1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ ክልል ከተሞች ሰላማዊ ውሎ፣ የአውሮጳ ኅብረት የአሜሪካና አጋሮቿ መግለጫ

ዓርብ፣ ነሐሴ 5 2015

ሸዋሮቢት፣ ላሊበላ እና ጎንደር መነቃቃት መጀመራቸውን የከተሞቹ ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። አንድ የላሊበላ ነዋሪ "ከወሰን፣ ከማንነት እና ከፍትኃዊ ተጠቃሚነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን መንግሥት በተገቢው ሁኔታ አይቶ ምላሽ" መስጠት እንዳለበት ገልጸዋል። በነበረው ግጭት በሕይወት እና በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት ወደፊት ይገለጻል ተብሏል

የላሊበላ ከተማ
የላሊበላ እንቅስቃሴ ወደነበረበት የመመለስ አዝማሚያ ማሳየቱን የተናገሩ የከተማዋ ነዋሪ ባንኮች መከፈታቸውን የመንግሥት ተቋማት ከሞላ ጎደል አገልግሎት መጀመራቸውን አስረድተዋል።ምስል Sergi Reboredo/picture alliance

ሰሞኑን ብርቱ ውጊያ ሲደረግባቸው የነበሩት የአማራ ክልል ዋና ዋና ከተሞች በተለይ ከትናንት ጀምሮ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እየተመለሱ መሆኑን ነዋሪዎች ተናገሩ። በባህር ዳር ፣ በጎንደር፣ በላሊበላ እና በሸዋሮቢት ከተሞች ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ሰዎች ወደ አብያተ ክርስትያናት ሲጓዙ መመልከታቸውን፣ ውስን ቢሆንም የትራንስፓርት እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን፣ የባንክ እና የህክምና ተቋማት እየተከፈቱ መመመልከታቸውን በየፊናቸው ገልፀዋል። በሌላ በኩል የአውሮጳ ሕብረት ልዑክ በኢትዮጵያ እና ጀርመንን ጨምሮ በኢትዮጵያ የሀያ የአውሮጳ ሀገራት ኤምባሲዎች በጋራ እንዲሁም ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ ሌሎች አምስት ሀገሮች በጋራ ባወጧቸው ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው መግለጫዎች "ሰሞኑን በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ሁከት እና የዜጎች ሞት እና አለመረጋጋት" እንዳሳሰባቸው ገልፀዋል። 

እስራኤል ከ200 በላይ የሚሆኑ ዜጎቿን ከአማራ ክልል አወጣች

ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የሸዋሮቢት ነዋሪ አርብ የከተማዋ እንቅስቃሴ መነቃቃት መጀመሩን ገልጸዋል። ጤና ጣቢያዎች እና መድሐኒት ቤቶች ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነ የሸዋሮቢት ከተማ ነዋሪ ገልጸዋል። ምስል Eshete Bekele/DW

አንድ ስሙን እንዳንጠቅስ፣ ድምፁንም አየር ላይ እንዳናውል የጠየቀ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ ከተማዋ ከትናንት ጀምሮ  ሰላማዊ መሆኗን እና የተኩስ ድምፅ እንደማይሰማባት ገልፀዋል። አክለውም የትራንስፖርት አገልግሎት አለመጀመሩን፣ ዋና ዋና መስመሮች መከፈታቸውን፣ ሆኖም ውስጥ ለውስጥ ያሉ መንገዶች ሙሉ በሙሉ ክፍት አለመሆናቸውን እንዳዩ ጠቅሰዋል።በመክላከያ ሠራዊት እና በፋኖ መካከል ከተማቸው ብርቱ ውጊያ ሲደረግባት እንደነበር የገለፀ አንድ የሸዋ ሮቢት ከተማ ነዋሪ ከተማዋ አሁን ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መግባቷን  ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል። "መንግሥት ሕዝብ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች በወቅቱ ምላሽ አለመስጠቱ ግጭቶች እንዲበራከቱ እያደረገ" መሆኑን የተናገሩ የላሊበላ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው በከተማው ሰዎች ወደየ አብያተ ክርስትያናት ነጠላ ለብሰው መንቀሳቀስ መጀመራቸውን እንደተመለከቱ እና የትራንስፖርት እንቅስቃሴም መጀመሩን ገልፀዋል።

የአማራ ክልል ከተሞች የሰዓት ዕላፊ ገደብና የዕለቱ እንቅስቃሴ

የጎንደር ከተማ ነዋሪው አስተያየት ሰጪም ተመሳሳይ የሰላም ሁኔታ እየተስተዋሉ መሆኑን ገልፀዋል።የአውሮጳ ኅብረት ልዑክ በኢትዮጵያ እና ጀርመንን ጨምሮ በኢትዮጵያ የሃያ የአውሮፓ ሀገራት ኤምባሲዎች በጋራ እንዲሁም ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ ሌሎች አምስት ሀገሮች ለብቻ ባወጡት ተመሳሳይ መግለጫ "ሰሞኑን በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ሁከት እና የዜጎች ሞት እና አለመረጋጋት" እንዳሳሰባቸው ገልፀዋል።

አንድ የጎንደር ነዋሪ በተማው ተኩስ መቆሙን ተናግረዋል። ይሁንና ባንክን ጨምሮ ተቋማት በይፋ በአግባቡ አገልግሎት መስጠት እንዳልጀመሩ ገልጸዋል። ምስል Alemnew Mekonnen/DW

"ሁሉም ወገኖች ሲቪሎችን እንዲጠብቁ ፣ ጉዳት ለደረሰባቸው ሕዝቦች የተሟላ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ቀጣይነት ያለው ሰብዓዊ ተደራሽነት እንዲረጋገጥ" ሲል በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ባወጣው መግለጫ የጠየቀው የአውሮፓ ሕብረት ልፁክ በኢትዮጵያ "የውጪ ዜጎች ከግጭቱ አካባቢ ለቀው እንዲወጡ እና ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ እንዲተላለፉ እንዲፈቀድ እና ግጭቱ ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክልሎች ተዛምቶ ብጥብጥ እንዳይፈጠር ተገቢው መከላከል እንዲደረግ እናበረታታለን" ብሏል።በተመሳሳይ ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ እንግሊዝ፣ ኦስትሪያ፣ ጃፖን እና ኒውዝላንድ ዛሬ በጽሑፍ ባወጡት የጋራ መግለጫ "ለዜጎች ሞት እና አለመረጋጋት ምክንያት የሆነው" ያሉት እና በቅርቡ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የተከሰተው ሁከት እንዳሳሰባቸው ገልፀዋል። ሁሉም አካላት ንፁሃንን እንዲጠብቁ ፣የሰብዓዊ መብትን እንዲያከብሩ፣ ውስብስብ ገዳዮችን በሰላማዊ ሁኔታ ለመፍታት በጋራ እንዲሰሩም እናበረታታለን ሲሉ ገልፀዋል።

 የአማራ ክልል ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታና ኮማንድ ፖስት

የአውሮፓ ሕብረት ልዑክ በኢትዮጵያ እና ሌሎች አምስቱ ሀገራት በተናጠል ባወጧቸው መግለጫዎች "አለም አቀፉ ማህበረሰብ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የረዥም ጊዜ መረጋጋት ግብ ድጋፉን ይቀጥላል" በማለት ቃል ገብተዋል።ከመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት እና ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፓስት ዕዝ ሁለት ባለስልጣናት ዛሬ በሰጡት  መግለጫ የጸጥታ ችግር በተከሰተባቸው የአማራ ከልል ስድስት ከተሞች ላይ በተወሰደው እርምጃ ከተሞቹ ወደ ሰላምና መረጋጋት ተመልሰዋል ተብሏል።

ሰሎሞን ሙጬ


ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW