1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትኢትዮጵያ

እቤት መቀመጥ የሰለቻቸው የአማራ ክልል የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ብሶት እና ጥያቄ

ልደት አበበ
ዓርብ፣ ኅዳር 7 2016

በተለያዩ የአማራ ክልል ዩኒቨርስቲዎች ተመድበው ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች እስካሁን ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለስ አለመቻላቸውን ለዶይቸ ቬለ ድምፅ ሁኑን ሲሉ ሰሞኑን ቅሬታቸውን ገልፀዋል። ተማሪዎቹ ዩኒቨርስቲዎቹ ሳይጠሯቸው እቤት ከተቀመጡ በርካታ ወራት እየተቆጠረ መሆኑ ስጋት ላይ ጥሏቸዋል። ከሚመለከተው አካልም እስካሁን ምላሽ ማግኘት አልቻሉም።

የባህር ዳር ዩንቨርስቲ
የባህር ዳር ዩንቨርስቲምስል A. Mekonnen/DW

የአማራ ክልል የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ብሶት እና ጥያቄ

This browser does not support the audio element.

በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ትምህርት መማር እየፈለጉ መማር ያልቻሉ ወጣቶች በርካታ ናቸው።  እቤት መቀመጡ መሯቸዋል። ይህም ይማሩበት የነበሩ እና አማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት እንዲጀምሩ እስካሁን መልሰው ስላልጠራቸው ነው። ያነጋገርናቸው ሁሉም የአማራ ክልል ተማሪዎች ስማቸው ባይገለፅ ይመርጣሉ።  የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ የሶስተኛ ዓመት ተማሪ እንደሆነች የገለፀችልን ወጣት የሶስተኛ ዓመት ተማሪ ናት ፣ ወይም ነበረች ማለት ይቻላል። « ከግቢው ከወጣን ሀምሌ ወር አንስቶ እስካሁን አልተመለስንም» ትላለች። « ኮሮና ስለነበር ክረምት ነው የተማርነው። የትምህርት አሰጣጡ ስለተዛባ የመጀመሪያው ሴሚስተርን ተምረን ነው የወጣነው» ከዚያን ጊዜ አንስቶ ወጣቷ ወደ ወላጆቿ ቤት ተመልሳለች። እዚያም ብዙ ስለ ትምህርት መረጃ እንደማታገኝ ነው የገለፀችልን። « የምኖረው ገጠር ነው ። ዳታ ስለተዘጋ መረጃ ብዙም የለኝም። ከአማራ ክልል ያሉ ጎደኞቼ ጋር እየደወልኩ ነው» የተወሰኑ መረጃዎች የማገኘው ትላለች።

ምስራቅ አርሲ ኦሮሚያ ክልል ነዋሪ የሆነው እና ባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ተመድቦ ይማር እንደነበር የገለፀልን ሌላው ወጣት ቢሳካለት ኖር ዘንድሮ ተመራቂ ነበር። « የማርኬቲንግ ማኔጅመንት ተማሪ ነኝ። ሰኔ መጨረሻ ጨርሰን እንደወጣን አልተመለስንም። በቅርብ ጥሪ እንደሚያደርግ ዩንቨርስቲው አስታውቆ ነበር» ይሁንና ተማሪው በተስፋ ቢጠብቅም እስካሁን ይህ ሳይሆን ቀርቷል። 

እስካሁን ከትምህር ሚኒስቴርም ይሁን ከሌላ የሚመለከተው አካል ምንም አይነት መረጃ እያገኙ እንዳልሆነ የገለፀልን የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ተማሪ ጥያቄ አለው። « ጥያቄያችን ቢያንስ ለተመራቂ ተማሪዎች እንኳን ትምህርት ሚኒስቴር የሚያመቻችልን ነበር ቢኖር ጥሩ ነው።  የመንግሥት ሚዲያዎች አብዛኛውን ጊዜ በክልሉ ያለው ነገር ሰላም ነው ይላሉ። እኛ እዛ ክልል ካሉ ተማሪዎች ጋር በምንደዋወልበት ጊዜ ግን ጦርነት እንዳለ ነው የሚነግሩን። እና በየአካባቢያቸው መከላከያ እና ፋኖ እየተዋኑ እንደሆነ ነው መረጃ የሚነግሩን። » ስለሆነም ከሚመለከተው አካል ምላሽ ይሻል።

ይኽ ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆነችው ወጣትም ጥያቄ ነው። የአራተኛ አመት እና የዘንድሮ ተማራቂ ተማሪ ነበረች። « ትምህርት ያቆምነው እና ከግቢ የወጣነው ሰኔ 24 ቀን ነበር። ሚድ ፈተና ተፈትነን ነበር ።   ያኔ ደግሞ የ 12ኛ ክፍል ፈተና ነበር። እና ለእነሱ ልቀቁ ተብለን ነው የለቀቅነው» ትላለች።

«ዩኒቨርስቲውን ለቀን ከወጣን በኋላ ነው ነገሮች የተባባሰው» የምትለው የደባርቅ ዩኒቨርስቲ የማኔጅመንት ተማሪ ነዋሪነቷ ኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ውስጥ ነው። ወጣቷ የነበራት መረጃ ትማርመት የነበረው ዩንቨርስቲ ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቆ መስከረም ወር ላይ ተማሪዎቹን እንደሚጠራ ነበር።

ደብረ ብርሃን ያለውስ ሁኔታ ምን ይመስላል?

የደብረ ብርሃን ተማሪ እንደሆነ  የገለፀልን ሌላው ተማሪ ደግሞ «ዩኒቨርስቲዎች ተማሪውን ያላገናዘበ ውሳኔ  ወስነዋል » ይላል።  እንደሱ አመለካከት ችግሩ ያለው ዩንቨርስቲዎቹ ጋር ነው። « አማራ ክልል ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት የሚታወቅ ሆኖ በአንፃራዊነት ሰላም የሆነ ነገር ተስተውሏል። ያም ሆኖ ግን ዩንቨርስቲዎች ዋና ስራቸውን ዘንግተው ፒለቲከኛ የሆኑበት ሁኔታ ነው ያለው። » የሚለው የደብረ ብርሃን ተማሪ ከግቢ ከወጣ አራት ወር አልፎታል። ከኮሮና ወረርሽኝ አንስቶ ተማሪው በተለያዩ ምክንያቶች  በተደጋጋሚ እቤት መቀመጡም ትልቅ የስነ ልቦና ጉዳት እያደረሰበት እንደሆነ  ተማሪው ያክላል። « ከቤተሰብ ጋር አለመስማማት ይመጣል። ጭንቀት አለ። ውጥረት ይነግሳል።  አሁን አራተኛ ዓመት መሆን ነበረብን  ግን ሶስተኛ ዓመት ላይ ነን» እያለ ያልተማረባቸውን ጊዜያት ይዘረዝራል። ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ የደብረ ማርቆስ ተማሪዋም ትልቁ ስጋት  ይኼ ነው። በተለይ የመብራት አገልግሎት እንኳን ወዳልተዘረጋበት ገጠር  ቤተሰቦቿ ጋር በመመለሷ ደግሞ ሁኔታውን ይበልጥ አባብሶታል። «   የከተማ ሰዎች እንኳን መብራት ዋይፋይ እንደልብ ያገኛሉ። ገጠር ግን መብራት የለም። ስልካችን ላይ ዳታ ስለተዘጋብን መፅሀፍ እንኳን ዋውረድ አንችልም። እና ተመልሰን ብንገባ ውጤታማ አንሆንም የሚል ስጋት አለኝ» ትላለች። ወላጆቿ አይዞሽ ቢሏትም ትልቅ ብስጭት አላት። ከሁሉም ነገር በላይ ግን መጀመሪያ ሀገር ሰላም እንዲሆን ትመኛለች።

የደብረ ታቦር ዩንቨርስቲምስል Alemnew Mekonnen/DW

ሌላዋ የደባርቅ ዩኒቨርስቲ ተማሪ የሆነችው ወጣት በተለያዩ ምክንያት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዲርቁ የሚገደዱበት ሁኔታ ጨርሶ ወደ ትምህርት አለሙ እንዳይመለሱ እንዳያደርግ ትሰጋለች። ለዚህም ምክንያት አላት። « ተማሪዎች ጦርነት ነው ብለው ይቀራሉ። በዚህ ምክንያት ብዙ የሚያቋርጡ ተማሪዎች አሉ። » ከዚህ በፊት በነበረው የሰሜኑ ጦርነትም  በርካታ ተማሪዎች ወደ ደባርቅ ዩንቨርስቲ እንዳልተመለሱ የምትናገረው ተማሪዋ ሌላ ክልል ላይ ትምህርት ማጠናቀቅን እንደ አማራጭ ታያለች። 

ኦሮሚያ ክልል ነዋሪ የሆነው የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ተማሪስ ዩኒቨርስቲው ቢጠራው ሄዶ ለመማር ስጋት ይኖረው ይሆን?

« ባህር ዳር ከተማ ላይ ስጋት የሚሆን ነገር አይኖርም። የተሻለ እና ሰላማዊ ሁኔታ ይኖራል ብዬ አስባለሁ። ትንሽ ስጋት የሚሆነው የመንገዱ ሁኔታ ነው።  የታሰበ እና በጉዳዩ ላይ የተያዘ ነገር ካለ አጣርታችሁ ግልፅ ብታደርጉልን» ይላል። ለተማሪዎቹ ጥያቄዎች  የትምህርት ሚኒስቴርን ምላሽ ለመጠየቅ በተደጋጋሚ ስልክ የደወልንላቸው እና ስለ ጉዳዩም የጽሁፍ መልዕክት የላክልንላቸው የትምህርት ሚኒስቴር ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወይዘሮ አመለወርቅ ህዝቄል ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ምንም አይነት ምላሽ ሳይሰጡን ቀርተዋል። ተማሪዎቹ ይማሩበት ወደነበሩት ዩንቨርስቲዎችም ስልክ ደውለን ነበር ስልክ አላነሱልንም። 

ልደት አበበ

ታምራት ዲንሳ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW