የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የኢድ አል አደሀ መልዕክት
ሰኞ፣ ሐምሌ 12 2013
ማስታወቂያ
የዘንድሮውን የኢድ አል አደሀ በዓል ምክንያት በማድረግ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡ የምክር ቤቱ ፕረዚደንት ሸክ ሰኢድ መሐመድ ዛሬ በጽ/ቤታቸው ግቢ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በዓሉ የሰላምና የፍቅር፣ የመረዳዳት እንዲሆንም ተመኝተዋል፡፡
በአማራ ክልልና በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በነበሩ ግጭቶች የተፈናቀሉ በርካታ ዜጎች መኖራቸውን አስታውሰው፣ በዓሉን ስናከብር እነኝህን ወገኖች መርዳት ያስፈልጋል፣ በፈጣሪ ዘንድም ዋጋ አለው ብለዋል፡፡
ብዙ ተግዳሮቶች ያሉበት ወቅት ቢሆንም የዚህን ዓመት ኢድ አል አደሀ ልዩ ያደርገዋል ያሉትን ሁኔታም ጠቁመዋል፡፡
ያጋጠሙንን ችግሮች ለመፍታት በሁሉም መስክ ትብብራችንን ማድረግ፣ በተለይ ደግሞ ወደ ፈጣሪ ፊታችን በማዞር መፀለይና መለመን አማራጭ የሌለው ጉዳይ እንደሆነ ሸክ ሰኢድ አመልክተዋል፡፡
በእለቱ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አባላትና ሰራተኞች በምክር ቤቱ ግቢ የችግኝ ተከላ ስነስርዓት አካሂደዋል፣ እንደዚሁም መስማት ለተሳናቸው ወገኖች የዘይትና የዱቄት እርዳታ ተደርጓል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ኂሩት መለሰ