1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ ክልል ቀውስ፦ ገፊ ምክንያቶች፣ ዳፋው እና በውይይት የመቋጨት ተስፋ

ሰኞ፣ ነሐሴ 8 2015

በአማራ ክልል ሲብላላ የቆየው ቅራኔ በሣምንቱ መጀመሪያ ወደ ውጊያ ቢያመራም የመረጋጋት ዝንባሌ አሳይቷል። የቀውሱ ገፊ ምክንያቶች ምንድናቸው? በውይይት ካልተቋጨ በአማራ ክልል እና በኢትዮጵያ ላይ የሚያስከትለው ዳፋ ምን ሊሆን ይችላል? ዶክተር ታደሰ ጥሩነህ፣ ዶክተር ብዙነህ ጌታቸው እና ዶክተር ሰማኸኝ ጋሹ በዚህ ውይይት ተሳትፈዋል።

በጦርነት የወደመ ታንክ እና የአማራ ክልል ፖሊስ
በፕሪቶሪያ በተፈረመ ግጭት የማቆም ሥምምነት በተገታው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አጋር የነበሩት የመከላከያ ሠራዊት እና የፋኖ ታጣቂዎች ወደለየለት ግጭት የገቡት ባለፈው መጋቢት የፌድራል መንግሥት በክልሎች የሚታዘዙ ልዩ ኃይሎች አባላት "ወደ ተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች እንዲገቡ" መወሰኑን ካስታወቀ በኋላ ነው።ምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images

ውይይት፦ የአማራ ክልል ቀውስ ገፊ ምክንያቶች፣ ዳፋው እና በውይይት የመቋጨት ተስፋ

This browser does not support the audio element.

የአማራ ክልል የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ካስከተለው ዳፋ በቅጡ ሳያገግም የሰላማዊ ሰዎች ሞት እና አለመረጋጋት ያስከተለ የጸጥታ እና የፖለቲካ ቀውስ ገጥሞታል። በፕሪቶሪያ በተፈረመ ግጭት የማቆም ሥምምነት በተገታው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አጋር የነበሩት የመከላከያ ሠራዊት እና የፋኖ ታጣቂዎች ወደለየለት ግጭት የገቡት ባለፈው መጋቢት የፌድራል መንግሥት በክልሎች የሚታዘዙ ልዩ ኃይሎች አባላት "ወደ ተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች እንዲገቡ" መወሰኑን ካስታወቀ በኋላ ነው። መንግሥት ውሳኔው በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ እንደሚሆን ቢያስታውቅም በተለይ በአማራ ክልል ተቃውሞ ገጥሞት ነበር። 

የክልል ልዩ ኃይሎችን የማፍረሱ ስራ እና የገጠመው ተቃውሞ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት "በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሚታየውን በትጥቅ የተደገፈ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ በመደበኛ የሕግ ማስክበር ሥርዓት ለመቆጣጠር ወደ ማይቻልበት ደረጃ የተሸጋገረ በመሆኑ" የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲደነገግ የወሰነው ሐምሌ 28 ቀን 2015 ነበር። ነሐሴ 3 ቀን 2015 በባሕር ዳር እና በጎንደር ከተሞች በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተደረገ ውጊያ ሰዎች መገደላቸውን የየከተሞቹ ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። እስካሁን በአማራ ክልል በአጠቃላይ ምን ያክል ሰዎች እንደተገደሉ የሚታወቅ ነገር የለም። 

የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ነሐሴ 05 ቀን 2015 በሰጠው መግለጫ "የሰላም አማራጮች ለማንኛውም፤ ለሁሉም ምንጊዜም ክፍት መሆናቸውን" ገልጿል። የመንግሥት ኮምዩንኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ በንባብ ባሰሙት መግለጫ "ከእነዚህ ኃይሎች የሚጠበቀው የታጠቋቸውን እና ያከማቿቸውን ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎች በማስቀመጥ ወደተዘጋጁላቸው ካምፖች መሰባሰብ ብቻ" እንደሆነ ተገልጿል። መግለጫው "እነዚህን ኃይሎች ወደ ሰላም ለማምጣት የሚፈልጉ አካላት ካሉም ይኸንንው መንገድ ብቻ መጠቀም" እንደሚኖርባቸው አስገንዝቧል።

የአማራ ልዩ ኃይል «አልተበተነም» ባለስልጣን

በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ቀውስ ዋንኛ ገፊ ምክንያቶች ምንድናቸው? ግጭቱ በውይይት እና በድርድር ሊቋጭ ይችላል? ቀውሱ ካልተፈታ ከጦርነት ዳፋ በቅጡ ባላገገመው የአማራ ክልልም ሆነ በኢትዮጵያ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ምን ያክል ይከፋል?በዚህ ውይይት ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ ከመንግሥት ኮምዩንኬሽን አገልግሎት እና ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ተወካይ ለመጋበዝ በተደጋጋሚ የተደረገው ጥረት አልተሳካም። 

በውይይቱ በዩናይትድ ኪንግደም በርሚንግሐም ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር ብዙነህ ጌታቸው፤ በጄኔቫ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ሥራ በማከናወን ላይ የሚገኙት የሕግ ባለሙያው ዶክተር ታደሰ ሞገስ እና በማሳቹሴትስ በሚገኘው ኢንዲኮት ኮሌጅ የዓለም አቀፍ ሕግ እና ሰብዓዊ መብቶች ተባባሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ሰማኸኝ ጋሹ ተሳትፈዋል። 

ሙሉ ውይይቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ፦ 

እሸቴ በቀለ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW