል ስም በፌስ ቡክ ባሰፈሩት አስተያየት 
«አሁን ትምህርት ቤት በግድ እንዲዘጋ ተማሪ እንዲበተን ት/ቤቶችም የታጣቂ ካምፕ ሆነው መምህርና ተማሪ በሚረሸንበት ጎጃም የት/ቤት አጥር ሢያጥሩ 100 ንፁሐን በድሮውን ሞቱ ሚለው ዜና እንዴት ሊታመን ይችላል?» ሲሉ በጥቃቱ በሰላማዊ ሰዎች ደረሰ የተባለውን ጉዳት  ይጠይቃሉ።

መምህርና ተማሪ በሚረሸንበት ጎጃም የት/ቤት አጥር ሢያጥሩ 100 ንፁሐን በድሮውን ሞቱ ሚለው ዜና እንዴት ሊታመን ይችላል?» ምስል፦ IMAGO/Depositphotos

በመንግሥት እና በፋኖ መካከል የሚካሄደዉ ጦርነት የአማራ ክልል ንግድን ማቀዛቀዙ
ስለአባት ጌትነት በበኩላቸው ባሰፈሩት አስተያየት 
«አዎ በገበያ ፣በሥራ እና በጉዞ ላይ ያሉ ንጹሐን ተጨፍጭፈዋል።  በየጊዜው በዚህ መንገድ የተገደሉት ንጹሐን ቁጥራቸው ይሔ ብቻ አይደለም ። 30 እና 40 ሺህ ይደርሳል ። የታጠቀ ያለውን ኃይል ግን አይደለም 300 ይቅርና 3 አልገደለም ።» ሲሉ መከላከያ በታጣቂዎች ላይ ወሰድኩ ያለውን እርምጃ አጣጥለዋል። 
ካሳሁን ሙላቱ ደግሞ ጥቃትም ይሁን አጠቃላይ የጦርነቱን ዳፋ በተመለከተ ባሰፈሩት ሃሳብ 
«በየትኞቹም ተቀናቃኝ የኢትዮጵያ ልጆች የተፈጸመ ሞት ለኢትዮጵያ ጉዳት ነው። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሆነ ብሔር በኢትዮጵያ ላይ እኩል መሆናቸው መቀበል ቢቻል ኖሮ ጦርነትና ደም መፋሰስ ባልኖረ ነበር።  ለኢትዮጵያ ሠላም ብቸኛ መፍትሔ ኢትዮጵያ የጋራ ቤታችን መሆኗን አምኖ መቀበልና በመከባበር ለኢትዮጵያ ሰላም መሥራት ብቻ ነው።» ብለዋል።
አበበ ኡቴ አላንቼ በበኩላቸው አስተያየታቸውን እንዲህ ሲሉ ነበር ያጋሩት።

በአማራ ክልል ያለው ጦርነት በኤች አይ ቪ ህክምና አሰጣጥ ላይ ጫና መፍጠሩ
«እስቲ እያንዳንዳችን ቆም ብለን እናስብ ። የእኔ የሆነ የቱ ነው? እኛ ሁላችን ኢትዮጵያዊያን ነን። ከአንድ ደም ተፀንሰን የተወለድን ሰዋች ነን። ነገር ግን ይህንን አመጣጥ ረስተን ነው እንደው በዚች በምታልፈው ቀን ወንድም ወንድሙን የሚገድለው፥ የምንበላላው፥ ዘር ሐረግን የምንጨፍጭፈው? ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ ሁሉ አንድ አካል ስለሆንን ሰከን ብለን እናስብ ።ይህንንም መጥፎ አስተሳሰብ ከራሳችን እናስወግድ ፤ስለ ኢትዮጵያዊነት ፥ስለአንድነት እናስብበት፤ ቀኖች ያልፋሉና የሰው ፍጡርን በራሱ አስመስሎ የፈጠረ እግዚአብሔርን ብለን እርስ በእርሳችን አንባላ፤ ነገርን ሁሉ ትተን ወደ ማኅበረሰብ ሰላምን ለማስፈን በፍቅርና በአንድነት ሆነን እንነሳ ። ኢትዮጵያ ትቅደም ፥ሰላም አንድነት ይስፈን።»

«በየትኞቹም ተቀናቃኝ የኢትዮጵያ ልጆች የተፈጸመ ሞት ለኢትዮጵያ ጉዳት ነው። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሆነ ብሔር በኢትዮጵያ ላይ እኩል መሆናቸው መቀበል ቢቻል ኖሮ ጦርነትና ደም መፋሰስ ባልኖረ ነበር።ምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

 

አዲሱ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አዲስ ካቢኔ ማዋቀራቸውን ተከትሎ ፤ ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ ትችት ቀርቦባቸዋል። ጄነራሉ ያዋቀሩት ካቢኔ አካታች አይደለም የሚል ትችት ሲቀርብ ወደ አንድ ወገን ያዘነበለ እና የፕሪቶሪያውን ስምምነት ያላከበረ ነው የሚል ወቀሳንም አስከትሎባቸዋል። ይህንኑ በተመከለተ በርካቶች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተለያዩ አስተያየቶችን አጋርተዋል። 
  ሰለሞን ይርጋ በፌስ ቡክ ባጋሩት መልዕክታቸው «ከስህተት አለመማር ምን ማለት ነው? ለትግራይ ሕዝብ ለምን ሰላም አትሰጡትም» ሲሉ ፤
ቻማዬ ቻማዩ በሚል የፌስ ቡክ ስም የሰፈረ ሃሳብ  «በመሰረቱ ሁለት ህወሓት / የእገሌ /ህወሓት የሚባል ነገር የለም። የሌለና ያልነበረ ትርክት መቆም አለበት» ይላሉ፤ 
ወዳጆ ዴሬሳ በበኩላቸው «ሸሽቶ መጥቶ ሥልጣን ለቆ መጮህ ሳይሆን እዛው ሆኖ የመጣውን መጋፈጥ ይገባ ነበር ። ለማስተካከል ከተፈለገ አሁን ባለሥልጣኑ ሌላ ነው። ማድረግ ያለበትን ለምን አደረገ የሚያውቀው እሱ እንጂ የሸሸው አይደለም » ይላሉ፤

አዲሱ የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ካቢቤና ተቃውሞው
ዳርጌ ጉቱ  የተሰማውን እሰጣገባ በተመለከተ ባጋሩት መልዕክት « ሕዝብ ግን ማን ነዉ?» ሲሉ ይጠይቃሉ ። «መቼስ ተሰምቶ ያቃል? በትግራይ መፈንቅለ መንግሥት እንጂ በሕዝብ ጫና የወረደ መንግሥት የለም።» ነው ያሉት። 
ለገሰ ጋላሮ ደግሞ «ግራ የገባው የሀገሪቱ ፖለቲካ መጨረሻው ይኼው ነው። አረ ለመሆኑ ጌታቸው ረዳ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አመራርነት ተነስተው ወደ ፌዴራል መጥተው የለም እንዴ?» ሲሉ ጠይቀዋል። 
ታሪኩ እርጎጎ ደግሞ እንዲህ ይላሉ ።« ህወሓት በሴራ የተሸበበ ድርጅት ነው ጄኔራሉም የመፈንቅለ መንግሥቱ አንድ አካል ነበሩ ጌች ሕይወቱ መትረፉ ከምንም በላይ ያስደስተኛል ።»
ቴ ጄ ገ በተባለ ምህጻረ ቃል በሰፈረ መልዕክት «መቀሌ ውስጥ  እያሉ ያልተሰሙ በስደት ላይ ሆነው የሚያወሩትን ማን ይሰማል» በማለት ጠይቀዋል። 
የበላይ አስፋው አስተያየት ደግሞ፤
«ይሄ እኔ ያላማሰልኩት አይጣፍጥም ዓይነት ፖለቲካ ነው። በእርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ የትኛውም ዓይነት የፖለቲካ አደረጃጀት ሲደራጅ/ሲዋቀር ለሕዝብ ጥቅም እንዲሆን አቅምና እውቀትን መሠረት ባደረገ መልኩ ሳይሆን የአንድን አንጃ ቡድን ፍላጎትና ግብ ሊመታ በሚችል መልኩ ታስቦ ስለሚደራጅ በጌታቸው አሳብ ብዙም አለመገረም ነው።» የሚል ነው።
መሰረት ለማ በበኩላቸው ለአዲሱ ፕሬዚዳንት ሕግ አልባውን አካሄድ ምነው ሳያስወግዱ ተነሱሳ እንዲያውም በማን ዘመን ተፈጠረ? ባይናገሩ ጥሩ ነው መልካም የሥራ ጊዜ ይሁንሎ
በጣፋ ብቁ አስተያየት ደግሞ እንዲህ ይላል።  

አዲሱ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አዲስ ካቢኔ ማዋቀራቸውን ተከትሎ ፤ ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ ትችት ቀርቦባቸዋል።ምስል፦ Office of the Prime Minister-Ethiopia

በትግራይ ክልል በተፈጸሙ ወንጀሎች ተጠያቂነት ይረጋገጥ ፤ ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች
«የትግራይ ሕዝብ ግምገማ መሆን ያለበት ካቢኔዎቹ እነማን ናቸው ሳይሆን ታደሰ ወረደ ከጌታቸው ረዳ የተሻለ ለማህበረሰቡ ምን ሰራ የምለው ላይ መሆን አለበት! በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ግን የተሻለ ምንም አይሠሩም።» 

ለገሰ ጋላሮ ደግሞ «ግራ የገባው የሀገሪቱ ፖለቲካ መጨረሻው ይኼው ነው። አረ ለመሆኑ ጌታቸው ረዳ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አመራርነት ተነስተው ወደ ፌዴራል መጥተው የለም እንዴ?» ሲሉ ጠይቀዋል። ምስል፦ Office of the Prime Minister-Ethiopia

ተከታዩ አስተያየት የሳሮን ዳዊት ነው ። « ሽማግሌዎቹ የህወሓት ኣምባገነን መሪዎች እኛ ብቻ ነን የነቃን ብለው ነው የሚያስቡት። ጌታቸው ረዳን በብረት መፈንቀለ መንግሥት ኣካሂደው ፕሬዝዳንቱ ትግራይን ለቆ እንዲሄድ ካስገደዱት በኋላ፣ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን እንደ ያዙ ሲያረጋግጡ 360 ድግሪ ተገልብጠው ፣ ጌታቸው የኛ ጀግና ና ወደ ትግራይ ጋቢ እና ኩታ እንሸልምህ የሚሉ ናቸው።» የሚል መልዕክት አስፍረዋል። 
አበባየሁ አምባው ደግሞ አልገባኝም አስረዱኝ ይላሉ ። « የተደረገው የሥልጣን ሽግግር ጠቅላይ ሚንስትሩ በተገኙበት በትግራይ መቐለ ቢሆን ትልቅ ትርጉም ይኖረው ነበር » ያሉት አቶ ጌታቸው « ትናንትን እየመዘዙ ቁርሾና ቂም በቀል ማቀጣጠል ፋይዳ የለውም » በማለት ተናግረዋል። «ይህ አገላለፅ የገባው ወይም የተረዳ ሰው ካለ አብራሩልኝ እስኪ?» በማለት ጠይቀዋል። እንግዲህ አድማጮች እኛም ለዛሬ ብለን በመራረጥናቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያሰባስብናቸውን አስተያየቶች በዚሁ ልንቋጭ ወደድን ሳምንት በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ዳግም ለመገናኘት ቀጠሮ እንያዝ ፤ ጤና ይስጥልን።
ታምራት ዲንሳ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW