የአማራ ክልል ምክርቤት ጉባኤና የነዋሪዎች አስተያየት
ረቡዕ፣ የካቲት 5 2017
የሠላም እጦቱ በህብረተሰቡ ላይ ዘርፈ ብዙ ችግር አስከትሏል
የአማራ ክልል ምክር ቤት በባሕር ዳር ጉባኤ እያካሄደ ነው፡፡ ለምክር ቤቱ የ6 ወራት ሪፖርት ያቀረቡት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አርጋ ከበደ ባለፈው 1 ዓመት ተኩል በአማራ ክልል የተፈጠረው የሠላም እጦት በኅብረተሰቡ ላይ በርካታ ቁሳዊ፣ ሰብአዊና ሰነ ልቦናዊ ጉዳት አስከትሏል ብለዋል። ርዕሰ መስተዳደር አረጋ በአብዛኛው የአማራ ክልል ሠላም ማስፈን ተችሏል ሲሉ ለምክር ቤቱ አመልክተዋል፡፡የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ መደበኛ ጉባኤ
“በከተሞች ዝርፊያና ግድያ አልቆመም” አስተያየት ሰጪዎች
አስተያየት የሰጡን በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ግን አሁንም ክልሉ በፀጥታ ችግር ውስጥ እንደሆነ ነው የገለፁልን። በከተሞች ግድያና ዝርፊያ ባልቆመበት ሁኔታ ሠዎች እንደልብ ከቦታ ቦታ በማይንቀሳቀሱበት፣ በተለይ በገጠራማው የአማራ ክልል አካባቢዎች ሠላሙ ተረጋግጧል ለማለት እንደማያስችል ተናግረዋል።
“ሠላም ነው፣ የፀጥታ ችግሩ እየቀነሰ ነው፣ የሚባለው ነገር አስቸጋሪ ነው፣ ከተሞች በአንፃራዊነት ሠላም ናቸው፣ ከከተማ ውጪ ያሉ አካባቢዎች ግን ሠላም አይደሉም፣ የተረጋጋ ነው የሚባለው ነገር ለእኔ ትርጉሙ አይገባኝም” ብለዋል፡፡ሌላዋ አስተያየት ስጪ በበኩላቸው ታች ያለው መዋቅር ባለመኖሩ የመረጃ ልውውጥ የሚባል ነገር የለም ሲሉ ነው አስተያየት የሰጡት፡፡
በርካታ መምህራንና ተማሪዎች ከትምህርትና ማስተማር ውጪ በሆኑበት ሁኔታ “በአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች ሠላም ሰፍኗል” ማለት አይቻልም ነው ያሉት፡፡
“የሸቀጦች ዋጋ ቀንሷል” ስለመባሉና የአስተያየት ሰጪዎች ምላሽ
የገበያ መረጋጋትን በተመለከት እዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በሪፖርታቸው ካለፈው ዓመት ሲነፃፀር ባለፉት 6 ወራት ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ዋጋ በ9.9 ከመቶ ቅናሽ ማሳየቱንና ምግብ ነክ የሆኑት ደግሞ በ9.4 በመቶ ቅናሽ አሳይተዋል ሲሉ በሪፖርታቸው አስረድተዋል።፡
የደሴ ከተማ አስተያየት ሰጪ ግን ይህን አይቀበሉም።እውነታውን ህዝብ ያውቀዋል ነው ያሉት።
የኑሮ ውድነቱ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰበትና ነዋሪው ውሎ መግባት የተቸገረበት መሆኑን ነው አስተያየት ሰጪው ያመለከቱት፡፡ የኑሮ ውድነቱን ህብረተሰቡ ምንም ጥናት ማድርግ ሳያስፈልግ ያውቀዋል ሲሉ አክለዋል፡፡የአማራ ክልል ባለሥልጣናት የሰላም ጥሪና የድርድር ሃሳቦቻቸው
1 ሚሊዮን 316 ሺህ ሠዎች በወባ ሲያዙ 70ዎቹ ህይዎታቸው አልፏል
በዚህ ዓመት በርካታ የወባ ታማሚዎች እንደነበሩ ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በጤና ተቋማት ብቻ 70 ሠዎች በወባ ህመም ህይዎታቸው ማለፉን በሪፖርታቸው ጠቁመዋል።
ባለፉት 6 ወራት በአማራ ክልል 3 ሚሊዮን 112ሺህ 722 ሠዎች የወባ ምርመራ ማድረጋቸውን ያነሱት አቶ አረጋ 1 ሚሊዮን 315ሺህ 970 ሠዎች የወባ ህመም ተገኝቶባቸው ህክምና ያገኙ ሲሆን 70ዎቹ ህይዎታቸው ማለፉን ገልጠዋል።
1.5 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው መድኃኒትና የህክምና ቁሳቁሶች ለጤና ተቋማት ተሰራጭተዋል
ርዕሰ መስተዳድር አረጋ 1.5 ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው መድኃኒትና የህክምና ቁሳቁሶች ወደ ህክምና ተቋማት መላካቸውን አብራርተዋል፡፡ የመድኃኒት አቅርቦትን በተመለከተ የፈረስ ቤት ሆስፒታል የሥራ ባልደረባ ባለፉት 6 ወራት የመድኃኒትም ሆነ የህክምና ቁሳቁስ እንዳልቀረበላቸው ሲግልፁ፣ በአንፃሩ የቡሬ ሆስፒታል ባልደረባ ቀደም ሲል ከነበረው የተሻለ አቅርቦት መኖሩን ለዶይቼ ቬሌ ተናግርዋል፡፡የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባኤ ጥሪ
3 ሺህ 466 ትምህርት ቤቶች አገልግሎት እየሰጡ አይደልም
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በተለያዩ ወቅቶች በሰጣቸው መግለጫዎች በ2017 ዓም የትምህርት ዘመን 7 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመዝገብ ቢያቅድም ባለው የፀጥታ ችግር ያን ማሳካት አልቻለም፡፡ ርዕሰ መስተዳድር አርጋ ትምህርትትን በተመለከተ በሪፖርታቸው እንዳመለከቱት ካለው የፀጥታ ችግር ተያይዞ በአማራ ክልል ወደ ትምህርት ገበታ የመጡ ተማሪዎች ቁጥር ክ2.7 ሚሊዮን አይበልጥም፣ 3ሺህ 466 ትምህርት ቤቶችም አገልግሎት እየሰጡ አይደልም ብለዋል።
ትናንት የተጀመረው የአማራ ክልል ምክርቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት 9ኛ መደበኛ ጉባኤ የፊታችን አርብ ይጠናቅቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ዓለምነው መኮንን
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ