1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ ክልል ገበሬዎች የማዳበሪያ ጥያቄ፤ ጥቃት በሃይማኖት ተቋማት እና ጠለፋ

ዓርብ፣ ግንቦት 25 2015

ሰሞኑን በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎችን እያነጋገሩ ነው። በዋናነት የበርካቶችን ትኩረት በሳቡ ሦስት ጉዳዮች ላይ ከተሰጡ አስተያየቶች የተወሰኑትን መራርጠናል።

Äthiopien Farmer und Farmland
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

This browser does not support the audio element.

 

በአማራ ክልል አርሶ አደሮች የክረምቱ የእርሻ ወቅት በተቃረበበት በዚህ ወቅት የአፈር ማዳበሪያ እንዳላገኙ እየገለጹ ነው። አጣን ያሉትን የአፈር ማዳበሪያ እንደወትሮው ሁሉ መንግሥት እንዲያቀርብላቸው በአደባባይ ሰልፍ ጭምር ለመጠየቅ መውጣታቸውም ታይቷል። የገበሬዎቹን ጥያቄ አስመልክተው በፌስቡክ ከተሰጡ በርካታ አስተያየቶች መካከል፤ ተስፉ ረታ፤ «አይ መንግሥት መዝናኛ ቦታ ከሚገነባ የማዳበሪያ ፋብሪካ ቢከፍት ይሻል ነበር።» ሲሉ፤ ታንክ ዩ ታምብ የሚል የፌስቡክ ስም ያላቸው ደግሞ፤ «መንግሥት ሆይ ገበሬን አትበድል ከገበሬ ጋራ ፖለቲካ አያምርም። ቶሎ መፍትሄ ይስጥ።» እንዳልክ በይናም ሃሳባቸው ይቀራረባል፣ «መንግሥት ለዚህ አርሶ አደር በቂ ማዳበርያ ማቅረብ አለበት በፍጥነት።»። ሃብታሙ አማረም እንዲሁ ለመንግሥት ጥሪያቸውን ያቀርባሉ፤ «መንግሥት ለእነዚህ አርሶ አደሮች የሚሉትን መረዳት አለበት ምክንያቱም ከማምረት ዉጭ የሚያዉቁት የለም ሊደመጡ ይገባል።»፤ ንሕልመይ እየዝነብር የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ደግሞ፤ «እዉነተኛ ገበሬ ሰላማዊ ጥያቄ በመላዉ ሀገሪቱ ያለ አርሶ አደር ገበሬ ጥያቄዉ ይመለስለት መዳበርያ ይሰጠዉ።» ነው የሚሉት። ፋልማታ ሀሰንም እንዲሁ፤ «ትክክለኛ ጥያቄ፤ በጨዋነት የተሞላ፤ መንግሥት በፍጥነት መፍትሔ ቢሰጥ ጥሩ ነው« ነው የሚሉት። ዳዊት አሰፋ መገርሳም ፤ «እርጋታ የተሞላበት ፣ትክክለኛ እና በአፋጣኝ መለስ ማግኘት ያለበት ጥያቄ» በማለት ሃሳባቸውን ይጋራሉ።

ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የትዊተር ተጠቃሚው የጌታ ባሪያ ደግሞ «የመንግሥት ባለሥልጣናት እንድንታገስ ነግረውናል። አሁን የእርሻው ጊዜ ካመለጠን ዕጣችን ምን ሊሆን ነው? ምንስ ልናደርግ ነው? መፍትሄውን ንገሩን» ማዳበሪያ በማጣታቸው ለተቃውሞ የወጡ ልብ ሰባሪው የአማራ ገበሬዎች ተማጽኖ።» በማለት በእንግሊዝኛ ቋንቋ አርሶ አደሮቹ ከተናገሩት ጠቅሰው አጋርተዋል። ሌላው የትዊተር ተጠቃሚ አለኸኝ በቀለ በበኩላቸው፤ «ይኽ ጉዳይ የገበሬው ብቻ አይደለም እኛንም ይበልጥ ሊያሳስበን ይገባል በኋላ የእህል ያለህ ማለቱ ዋጋቢስ ነው።» ብለዋል። ሳምራዊት ጌታቸውም እንዲሁ በትዊተር፤ «እኔ የምለው ግን ከተሜው ምን ሊበላ ነው? ገበሬ እኮ ለራሱ አያንሱም፤ ከአሁኑ መጪው እጅግ አስፈሪ ነው።» ነው ይላሉ። የሰው ሀገር ሰው የሚል ስም ያላቸው ሌላው የትዊተር ተጠቃሚ፤ «የማዳበሪያ እጥረት የሚለው አገላለጽ ስህነት ነው» ይላሉ። አስተያየታቸው ይቀጥላል፤ «የማዳበሪያ እጥረት የሚለው አገላለጽ ስህነት ነው፤ እጥረት ሳይሆን ክልከላ ነው። እጥረት ቢሆን በሌላም አካባቢ ይከሰት ነበር። » ሲሉም ይሞግታሉ። የአርሶ አደሮቹ ችግራቸውን በአደባባይ ወጥተው መግለጽ ያስደሰታቸው የሚመስሉት ጌት ጋሻነህ በፌስቡክ፤ «ጎበዝ በርቱ መንግሥት ምላሽ መስጠት አለበት።» ሲሉ፤ ኢቤላ ዋቢ ደግሞ፤ «ይኽ በጣም ጥሩ እና ሕጋዊ ጥያቄ ነው፤ መንግሥት ተመልክቶ ባስቸኳይ ችግሩን ማስወገድ ይኖርበታል።» ብለዋል። ማማሩ ነጋ ኦኬም፤ «በገዛ ገንዘቡ መንግሥት የህዝብን ጥቅም አለማስጠበቅ ማለት የተፈጥሮ ኦክስጂንን እንደማገድ ይቆጠራል« ነው ያሉት። ባንተይሁን ጥላዬ ኃይሉ ደግሞ፤ «ገበሬ አርሸ ህዝብን ልመግብ በማለቱ ተሰቃየ።» ባይ ናቸው። የአርሶ አደሮች አቤቱታቸውን ለማሰማት አደባባይ መውጣት፣ ለትዊተር ተጠቃሚው አበበ አፈወርቅ፣ «የ1960ው አብዮት? ተመልሶ መጣ እንዴ?» ብለው እንዲጠይቁ ሲያደርግ፤ በላይ አሰፋም በፌስቤክ፤ « የመጨረሻው መጀመሪያ ነው» አስብሏቸዋል። ሚኪ ደግሞ፤ «አሳዛኝ» ሲሉ በአጭሩ ሃሳባቸውን አካፍለዋል።

ምስል AP

በአዲስ አበባ ዙሪያ በኦሮሚያ ክልል የመስኪዶች መፍረስ ከመንግሥት ፍትህ እየተጠየቀበት ነው። በአማራ ክልል ደብረ ኤልያስ ብሔረ ብፁዓን ሥላሴ መልከአ አንድነት ገዳም በጸጥታ ኃይሎች ጥቃት የመጎዳቱ፤ በአርሲ በአርሲ ዞን ጢዮ ወረዳ ጨፌ ሚሶማ በተባለ አከባቢም ታጣቂዎች አራት ሰዎች መግደላቸውም ተሰምቷል። በሃይማኖት ተቋማት እና አማኞች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን አስመልክቶ በፌስቤክ ከተሰጡት አስተያየቶች፤ ጌታቸው ማሞ፤ «እጅግ ያሳዝናል፣ ድርጊቱን ትክክል አይደለም ስትል ፀረ ኦሮሞ ብለው ይፈርጁሃል፣ ለሞቱት ነብስ ይማር፣ ወይ ይህቺ ሀገር እንዲሁ እየታመሰች ቀጥላለች?» በማለት ሲጠይቁ፤ ታደሰ ሃይለማርያም በበኩላቸው፤ « ያሁኑ ይባስ " አለ ያገሬ ሰዉ ? ወዴት ወዴት እየሄድን ይሆን ?» በሚል እሳቸውምጥያቁ አቅርበዋል። አሊ ሀሙድ ደግሞ፤ «መንግሥት ከሃይማኖት መራቅ ነበረበት» ባይ ናቸው። ማር ዘነብ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚም፤ «አንድም መስጊድ መፍረስ የለበትም። ማነኛውም የአምልኮ ቦታ መከበር አለበት።» ይላሉ። ጃፋር አሊ ሂቦ ደግሞ «ሕገ ወጥ የሆኑ ግንባታዎችን የማፍረሱ ሂደት ተጠናክሮ ይቀጥላል።» በሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ምስል Seyoum Getu/DW

 ነስረ ይልማ፤ «በሥልጣን ላይ ያለ አካል ሃይማኖትን ሲነካ አለሃ የሱን ቁዋ ያነሳበታል ። ህዝቡ የዳምጠኛል ያስተዳድረኛል ችግሮቼን ይፈታልኛል ብሎ በመረጠው መንግሥት የሀይማኖቱን መገለጫ የሆነ መስጂድ መፍረሱ ያሳዝናል ።» በማለት ሃሳባቸውን አጋርተዋል። አቡ ዑካሻ አቡ ሱፊያንም እንዲሁ፤ «ሕወታቸው ያለፈው ወንድሞቻችን አላህ ይርሀም የፈረሰውን መሳጅዶች የመንግሥት አካላት በመነጋገር ተለዋጭ ቦታ እዲሰጥና እንዲገነባልን በጥብቅ እንጠይቃለን።» ብለዋል። ሜምኖን ኃይለ ሚካኤል በትዊተር፤ «ከአርሲ  የኢትዮጵዮ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች በአሰቃቂ ሁኔታ በኦነግ ታጣቂዎች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተፈጸመውን ግድያ የሚያሳይ ምስሎችን ተመለከትኩ። በተመሳሳይ በደብረ ኤልያስ ገዳምም የመነኮሳት አስከሬን ፎቶ አየሁ። ኢትዮጵያ!» ሲሉ። ሰይድ ሙሀመድ በበኩላቸው፤ «እምየ ኢትዮጵያ መቼ ይሆን የሠላም ዜናሽን የምሠማው?» በማለት የተሰማቸውን ገልጸዋል።


ምስል Joel Saget/AFP/Getty Images/Newscom/picture alliance

ሌላው ሰሞኑን የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴው ተጠቃሚዎችን በስፋት እያነጋገረ የሚገኘው በሀወሳ ከተማ ከንቲባ ጠባቂ ተጠፈች የተባለችው ወጣት ጉዳይ ነው። ወጣቷ የዳሸን ባንክ ሠራተኛ መሆኗን ጠላፊው ደግሞ ኮንስታብል መሆኑም ተጠቁሟል። ጠለፋ ጎጂ ባህል ከሚባሉት አንዱ ሆኖ ሳለ ዛሬም እንደ ወግ መታየቱን የተቹ፤ ጠላፊው የፖሊስ ባልደረባ መሆኑ አልፎ ተርፎም ከባለሥልጣን ጥግ መሆኑ ፍትህ እንዲጓተት አድርጓል በሚል ማነጋገሩን ቀጥሏል።  እንዲያም ሆኖ ፖሊስ ከተጠርጣሪው ጋር ያበሩና መረጃ በማቀበል የረዱ ያላቸውን ስድስት ፖሊሶችን አስሮ እየመረመረ መሆኑ ተዘግቧል። ምህረት በቀለ፣ «የክልሉም ይሁን የፌዴራል ፖሊስ መያዝ አቅቶት አይመስለኝም የሆነ የተደበቀ ግልፅ ያልሆነ ነገርማ አለ» ሲሉ፤ መሬም ኢብራሂምም እንዲሁ፤ «ሕግ ሲኖር እኮ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህ የሚጠየቀው» ይላሉ። ዴቬ አብ ደግሞ፤ «በሚያሳዝን ሁኔታ ሴት ጠልፈው ይደፍራሉ ከዝያ ሽማግሌ ይላካል፤  ልጅቷም ድንግልናዋን ካጣች ተፈላጊ አይደለችም ተብሎ ስለሚታሰብ ለደፋሪዋ በሰርግ ትሰጣለች፤ ይሄ ሀዋሳ ውስጥ ከዚህ በፊትም ተከስቶ ሰምቻለሁ፤ ባህል ቢጤ ነው።» በማለት ያስረዳሉ፤ ሳምሶን ሰሎሞን ደግሞ፤ «በዚህ ጉዳይ የተጎዱ እህቶቻችን ቢናገሩ ያምራል ሲዳማ አንዳንድ ገጠር ከተሞች የተለመደ በሕግ በባህል ለሴትልጅ ምላሽ የማይሰጥ በተለይ የሴት ቤተሰብ የሚገፉበት የሚበደልበት ያደባባይ ሚስጥር ነው።» ባይ ናቸው። ወርቁ ኪሮስም እንዲሁ በትዊተር፤ አንድ የክልል ዋና ከተማ ላይ ጠለፋ ከተጀመረ ሀገሪቱ ወደ ሙሉ ስርዓተ አልበኝነት ለመግባት እየተንደረደረች እንዳለች ጥሩ ማሳያ ይሆናል።» ነው የሚሉት። እናቴ እወድሻለሁ በበኩላቸው፤ «ወጠምሾች እንደልባቸው በዚች ሀገር እንዲፈነጩባት በመንግሥት ይሁንታ ተፈቅዶላቸዋል ፍትህ ሕግ እሚባሉት ባልሰማ ይታለፋሉ ይህው ነው።» ይላሉ።  ዳዊት አበበ ደግሞ ፤ «በቃ የድሮ ዘመን ልመለስ ነው መሰለኝ» ሻንቆም በትዊተር ተመሳሳይ አስተያየት ነው ያጋሩት፤ «አሁንም ጠለፋ? ጉዞ ጥንታዊ የጋርዮሽ ስርዓት በሉኛ» በማለት። የወጣቷ ጠለፋ ብዙዎችን እያነጋገረ ሳለ ለ10 ቀናት ገደማ ከተሰወረችበት ተለቃ ወደ ሀወሳ መመለሷ ተሰምቷል። ይህን አስመልክተው ዳግማዊ ታሪኩ በፌስቡክ፤ «በሀዋሳ" ተጠልፋ" የነበረችው እህታችን "በሰላም " ወደ ቤት ተመልሳለች የሚሉ ፖስቶች እያየሁ ነው። በሰላም መመለስ ምን ማለት ነው? እህታችን ያለፈችበትን ማወቅ ባይቻል መገመት ግን አይከብድም ።» ነው ያሉት።  

ምስል CHRIS DELMAS/AFP via Getty Images

ሸዋዬ ለገሠ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW