1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችአፍሪቃ

የአማራ ክልል ባለሥልጣናት የሰላም ጥሪና የድርድር ሃሳቦቻቸው

እሑድ፣ ሰኔ 30 2016

በአማራ ክልል ሰላም እንዲሰፍን የክልሉ ባለሥልጣናት በትጥቅ ከሚፋለሙት ጋር ለመደራደር ከክልሉም ሆነ ከፌደራል መንግሥት በኩል ዝግጁነት መኖሩን እየገለጹ ነው። ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ተንታኝ ግን የክልሉን ሰላም ያደረፈረው ግጭት እየተወሳሰበ መሄዱን በማመልከት በሀገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት መሪዎች የሚፈታ እንደማይሆን ያመለክታሉ።

የአማራ ክልል
በአማራ ክልል የተካሄደው የሰላም ጉባኤ ተሳታፉዎች በከፊል ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የአማራ ክልል ባለሥልጣናት የድርድር ሃሳብ

This browser does not support the audio element.

በአማራ ክልል ያለው የጸጥታ ችግር ከጠብመንጃ ውጪ ሁሉንም ነገር ሰጥቶ በመቀበል መርህ መፈታት እንደሚኖርበት የክልሉ ፕሬዝደንት በቅርቡ አሳስበዋል። የአማራ ክልል ፕሬዝደንት አቶ አረጋ ከበደ ይህ እውን እንዲሆንም መንግሥት ላይ ጭምር ተጽእኖ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ነው የተናገሩት። «ከብረት በመለስ በውይይት፣ በድርድር፤ በሰጥቶ መቀበል ሕዝብ እና ሀገርን በሚያሳድግ አቅጣጫ መነጋገር አለብን መወያየት አለብን የሚል አቋም መያዝ አለበት። መንግሥትንም ጭምር ይህን አማራጭ እንዲከተል፤ በተጨባጭ ውጊያ እያደረገ ያለው ኃይልም ከፍተኛ ተጽዕኖ ማድረግ ወደሰላም አማራጭ እንዲመጣ የሚደርግ ውይይት ማድረግ ይጠበቅበታል።»

ባለሥልጣኑ ይህን ያሉት በአማራ ክልል በያዝነዉ ሳምንት የተካሄደውን የሰላም ጉባኤ በከፈቱበት ንግግር ነው። ከእሳቸው በተጨማሪም በዚህ ጉባኤ ላይ የተገኙት የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገርም በበኩላቸው የአማራ ክልል ጸጥታ ማጣት የክልሉን ነዋሪዎች እንቅስቃሴ እንዳስተጓጎለ በማመልከት መፍትሄ ያሉትን ተመሳሳይ የድርድር ሃሳብ አንስተዋል። ወደክልሉ ከአዲስ አበባም ሆነ ወደ አዲስ አበባ በመኪና ለመመላለስ አስቸጋሪ ሁኔታ መፍጠሩን፤ የክልሉ በርካታ ተማሪዎች መማር አለመቻላቸውን፤ የሀገሪቱን ከፍተኛ ምርት ያመርት የነበረው የአማራ ክልል አርሶ አደር አሁን ማምረት አለመቻሉን፤ መንግሥትም የልማት ሥራዎችን ማከናወን እንዳዳገተውም ዘርዝረዋል። እስከዛሬ ከበቂ በላይ ተገዳድለናል ያሉት አቶ አገኘሁ መንግሥት ለድርድር ዝግጁ ነው ባይ ናቸው።

የአማራ ክልል የጸጥታ ሁኔታ

መንግሥት የአማራ ክልል ልዩ ኃይልና ሌሎች ታጣቂዎችን ትጥቅ አስፈታለሁ በሚል በይፋ ወደ ክልሉ ሠራዊት ካስገባ አንድ ዓመት ሊደፍን ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ በክልሉ የኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጠ ሲሆን በተለያዩ አካባቢዎችና ጊዜያት በመንግሥትና በታጣቂ ኃይሎች በሰላማዊው ሕዝብ ላይ ተፈጽመዋል የተባሉ ጥቃቶችና ግድያዎች እንዲሁም የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ አካል እንዲመረመሩ ከሀገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ የመብት ተቆርቋሪዎች በተደጋጋሚ ጥሪዎች ቀርበዋል።

በሰሞኑ የሰላም ጉባኤ ላይ ምንም እንኳን ባለሥልጣናቱ የክልሉን ጸጥታ ለማረጋጋት የድርድርን አስፈላጊነት ቢያነሱም እንዴት ተግባራዊ ይሆናል የሚለውን ግን አላመላከቱም። በተጠቀሰው ጉባኤ ላይም በነፍጥ የሚፋለሙትን አካላት ወደዚህ መንገድ ለመግባት ያስገደደው መሠረታዊ ጥያቄ አለመነሳቱን በማመላከትም የተባለው የድርድር ሃሳብ ተጨባጭነቱን የሚያሳዩ ምልክቶች አለመታየታቸውን የሚያነሱ በርካቶች ናቸው። በኔዘርላንድ ነዋሪ የሆኑት የፖለቲካ ተንታኝ መስፍን አማን የአማራ ክልል ባለሥልጣናት ስለድርድር የተናገሩትን ከምር ለመውሰድ የከበዳቸው ይመስላል።

«ከባለሥልጣናቱ የቀረበው ከልብ የመነጨ ነው ለማለት ያስቸግራል» ያሉት የፖለቲካ ተንታኙ፤ በማሳያነትም በሰላም ጉባኤው መድረክ የተነሳው የችግሩ መንስኤ የፋኖ ታጣቂዎችን «ትክክለኛ ጥያቄ» አልተነሳም በማለትም ያስረዳሉ።

የአማራ ክልል ፕሬዝደንት አቶ አረጋ ከበደ ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የድርድርና የመፍትሄ አማራጭ

በአማራ ክልል ያለውን ያለመረጋጋት ሁኔታ ያስከተለው ችግር ተወሳስቦ ሰፍቷል የሚሉት የፖለቲካ ተንታኙ፣ በባለሥልጣናቱ እንደታሰበው በሀገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች ይፈታል የሚል እምነት የላቸውም። ከምንም በላይ ከመንግሥት ጋር በጠመንጃ እየተፋለሙ የሚገኙት የፋኖ ኃይሎችን ወደዚህ እርምጃ ያስገቡ ተግባራት አሁንም መቀጠላቸውን በማመልከተም፤ የተነሳው የድርድር ሃሳብ የምር ከሆነ ሊደረግ ይገባል ያሉትን እንዲህ ይገልጻሉ።

«መንግሥት ከልቡ ከፈለገ ሦስተኛ ወገንም በሌላም ዓይነት አደራዳሪ ,,, ብሎ ፤ ቁጭ ብሎ ፋኖ ያነሳቸውን ጥያቄዎች፤ ፋኖ እንግዲህ ያነሳቸው ጥያቄዎች አብዛኛዎቹ ሰው ስለሚስማማበት ነው ከሕዝቡ ድጋፍ አግኝቶ እስካሁን የቀጠለው። ስለሰላም እና ስለእርቅ እየተወራ ባለበት ኦሮሚያ ክልል በተለይ ምዕራብ ሸዋ አመያ አካባቢ፣ ምሥራቅ ሸዋ፤ ወለጋ አካባቢ አሁን አማራዎች እየተፈናቀሉ ነው። ያ ማለት ፋኖ ዋነኛ የተነሳለት አላማ ምን ዓይነት ሳይን የለም ተስፋ ሰጪ ነገር ቢኖር ኦኬ።»

የኢትዮጵያ ችግር በጣም መወሳሰቡን ያመለከቱት የፖለቲካ ተንታኙ በመፍትሄነትም የተለያዩ ኃይላት ጋር በተናጠል ከሚደረግ ድርድር ይልቅ እውነተኛ የሆነ አጠቃላይ ሀገራዊ ውይይት መደረግ እንደሚኖርበትም አመላክተዋል። 

በአማራ ክልል በተካሄደው የሰላም ጉባኤ ማጠቃለያ የወጣው 10 ነጥብ ያሉት የአቋም መግለጫ ጠብመንጃ ላነሱት ኃይሎች የሰላም ጥሪ ከማስተላለፉ በተጨማሪ ከክልሉ ወቅታዊ ጉዳይ በተገናኘ የታሠሩ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና ምሁራን በይቅርታና በምህረት እንዲፈቱም ጠይቋል። ምንም እንኳን ባለሥልጣናቱ የድርድር ሃሳቦችን ቢያነሱም በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ግን አሁንም የመንግሥት ኃይሎች ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር የሚያደርጉት ውጊያ መቀጠሉ ይነገራል።

ሸዋዬ ለገሠ 

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW