1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ ክልላዊ መንግስት የሰላም ጥሪዉን ማራዘሙ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 9 2016

የአማራ ክልላዊ መንግስት ዳግም ለ 7 ቀናት የሚቆይ የሰላም ጥሪ ማድረጉን አስታወቀ፡፡ የክልሉ መንግስት ጥሪውን ያስተላለፈው፣ ከዚህ በፊት የተሰተው የ7 ቀናት የሰላም ጥሪ በቂ ባለመሆኑ ነው ብሏል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች ውጊያዎች እንደነበሩና አሁንም እንደቀጠሉ ከየአካባቢው የሚደርሱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

 ዶ/ር መንገሻ ፋንታው የአማራ ክልል መንግስት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ
ዶ/ር መንገሻ ፋንታው የአማራ ክልል መንግስት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊምስል Alemnew Mekonnen/DW

በአማራ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች ውጊያዎች እንደነበሩና አሁንም እንደቀጠሉ ከየአካባቢው የሚደርሱን መረጃዎች ያሳያሉ

This browser does not support the audio element.

የአማራ ክልላዊ መንግስት ዳግም ለ7 ቀናት የሚቆይ በክልሉ ለሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች የሰላም ጥሪ ማድረጉን አስታወቀ፣ የክልሉ መንግስት ጥሪውን ያስተላለፈው፣ ከዚህ በፊት የተሰተው የ7 ቀናት የሰላም ጥሪ በቂ ባለመሆኑ ነው ብሏል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች ውጊያዎች እንደነበሩና አሁንም እንደቀጠሉ መሆናቸውን ከየአካባቢው የሚደርሱን መረጃዎች ያሳያሉ፣ በደቡብ ወሎ ወገልጤና የተባለችውን ከተማ የመከላከያ ሰራዊት ሲቆጣጠር፣ በምዕራብ ጎጃም የፈረስ ቤት ከተማን ደግሞ የፋኖ ታጣቂዎች ተቆጣጥረዋል፡፡

ከአለፈው ሐምሌ 2015 ዓ ም መጨረሻ ጀምሮ በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎችና በመከላከያ ሰራዊት መካከል ውጊያ ከተቀሰቀሰ ጀምሮ በርካታ ቁሳዊና ሰብአዊ ጉዳቶች ደርሰዋል፡፡ የተከሰተውን ውጊያ ተከትሎ መንገዶች በመዘጋታቸው እለታዊ የምግብ ፍጆታዎችን ወደ ገበያ ወጥቶ መግዛትም ሆነ መሸጥ አልተቻለም፣ የመድሀኒት እጥረቶችም በየጤና ተቋማቱ መከሰታቸውን ነዋሪዎቹ ይናገራሉ፡፡

የአማራ ክልል መንግስት  ከአስቸኳይ ገዜ አዋጅ ጣቢያ መምሪያው ጋር በመመካከር ለታጣቂዎቹ ባለፈው ሳምንት የ7 ቀናት የሰላም ጥሪ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ የሰላም ጥሪው ትናንት ሲጠናቀቅ “ጊዜው በቂ አይደለም” በሚል የክልሉ መንግስት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መንገሻ ፋንታው ሌላ ተጨማሪ የ7 ቀናት የሰላም ጥሪ መተላለፉን ትናንት ማምሻውን በሰጡት መግለጫ አመልክተዋል፡፡

የሰላም ጥሪውን ተከትሎ ባለፉት 7 ቀናት እጃቸውን ለመንግስት የሰጡ የተባሉ ታጣቂዎችን ቁጥር መንግስት በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ይህ በእንዲህ በአንዳንድየአማራ ክልል አካባቢዎች ውጊያዎችመኖራቸውን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ በምዕራብ ጎጃም ዞን ደጋዳሞት ወረዳ ዛሬን ጨምሮ ሰሞኑን ከፍተኛ ውጊያ እንደነበር የፈረስ ቤት ከተማ ነዋሪ ለዶይቼ ቬሌ አመልክተዋል፡፡

ሌላ የፈረስ ቤት ከተማ ነዋሪ ዛሬም በአካባቢው የተኩስ ልውውጥ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

“ትናንትና ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ውጊያው ተጀመረ፣  ዋለ ሙሉ ቀን፣ ከተማም ገጠርም ነበር ውጊያው፣ በጣም ጠንካራ ውጊያ ነው የነበረው፣ ሌሊቱን ውጊያ አልነበረም፣ ዛሬ ጠዋት ደግሞ በከተማው ዙሪያ ይተኮሳል፡፡” ብለዋል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤትምስል Alemnew Mekonnen/DW

ይህ ዘገባ እየተጠናቀረ ባለበት ዛሬ 7  ሰዓት ላይ የፋኖ ታጣቂዎች የፈረስ ቤት ከተማን  መቆጣጠራቸውን አንድ የዓይን እማኝ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡

“ትናንት ከጠዋት ጀምሮ ውጊያ ነበር፣  ዛሬ ጠዋትም ከፍተኛ ውጊያ ነበር ዛሬ ቀን 7 ሰዓት ከተማዋን ፋኖ ተቆጣጥሯታል፡፡”

በተመሳሳይ በደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ ወገልጤና ከተማ ከወራት በኋላ ሰሞኑን በመከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር መዋሏን ግን ደግሞ ምንም ዓይነት የመንግስት ስራ እንዳልተጀመረ አንድ ከተማዋ ነዋሪ ለዶይቼ ቬሌ አመልክተዋል፡፡

“ ከትናንት ወዲያ መከላከያ ወደ ወገልጤና ሲገባ፣ ጠዋት ለሁለት ሰዓት ሩብ ጉዳይ  ጀምሮ በፋኖና በመከላከያ መካከል ውጊያ ነበር ከወር በላይ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ዝግ ናቸው” ብለዋል፡፡

በደቡብ ጎንደር ዞን ልጫና አርብ ገበያ በተባሉ አካባቢዎች ሰሞኑን ከፍተኛ ውጊያ እንደነበር አስተያት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡ መንግሰት ያወጣውን የሰላም ጥሪ በተመለከተ ከፋኖ በኩል አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡

ዓለምነው መኮንን

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW