1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል ከአሜሪካ አምባሳደር ጋር ተወያየ

ሰለሞን ሙጬ
ሐሙስ፣ ነሐሴ 30 2016

በፌዴራል መንግሥት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የቀጠለው የትጥቅ ግጭት በድርድር እንዲፈታ የማግባባት ሥራ ለማከናወን የ«አመቻችነት» ሚና ይዞ ከሁለት ወራት በፊት ተቋቋመ የተባለው «የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል» ትናንት በኢትዮጵያ ከአሜሪካ አምባሳደር ጋር ተወያይቷል ።

US Ambassador Ervin Massinga and USAID   Assistance Sonali Korde
ምስል Seyoum Getu/DW

«የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል» ትናንት በኢትዮጵያ ከአሜሪካ አምባሳደር ጋር ተወያይቷል

This browser does not support the audio element.

በፌዴራል  መንግሥት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የቀጠለው የትጥቅ ግጭት በድርድር እንዲፈታ  የማግባባት ሥራ ለማከናወን የ«አመቻችነት» ሚና ይዞ ከሁለት ወራት በፊት ተቋቋመ የተባለው «የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል» ትናንት በኢትዮጵያ ከአሜሪካ አምባሳደር ጋር ተወያይቷል ። ካውንስሉ ከአምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በተጨማሪ ከምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) የደኅንነት ጉዳይ ኃላፊ ጋርም ስለመወያየቱ ለዶቼ ቬለ አረጋግጧል ። ምክር ቤቱ የውይይቱን ዝርዝር ጉዳዮች ከመግለጽ የተቆጠበ ቢሆንም፣ እስካሁን ስላከናወናቸው ሥራዎች፣ ስለገጠሙት ችግሮች እና ለውጥኑ መሳካት ከዲፕሎማሲ ማሕበረሰቡ ሊደረግለት ስለሚፈልጋቸው ድጋፎች ጭምር መነጋገሩን ጠቅሷል ። ሰለሞን ሙጬ ከአዲስ አበባ ዝርዝር ዘገባ ልኮልናል ።

ለድጋፍ ፍለጋ የተደረገው ውይይት

የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እንዲፈርስ መደረጉን ተከትሎ በፌዴራል መንግሥት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል  ከአንድ ዓመት በላይ የቀጠለውን የትጥቅ ግጭት በድርድር ለመፍታት የ "አመቻችነት" ኃላፊነት ይዞ "ድንገት" ስለመቋቋሙ የሚነገርለት የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል ትናንት በአሜሪካ ኤምባሲ ውስጥ ስድስት አባላቱ ከአምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ እና ስድስት የዲፕሎማሲ አባሎቻቸው ጋር መነጋገሩን የካውንስሉ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያቸው ተሻለ አረጋግጠዋል።

ከተቋቋመ ከሁለት ወራት በላይ ያስቆጠረው ምክር ቤቱ በቀጣይ ከአፍሪካ ሕብረት ጋርም ለመነጋገር ጥያቄ ማቅረቡን አስታውቋል። ምክር ቤቱ ይህንን ውይይት የሚያደርገው ቆምኩለት ላለው ጥረት መሳካት የሚረዳውን ድጋፍን ፍለጋ እንደሆነ አስታውቋል።

ድርድር ለመጀመር የሚያስችል ተጨባጭ ውጤት እስካሁን ማምጣት ያልቻለው ይህ 15 አባላት ያሉት አካል የትጥቅ ግጭት ውስጥ ባሉት ኃይላት መካከል አለመተማመን መኖሩን፣ የፋኖ ታጣቂዎች  አንድ ወጥ አደረጃጀት ያለው አለመሆኑ እና የሚቀርብበት የገለልተኝነት ጥያቄ የገጠሙት ችግሮች መሆናቸውን ገልጿል።

ግጭቱም ከአንድ ዓመት በላይ ተሻግሮ በክልሉ ላይ ዘርፈ ብዙ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውሶችን ማድረሱን ስለመቀጠሉ ተደጋግሞ ተገልጿል።

የፋኖ ታጣቂ ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Solan Kolli/AFP/Getty Images

ሁለቱን አካላት ወደ ሰ ላም ለመምጣትና ለድርድር ለማብቃት የሚቸግራቸው ጉዳይ ይኖር ይሆን? የሚለውን የፖለቲካ ተንታኞችን ሐሳብ ለማካተት ጥረት ብናደርም ፈቃዳቸውን የነፈጉን ጥቂት አይደሉም።

ይሄው ካውንስል አምባሳደር ማሲንጋ ጋር ከመገናኘታቸው አስቀድሞ ከአማራ ክልል ርእሠ መስተዳድር፣ ቀጥሎም ከሰላም ሚኒስትሩ ጋር መወያየቱን አስታውቋል። በቀጣይም ለማግኘት ጥያቄ ያቀረበላቸው የፌዴራል የመንግሥት ባለስልጣናት እንዲሁም አሕጉራዊ እና አለም አቀፍ ተቋማት መኖራቸውን ገልጿል።

ወደ  ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የሚጓዙትና በሰላም ጥረት ላይ ምክክር የሚያደርጉት የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር ሰሞኑን ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ሲሆን ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ይወያዩባቸዋል ከተባሉ ነጥቦች መካከል በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የቀጠለውን የፀጥታ ችግር ማስቆም የሚሉት ይገኙበታል ተብሏል።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW