የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ሠራተኞች የደመወዝ ጥያቄ
ቅዳሜ፣ መጋቢት 20 2017
በአማራ ክልል የተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች በሥራ ላይ የሚገኙ የአማራ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ሠራተኞች አሁን የሚከፈላቸው ደመውዝ ኑሯቸውን በአግባቡ እንዲመሩ ባለማስቻሉ የደመውዝ ማሻሻያ እንዲደረግላቸውና ጥቅማጥቅሞች እንዲከበርላቸው ለበርካታ ጊዜ ሲጠይቁ እንደነበር ይገልፃሉ። ጥያቄያቸው ምላሽ አግኝቶ የክልሉ መንግሥት የደመወዝ ማሻሻያና ጥቀማጠቅሞች እንዲፈቀዱ የወሰነ ቢሆንም የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ውሳኔውን ተከትሎ ሊያስተገብረው እንዳልቻለ ሠራተኞቹ ይናገራሉ፡፡
ሠራተኞቹ ውሳኔው ተግባራዊ እንዲደርግ የሚመለከታቸውን ኃላፊዎች ሲጠይቁም ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው እንደሆነ ነው ለዶይቼ ቬሌ የተናገሩት፡፡
እንደሰራተኞቹ አስተያየት አንዳንድ የዞንና የወረዳ አመራሮች ለምን ጠያቄ ታነሳላችሁ በማለት ከሥራ ትባረራላችሁ እስከማለት ደርሰዋል ነው ያሉት፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ጥያቄውን ለመስማትም ፍላጎት እንደሌላቸው አመልክተዋል፡፡
ከዛሬ ነገ አዲሱ ደመወዝና ጥቅማጥቅም እንድሚደርሳቸው ቢጠብቁም እስካሁን የመጣ ነገር እንደሌለ የሚናገሩት አስተያየታቸውን የሰጡን የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ሠራተኞች እንዲያውም ጥያቄ ሲጠይቁ ከአንዳንድ ኃላፊዎቻቸው “ቢሮውን መልቀቅ ትችላላችሁ” የሚል ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት እንደሚደርሳቸው ተናግረዋል፡፡
“ደመወዝ ከተከፈለን 4ኛ ወራችን ነው” የመንዝ ላሎ ምድር ወረዳ ሠራተኞች
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ታዘባቸው ጣሴ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የሠራተኛው የደመውዝ ይሻሻልልኝና የጥቅማጥቅም ጥያቄ በክልሉ መንግሥት አዎንታዊ ምላሽ ማግኘቱን ጠቅሰው ሆኖም ሠራተኛው ጉዳዩን በትዕግሥት እንዲጠብቅ ጠይቀዋል፡፡ የወረቀት ሥራ እንደቀረው የሚናገሩት አቶ ታዘባቸው ሠራተኛውም ሥራውን እየሰራ በትዕግስት እንዲጠብቅ አደራ ብለዋል፡፡
አንዳንድ የሥራ ኃላፊዎች የሠራተኞችን ጥያቄ በአግባቡ መልሰው ካልሆነ ትክክል ባለመሆኑ መታረም እንዳለበትም ኃላፊው አሳስበዋል፡፡ የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ በብጀት ዓምቱ ከ71 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለምሰብሰብ አቅዶ እስካሁን 38 ቢሊዮን፣ 638 ሚሊዮን፣ 534ሺህ፣ 603 ብር መሰብሰብ መቻሉን አቶ ታዘባቸው ተናግረዋል፡፡ ቢሮው አጠቃላይ በክልሉ 7ሺህ 901 ሠራተኞች እንዳሉት ያገኘነው መረጃ ያመለከታል፡፡
ዓለምነው መኮንን
እሸቴ በቀለ