የአማራ ክልል ዘንድሮ ለመማር የተመዘገቡት ተማሪዎች ቁጥር ከታቀደዉ ከግማሽ በታች ነዉ
ማክሰኞ፣ መስከረም 6 2018
የአማራ ክልል ትምሕርት ቢሮ በዘንድሮዉ የትምሕርት ዘመን ከ7.4 ሚሊዮንበላይ ተማሪዎችን ለማስተማር ማቀዱን አስታወቀ።ቢሮዉ እንደሚለዉ ዘንድሮ ሊያስተምር ያቀደዉ ባለፉት ሁለት ዓመታት ትምሕርት ያቋረጡን ጨምሮ ነዉ። የዓመቱ ትምህርት ትናንት በክልሉ ሲጀመር እንደተገለጠው ግን ለመማር የተመዘገቡት ተማሪዎች ቁጥር 3 ሚሊዮን አይሞላም። ምዝገባ ያልጀመሩ ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ ወላጆችና መምህራን ተናግረዋል።
በክልሉ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ትምህርት አቋርጠዋል፡፡በአማራ ክልል ያለው የሠላም መደፍረስ የክልሉን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ሰብአዊ ሁኔታዎችን በእጅጉ አዛብቷል፡፡ በተለይ በትምህርቱ ዘርፍ ያስከተለው ቀውስ ከፍ ያለ ነው፡፡ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሙሉነሽ ደሴ በቅርቡ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ ሆነዋል፡፡
በክልሉ ያለው ጦርነት የትምህርቱ ዘርፍ እየፈተነው ስለመሆኑ
ዶ/ር ሙሉነሽ፣ “በ2016 ዓ ም ካቀድነው 6.2 ሚሊዮን ተማሪ ለማስተማር አቅደን 2.5 ሚሊዮን የሚሆኑት ወደ ትምህርት ቤት አልመጡም፣ በ2017 ዓ ም ከ 7 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ 4 ሚሊዮን የሚሆኑ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት መምጣት አልቻሉም፣ ከተመዘገቡት መካክልም ብዙዎቹ ያቋረጡ ናቸው፡፡” ብለዋል፡፡
በ2018 የትምህርት ዘመንም ባለፉት ዓመታት ከትምህርት ርቀው የነበሩ ተማሪዎችን በማካተት 7 ሚሊዮን 445 ሺህ 545 ተማሪዎችን ለማስተማር መታቀዱን ነው ቢሮ ኃላፊዋ ያመለከቱት፡፡
ትናንት ትምህርት በክልሉ መጀመሩን ለመንግሥት መገናኛ ብዙሐን ዶ/ር ሙሉነሽ በሰጡት መግለጫ ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ 3 ሚሊዮን ያክል ተማሪዎች መመዝገባቸውንና ለምዝገባው ዝቅተኛነት ምክንያት ነው ያሉትን አስቀምጠዋል፡፡
እንደ ኃላፊዋ ዋናዎቹ ምክንያቶች፣ “ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ቀድሞ የመመዝገብ ልምድ የሌላቸው መሆኑና ሌላው ደግሞ የፀጥታ ችግር ያለባቸው ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን መመዝገብ ባለማቻላቸው ነው፡፡” ያሉት፡፡
በክልሉ አንፃራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች ትምህርት ተጀምሯል
“በክልሉ ትምህርት ተጀምሯል” ያሉት ኃላፊዋ፣ በባሕርዳር ከተማ በሚገኙ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች የትምህርት አጀማምሩ ምን እንደሚመስል ትናንት በአካል እንደተመለከቱ ገልጠዋል፡፡ የዶይቼ ቬሌ ሪፖርተር በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች በአካል እንደተመለከተውም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤቶች በመሄድ የክፍል ምደባቸውን ሲመለከቱ ታዝቧል፡፡
መምህራንና ወላጆች በተልይ በከተሞች አካባቢ ትምህርት መጀመሩን ሲገልፁ፣ የፀጥታ ስጋት ያለባቸው የገጠር አካባቢዎች ግን ምዝገባ እንኳን እስካሁን እንደሌለ ነው ለዶይቼ ቬሌ ያስረዱት፡፡
ትምህርት ከተጀመረባቸው አካባቢዎች መካክል በሰቆጣ ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሚጠቀሱ ሲሆን የዋግሥዩም አድማስ ወሰን 2ኛ ደርጃ ትምህርት መምህር መንግሥቱ አረጋ ይህንኑ አረጋግጠውልናል፡፡
መምህር መንግሥቱ፣ ተማሪዎች በፈረቃ ትምህርት ጀምረዋል፣ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱ ባሻገር የመድኃኔ ዓለም፣ ሌተናንት ጀነራል ኃይሉ ከበደ፣ ኮሎኔል አማረ ሞላ እና ሌሎችም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሥራቸውን መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ እርሳቸውም ክፍል ገብተው የእለቱን ትምህርት ለተማሪዎቻቸው ማስተማራቸውን ገልጠዋል፡፡
በሰሜን ሽዋ ዞን የምንዝ ላሎ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሪዎች ምዝገባ ቢካሄድም ትምህርት ቤቱ ለማስተማር የማያስችሉ ቅሪ አንዳንድ ጉዳዮች ቢኖሩም ያሉ ጉዳዮች እልባት እንዲያገኙ ምክክር መደረጉን ጠቁመው በቅርቡ ትምህርት በትምህርት ቤቱ እንደሚጀመር አንድ የትምህርት ቤቱ መምህር በስልክ ነግረውናል፡፡
በሰሜን ጎጃም ዞን የጎንጂ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና በምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረወርቅ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራን በበኩላቸው በከተሞች ትምህርት መጀመሩን ነው ያረጋገጡልን ሲሆን በገጠር አካባቢ ግን የመማር ማስተማሩም ሆነ ምዝገባ ገና እንደሆነ ነው ያስረዱን፡፡፡
“ምዝገባ ያልጀመሩ ትምህርት ቤቶች አሉ” ወላጆችና መምህራን
ከደቡብ አቸፈር ገጠራማ አካባቢ ወደ ዱርቤቴ ከተማ ልጆቻቸውን በማምጣት ማስመዝገባቸውንና የገለፁልን አንድ የወረዳው ነዋሪ፣ በገጠሩ አካባቢ ግን መምህራንም ወደ ትምህርት ቤት መሄድ አልቻሉም ተማሪዎችም አልተመዘገቡም ነው ያሉት፡፡
በምዕራብ ጎጃም ዞን ማቻከል፣ በምስራቅ ጎጃም ዞን የጁቤና በሰሜን ጎጃም ዞን የይልማና ዴንሳ ወረዳዎች የገጠር ትምህርት ቤቶች እስካሁን ምዝገባ እንዳልጀመሩና ልጆቻቸው ሌላ ሦስተኛ ዓምትን ያለትምህርት ሊቀጥሉ እንደሆነ ወላጆች አመልክተዋል፡፡
በአማራ ክልል ከ10ሺህ በላይ የቅድመ አንደኛ፣ የመለስተኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ፣ በክልሉ በሚካሄደው ጦርነት ደግሞ ከ3ሺህ 700 በላይ ትምህርት ቤቶች ከሥራ ውጪ መሆናቸው ቀደም ሲል መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ነጋሽ መሐመድ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር