1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ ክልል ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታና ኮማንድ ፖስት

ሰኞ፣ ነሐሴ 1 2015

በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተደነገገ በኋላ በጎንደር እና ባሕርዳር ከተሞች ዛሬም በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ መካከል ውጊያ እና የተኩስ ድምፅ መኖሩን ነዋሪዎች ገለፁ። በእነዚህ ከተሞች ልዩ ልዩ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት በተለይ የመጓጓዣ አገልግሎት፣ የጤና ተቋሟት እና ሌሎችም ዝግ መሆናቸውን ነዋሪዎቹ አመልክተዋል።

Äthiopien Stadt Gonder
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የአማራ ክልል ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ እና ኮማንድ ፖስት

This browser does not support the audio element.

በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተደነገገ በኋላ በጎንደር እና ባሕርዳር ከተሞች ዛሬም በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ መካከል ውጊያ እና የተኩስ ድምፅ መኖሩን ነዋሪዎች ገለፁ። በእነዚህ ከተሞች ልዩ ልዩ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት በተለይ የመጓጓዣ አገልግሎት፣ የጤና ተቋሟት እና ሌሎችም ዝግ መሆናቸውን ነዋሪዎቹ አመልክተዋል። ትናንት ውይይት ማድረጉን ያስታወቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ አራት ኮማንድ ፖስት እና መምሪያዎችን ማደራጀቱን ገልጿል። የዕዘ ዋና ሰብሳቢ እና የብሔራዊ መረጃ እና ዳህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የተደራጁ ዘራፊ ቡድኖች ያሏቸው አካላት በኃይል የክልሉን መንግሥት የማፍረስ እንዲሁም ወደ ፌዴራል ሥርዓቱ የመሄድ ፍላጎት፣ አዝማሚያ እና ግብ ይዞ የሚሄድ ያሉት ይህ አካል በክልሉ ያለውም ችግር መፍጠሩን ተናግረዋል። አክለውም እነዚሁ አካላት በክልሉ «አንዳንድ የዞን ከተሞችን እና የወረዳ ከተሞችን በመቆጣጠር የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋማትን እና ማረሚያ ቤቶችን በመፍታት ወንጀለኞችን እስከመልቀቅ የደረሱባቸው ወረዳዎች አሉ» ብለዋል።

በአማራ ክልል የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ በክልሉ አራት ኮማንድ ፖስት እና መምሪያዎችን ማደራጀቱን ትናንት አስታውቋል። ይህንን ተከትሎ የክልሉ ዋና ዋና ከተሞች ውሎ ምን ይመስላል የሚለውን ጠይቀናል። በጎንደር ከተማ ከትናንት ምሽት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ብርቱ ውጊያ እና የተኩስ ልውውጥ በመከላከያ ሠራዊት እና መንግሥት ዘራፊ ቡድን ብሎ በሚጠራቸው የፋኖ አባላት መካከል መደረጉን አንድ የከተማዋ ነዋሪ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል። ነዋሪው እንደሚሉት አሁን እየተስተዋለ ያለው ውጊያ እና የፀጥታ ችግር ከ ሰባት ዓመታት በፊት በ2008 እና 2009 ዓ. ም ተከስቶ ከነበረው ሁኔታ የከፋ እና የሚያይል ነው።  ደሴ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ እና የመንግሥት ሠራተኛ መሆናቸውን የገለፁ አንድ አስተያየት ሰጪ እንደሚሉት ደግሞ ከከተማ ከተማ የእንቅስቃሴ ፍሰት ባይኖርም ከተማው ሰላማዊ ነው። ግለሰቡ ዛሬ ለስብሰባ ተቀምጠው እንደነበርም ገልፀዋል።

ላሊበላ ምስል Annabelle Steffes-Halmer/DW

የላሊበላ ከተማ ነዋሪ የሆኑ ሌላ ግለሰብም ተመሳሳይ አስተያየት የሰጡ ሲሆን ፣ ከተማዋ በማን ቁጥጥር ሥር እንደሆነች ለመግለጽ እንደማይፈልጉ ተናግረዋል። የአማራ ክልል ርእሠ ከተማ ባሕር ዳር መደበኛ እንቅስቃሴ መታጎሉን የገለፁ ነዋሪ በከተማዋ ውስጥ ተኩስ እንደሚሰማ እና ከባድ የጦር መሣሪያዎች በመሀል ከተማ ሲንቀሳቀስ መመልከታቸውን ገልፀዋል። በአማራ ክልል የተከሰተውን ችግር ለመቀልበስ የተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያቋቋመው ኮማንድ ፖስት ትናንት ውይይት ማድረጉን የገለፁት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ዋና ሰብሳቢ እና የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የክልሉ ህዝብ የሚጠይቃቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች መኖራቸውን ገልፀው «ብልጽግና ለመፍታት እየተንቀሳቀሰ ባለበት ሁኔታ በኃይል ጥያቄዎችን አስመልሳለሁ በሚል» «የተደራጁ ዘራፊ ቡድኖች» ባሏቸው አካላት ሕዝብን ለእንግልት የዳረገ የፀጥታ ችግር መከሰቱን ተናግረዋል። በእነዚህ አካላት በአንዳንድ አካባቢዎች ፍርድ ቤቶች እና የፍትሕ ተቋማት እንዲወድሙ እየተደረገ መሆኑንና «በአጭር ጊዜ ውስጥ ክልሉን ወደ ሰላም ለመመለስ» የተዋቀረው ኮማንድ ፖስት እንደሚሠራ ገልፀዋል። ይህንን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገግ ተከትሎ በአዲስ አባባ እና ዙሪያዋ በርካታ ሰዎች እየታሰሩ መሆኑን ወላጆችና ቤተሰቦቻቸው የገለጹ ሲሆን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሉት ሚኒስትር በበኩላቸው «በአማራ ክልል ካለው ወቅታዊ ጉዳይ ጋር ግንኙነት ያላቸው፣ የሚያባብሱ እና ሥምሪት የሚሰጡ» የተባሉ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋል ስለመጀመሩ ተናግረዋል።ጉዳዩን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ያወጣው የአዲስ አበባ ከተማ «የዚህ የጥፋት ኃይል ከአማራ ክልል ቀጥሎ አዲስ አበባን የሽብር እና የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ በተለያየ መንገድ እየሞከረ እንደሚገኝ ተደርሶበታል» ሲል አስታውቋል። በሌላ በኩል ኢትዮጵያዊው የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት ምክንያት መንገዶች መዘጋታቸው ፣ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ መደረጉ የሰብዓዊ እርዳታን ማድረስ አስቸጋሪ እንደሚያደርገው እና ሁኔታው ድርጅታቸውን እንዳሳሰበው በትዊተር መገናኛ ገልፀዋል።

አቶ ተመስገን ጥሩነህምስል DW/A. Mekonnen

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW