የአማራ ክልል የፀጥታ ችግር ወላዶች ሕክምና እንዳያገኙ አድርጓል
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 19 2017በአማራ ክልል በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶች ቁጥር ከ55% በታች መሆኑን የጤና ባለሙያዎች ተናገሩ፣ በምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ወረዳ ብቻ ባለፈው ዓመት 49 እናቶች በወሊድና ተያያዥ ችግሮች መሞታቸዉን አንድ የፍኖተሠላም ሆስፒታል የእናቶችና ህፃናት ባለሙያ አስታዉቀዋል። በክልሉ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት የመረጃ ልውውጥም በእጅጉ መዳከሙን ባለሙያዎቹ ገልጠዋል።
በአማራ ክልል ያለው ያልተረጋጋ የፀጥታ ሁኔታ ችግር ከፈጠረባቸው ዘርፎች መካከል የጤናው ዘርፍ ግምባር ቀደሙ ነው። በየአካባቢዎቹ የሚከሰተው የፀጥታ መደፍረስና የመንገዶች ተደጋጋሚ መዝጋት ህሙማን ወደ ጤና ተቋማት በቀላሉ እንዳይደርሱ አድርጓል፣ መድኃኒትና ሌሎች ግብዓቶችንም ወደ ህክምን ማዕከላት ማድረስ ሌላው ፈተና ሆኗል። ችግሩ በተለይ ለወላድ እናቶች ሞት፣ እንግልትና ስቃይ ዋና ምክንያት እንደሆነ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን የፍኖተሠላም ሆስፒታል የእናቶችና ህፃናት ባለሙያ ተአግረዋል።
በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶች ቁጥር እየቀነስ ነው
ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ብዙዎቹ ወላዶች ወደ ጤና ተቋማት አይመጡም ከመጡም እጅግ ተጎድተው እንደሆን ነው የገለፁት፣ በዚህ ምክንያትም አንዳንዶቹ ለፌስቱላ እንደሚጋለጡሉ፣ ከዚያም ሲያልፍ ህይወታቸው እንደሚያልፍ አመልክተዋል።
“አብዛኛዎቹ እናቶች ወደ ጤና ተቋም አይመጡም፣ ከመጡም በቤታቸው ከወለዱና ችግር ከገጥማቸው በኋል በ"ቃሬዛ” /በእንጨት አልጋ/ በሠው ኃይል ታግዘው ነው፣ ባለፈው በጀት ዓመት በዚህ መንገድ ወደ ህክምና ከደረሱ በኋል 8 እናቶች ሞተዋል፣ 9 ደግሞ ፊስቱላ አጋጥሟቸዋል” በለዋል።
ባልፈው በጀት ዓመት ከአንድ ወረዳ ብቻ 49 እናቶች በወሊድ ምክን ያት ህይወታቸው ማለፉ መረጃ እንደደረሳቸውም ባለሙያው ተናግረዋል።
በቋሪት ወረዳ 49 እናቶች በወሊድ ሞተዋል
ባለሙያው እንዳሉት እስከ ሐምሌ 2016 ድረስ ከምዕራብ ዞን ቋሪት ወረዳ 49 እናቶች በወሊድ ምክንያት ህይወታቸው እንዳልፈ ከወረዳው ባለሙያዎች ሪፖርት ደርሷቸዋል።
በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ፈለቁ መኮንን በአምቡላንስ እጥረትና በሌሎችም ምክንያቶች ወደ ጤና ተቋማት መጥተው የሚወልዱ እናቶች ቁጥር ባለፉት 3 ወራት በግማሽ መቀነሱን አስረድተዋል።
እናቶች ወደ ጤና ተቋማት መጥተው እንዳይወልዱ የሆነበት ዋናው ምክንያት የአምቡላንስ አለመኖር እንደሆን የሚገልፁት ባለሙያዋ፣ በዚህም ምክንያት የእናቶች በጤና ተቋም የመውለድ ምጣኔ ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል፣ በዞኑ ባለፉት 3 ወራት ጤና ጣቢያ መጥተው የወልዱ እናቶች ከ50% አይበልጥም ነው ያሉት ።
በአማራ ክልል በጤና ተቋም የሚወልዱ እናቶች ምጣኔ 55% ብቻ ነው
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልከሪም መንግሥቱ ካለው ወቅታዊ የክልሉ የፀጥታ ችግር አኳያ በርካታ እናቶች ወደ ጤና ተቋማት እንደማይመጡ ጠቁመው፣ ሁሉም አካል እናቶች ወደ ጤና ተቋማት መጥተው እንዲወልዱ የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
ያለው የፀጥታ ሁኔታ በጤናው ዘርፍ እንደልብ እያሰራ አይደለም የሚሉት አቶ አብዱልከሪም በዚህም ምክንያት እናቶች ወደ ጤና ተቋም መጥተው መውለድ አልቻሉም ብለዋል፣ በአጠቃላይ በክልሉ በጤና ተቋማት የመውለድ ምጣኔ 55% መሆኑንም ገልፀዋል። የትራንስፖርት ችግር፣ የአምቡላንሶች አለመኖር፣ ዋና ችግሮች እንደሆኑም አመልክተዋል።
“በ18 ከተሞች ብቻ የኢንተርኔት ግንኙነት እናግኛለን” የአማራ ክልል ጤና ቢሮ
የክልሉ ጤና ቢሮ የእቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ አማረ ሹመት ወቅታዊ ሁኔታው በፈጠረው ችግር ምክንያት የመርጃ ልውውጡ የጤናውን ሥራ በጣም አስቸጋሪ እንዳደረገው አመልክተዋል።
በየወርዳው የኢንተርኔት አገልግሎትእንደልብ አለመኖር የመረጃ ልውውጡን በእጅጉ መጉዳቱንና የመረጃ ልውውጡን ፈታኝ እንዳደረገው ተናግረዋል። ። “በክልሉ በ18 ከተሞች ብቻ ነው የኢንተርኔት አገልግሎት ማግኘት የሚቻለው” ሲሉ ነው የግንኙነቱን ችግር የገለጡት።
በቀደም ሲል በሰሜኑ ጦርነት ወቅትና አሁን ደግሞ በአማራ ክልል ያለው የፀጥታ ችግር በአማራ ክልል ያለውን የጤና መሰረት ልማትና የግብዓት አቅርቦት ከፍተኛ ተፅዕኖ ውስጥ እንደከተተው በተለያይ ጊዜ ተገልጧል።
ዓለምነዉ መኮንን
ነጋሽ መሐመድ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር