የአማራ ክልል ተፈናቃዮች አቤቱታ
ሰኞ፣ የካቲት 20 2015በአማራ ክልል የተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች የሚኖሩ ተፈናቃዮች ለከፍተኛ የምግብ እጦት መጋለጣቸውን ተናገሩ። አንዳንዶቹ መጠለያ በማጣታቸው ለቀናት ሜዳ ላይ ለብርድና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች እየተጋለጡ እንደሆኑ አመልክተዋል። በየደረጃው የሚገኙ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኃላፊዎች “የሚመጣው የእርዳታ እህል በቂ አይደለም በወቅቱም ለተፈናቃዮች አይደርስም” ብለዋል።
ካለፉት 4 ዓመታት ጀምሮ ከማንነት ጋር በተያያዘ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች በተነሱ ግጭቶች የአማራ ማንነት ያላቸው በርካታ ወገኖች ህይወታቸው አልፏል፣ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ ሌሎች ደግሞ ቀያቸውን ለቅቀው ተፈናቅለዋል፡፡
በሰሜኑ ጦርነት ምክንያትም ቀያቸውን ለቅቀው በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ ከተማና አካባቢው ተጠልለው የሚገኙትም ብዙዎች ናቸው፡፡
የሰሜኑን ጦርነት ሸሽተው ከነበሩበት የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ፃግብጂ ወረዳ ወደ ሰቆጣ የመጡ አንድ ተፈናቃይ እርዳታ በተገቢው መንገድ እያገኙ እንዳልሆነ ገልጠዋል፡፡
“አምና ጥር 2 ነው የመጣሁት፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ነገ ዛሬ እንመለሳለን እያልን ምንም መፍትሔ ሳናገኝ አለን፣ መጀመሪያ የመጡት ግማሾቹ ፍራሽ ነገር ያገኙ አሉ፣ አሁን ግን ምንም ነገር የለም፣ ከሚያዝያ ጀምሮ ግብዓትም እየመጣ አይደለም፣ ይመጣል ጠብቁ ብቻ ነው፡፡”
ከወለጋ ተፈናቅለው በሰሜን ወሎ ዞን ጃራ የመጠለያ ጣቢያ ከደረሱት መካከል አንዱ ለዶይቼ ቬሌ እንደተናገሩት አልፎ አልፎ ከሚሰጣቸው ደረቅ ብስኩት ውጪ ምንም እርዳታ አላገኙም፡፡
“በምግብ በኩል አንድ ነገር የለም፣ ከደረቅ ብስኩት በቀር ሙሉ እርዳታ የለም፣ ህዝቡ በጣም በችግር ላይ ተጨናንቆ ነው ያለው፣ ምንም ነገር የለም ከአሁን በኋላ ምናልባት ከተላከ እንጠብቃለን እስካሁን ግን የለም፡፡”
ሌላው ከወለጋ ሰሞኑን ተፈናቅለው ደብረብርሀን ከደረሱት መካከል እንዳስረዱት ደግሞ እጅግ ብርዳማ በሆነው ደብረብርሀን ሜዳ ላይ ያለ ምግብና መጠለያ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
“ያለነው ያው ሜዳ ላይ ነው፣ የምንተኛውም ያው ከዋልንበት ላይ ነው፣ እኔ ምንም የያዝኩት ልብስ የለም፣ አንዲት የብርድ ልብስ ለ5 ቤተሰብ ነው የምንጠቀም፣ ከእኔ የባሱ ደግሞ ምንም የማይበሉ የማይጠጡ አሉ፣ እርዳታ ምንም አልገባም፣ ተፈናቃዩ ህይወቱን እየመራ ያለው በደብረብርሀን ህዝብና በከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ ብቻ ነው፣ አራሶች አሉ፣ ነብሰ ጡሮች አሉ፣ በሽተኞች፣ አዛውንቶች በብርድ ተኮርትመው የተቀመጡ አሉ፣ መጠለያ አለመኖሩ አሳዛኝ ነገር ነው፡፡”
በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰከላ አካባቢ የሚገኙ ተፈናቃዮች አብዛኛዎች በቀን ስራ መሰማራታቸውን አብራርተዋል፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪው፣ በአብዛኛው ወንዶች ያገኙትን ስራ ሁሉ ይሰራሉ፣ ሴቶች ግን በጣም ተቸግረው እንዳሉ ነው ያብራሩት፡፡
የሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዓለሙ ይመርና የምዕራብ ጎጃም ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተዋቸው ዓለማየሁ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የአቅርቦት እጥረትና የእርዳታ መዘግየት ችግሮች አሉ ብለዋል፤ ሆኖም የተገኘውን በማብቃቃት ተፈናቃዮች ህይወታቸው የከፋ እንዳይሆን እየተሰራ እንደሆነ አስረድተዋል፣ ሆኖም ግን ዘላቂ መፍትሔ ካልተበጀ ከፍተኛ ስጋት መኖሩንም ጠቁመዋል፡፡
የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ እህታገኝ አደመ በበኩላቸው እርዳታ በረጂ ድርጅቶችና በመንግስት እየቀረበ መሆኑን አስታውሰው፣ ሆኖም እጥረት በመኖሩ በተሟላ መልኩ እየቀረበ ነው ለማለት እንደማያስደፍር ገልጠዋል፡፡
“እጥረት አለ እጥረት የለም አንልም፣ እጥረቶች አሉ፣ ነገር ግን በአሰራሩ መሰረት ደግሞ በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ የሚያቀርቡ ረጂ ድርጅቶች አሉ፣ በስድስት ሳምንት አንዴ እያቀረቡ ነው ያለው፣ እሱም ሆኖ ተፈናቅለው በመጡ ዜጎች ላይ አሁንም የቀለብ እጥረት አለ፣ በፌደራል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በኩል የሚቀርብላቸው አካባቢዎች ደግሞ፣ ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ምዕራብ ጎጃም፣ ምስራቅ ጎጃም፣ ማዕከላዊ ጎንደርና ደቡብ ጎንደር ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ እዚህ አካባቢ ያሉት ደግሞ ከሶስት ወር ያላነሰ የመዘግየት ሁኔታ ይታያል፣ ስለሆነም ድጋፉ በተሟላ ሁኔታ ይደርሳል ለማለት ይከብዳል እጥረቱ ስላለ፡፡” ብለዋል፡፡
የእርዳታ መዘግየትን በተመለከተ ለፌደራሉ መንግስት አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ብንደውልም ያሉበት ቦታ መረጃ ለመስጠት እንደማያስችል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ነጋሽ መሐመድ