1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ ክልል የጸጥታ ሁኔታ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 25 2015

በአማራ ክልል ሰሞኑን ውጊያ የተካሄደባቸው አካባቢዎች መረጋጋታቸው ቢነገርም በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች በፋኖ እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ግጭት መቀጠሉም እየተነገረ ነው። ሰላም ለማስፈን ተፋላሚ ኃይሎች ተኩስ አቁመው ወደ ውይይት እንዲመጡ የአውሮጳ ኅብረት፤ የአፍሪቃ ኅብረት እና የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጥሪ አቅርበዋል።

ፎቶ ከማኅደር፤ አማራ ክልል ጭና ተክለሃይማኖት
በአማራ ክልል ሰሞኑን ውጊያ የተካሄደባቸው አካባቢዎች ዛሬ መረጋጋታቸው ቢነገርም ማኅበራዊ አገልግሎቶች ግን እንዳልተጀመሩ ከየአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። ፎቶ ከማኅደር፤ አማራ ክልል ጭና ተክለሃይማኖት ምስል AP/picture alliance

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

This browser does not support the audio element.

በአማራ ክልል ሰሞኑን ውጊያ የተካሄደባቸው አካባቢዎች ዛሬ መረጋጋታቸው ቢነገርም ማኅበራዊ አገልግሎቶች ግን እንዳልተጀመሩ ከየአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። በአንጻሩ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች በፋኖ እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ግጭት መቀጠሉም እየተነገረ ነው። በአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥም ሆነ የኢነትርኔት አገልግሎት አለመኖር መረጃ ለማሰባሰብ እንቅፋት ሆኗል።

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ይልማና ዴንሳ ወረዳ አዴት በምትባለው ከተማና በዙሪያዋ ከፍተኛ ውጊያ ትናንት ሲካሄድ እንደነበረ ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ያስረዳል። በውጊያው ምክንያት የአራት ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ እና ቀብራቸውም ዛሬ መፈጸሙን የከተማዋ ነዋሪ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል። በተመሳሳይ ምላጭ በር በተባለ አካባቢም የአራት ሰዎች ሕይወት በውጊያው መጥፋቱም ተሰምቷል። በምሥራቅ ጎጃም ዞን አማኑኤል ከተማም እንዲሁ በነበረው አለመረጋጋት ዛሬ ጠዋት የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉን የአካባቢው ነዋሪ ተናግረዋል። ይኽ በእንዲህ እንዳለም የተመ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አማራ ክልል ውስጥ በሚካሄደው ግጭት ቢያንስ 183 ሰዎች መገደላቸውን በማመልከት በክልሉ የሚፈጸመው ግድያ፤ የመብት ጥሰት እና ወከባ እንዲቆም ጥሪውን አቅርቧል። እሑድ ዕለት ባገረሸው ግጭት ደብረ ታቦር ከተማ ላይ ቢያንስ አራት ሰዎች መገደላቸው ሁለት ዶክተሮችን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል። አዣንስ ፍራንስ ፕረስ በበኩሉ ፍኖተሰላም ከተማ ላይ በአikር ጥቃት 26 ሰዎች መገደላቸውን የጤና ባለሙያዎች በእማኝነት ጠቅሷል። የመንግሥታቱ  ድርጅት አክሎም መንግሥት ያወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ ከአንድ ሺህ በላይ አብዛኞቹ ወጣት የአማራ ተወላጆች የሆኑ ዜጎች መታሠራቸውንም አመልክቷል። ይኽ በእንዲህ እንዳለም በአማራ ክልል ሰላም ለማስፈን ተፋላሚ ኃይሎች ተኩስ አቁመው ወደ ውይይት እንዲመጡ የአውሮጳ ኅብረት፤ የአፍሪቃ ኅብረት እና የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጥሪ አቅርበዋል። ትናንት ካቢኔያቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰበሰቡት የክልሉ አዲሱ ርዕሰ መስተዳድርም የክልሉን ሰላም ለመመለስ እንደሚሠሩ መግለጻቸው ተሰምቷል።

በአማራ ክልል ሰላም ለማስፈን ተፋላሚ ኃይሎች ተኩስ አቁመው ወደ ውይይት እንዲመጡ የአውሮጳ ኅብረት፤ የአፍሪቃ ኅብረት እና የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጥሪ አቅርበዋል። ፎቶ ከማኅደር፤ የአውሮጳ ኅብረት ምስል Daniel Kalker/picture alliance

ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW