1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችኢትዮጵያ

የአማራ ክልል ጦርነት፣ የድሮን ጥቃት የመከላከያ ሠራዊት ምላሽ

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 3 2016

ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ “ጽንፈኛ” ካሏቸው ኃይሎች ጋር የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሚያደርገው ውጊያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ወይም ድሮኖች መጠቀሙን እንደሚቀጥል ተናግረዋል። የጦሩ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም “ሕዝብ ላይ ድሮን አይተኮስም” ቢሉም በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ጄኔራል ሳሉ
ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት መፈጸሙን እንደሚቀጥል ተናግረዋል። ፎቶ፦ ከማሕደርምስል Office of the Prime Minister

የአማራ ክልል ጦርነት፣ የድሮን ጥቃት የመከላከያ ሠራዊት ምላሽ

This browser does not support the audio element.

ከመከላከያ ሠራዊት ጋር የትጥቅ ውጊያ ጦርነት ውስጥ በገቡ የፋኖ ታጣቂዎች ላይ በድሮን የሚወሰደው እርምጃ እንደሚቀጥል "በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ" ለብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያው ማብራሪያ የሰጡት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ። 

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ይህንን ያሉት የሚሠነዘሩ የድሮን ጥቃቶች ሲቪል ሰዎችን እየጎዱ ነው የሚል መረጃ መኖሩ ተጠቅሶ እንዲያብራሩ ሲጠየቁ ነው። "የጽንፈኛ ስብስብ ስናገኝ በድሮን እንመታለን" ያሉት የሠራዊቱ አዛዥ "ሕዝብ ላይ ድሮን አይጣልም" ሲሉ የድሮን ጥቃቶች ኢላማዎች ታጣቂዎች ስለመሆናቸው ገልፀዋል። 

የፋኖ ታጣቂዎች ከመከላከያ ሠራዊት ጋር የትጥቅ ግጭት ውስጥ የገቡበት ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጀምሮ ግን ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ የዐይን እማኞች በሚሰነዘሩ የድሮን ጥቃቶች ንፁሃን ዜጎች ጭምር እየተጎዱ ለሞትና ለአካል መጉደል መዳረጋቸውን ገልፀዋል።  

ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ የድሮን ጥቃት በታጣቂዎች ላይ ያነጣጠረ ነው ቢሉም ላሊበላ አካባቢን ጨምሮ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል። ምስል Annabelle Steffes-Halmer/DW

ወሎ ውስጥ ባለው የሠራዊቱ እና የፋኖ ጦርነት፣ ከላሊበላ ከተማ አርባ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለ የገጠር መንደር ውስጥ  ባለፈው ሳምንት የተሰነዘረ የድሮን ጥቃት ንፁሃን ገበሬዎችን ጭምር ስለመግደሉ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የአካባቢው ነዋሪ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ሰሜን ሸዋ ውስጥ ባለው ግጭት በተለያዩ ወረዳዎች ላይ ሠራዊቱ ብቻ በታጠቃቸው ድሮኖች አልፎ አልፌ በሚፈፀሙ ጥቃቶች ሰላማዊ ዜጎች ተጎጂ ስለመሆናቸው ሌላ የመረጃ ምንጫችን ገልፀዋል።

"ድሮን ይሄን ያህል ተጠቅመናል" ማለት እንደማይችሉ የገለፁት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁሉ እርምጃው በየትኛውም ቦታ በሉ "ጽንፈኞች" ላይ ይቀጥላል ብለዋል። በአማራ ክልል በአብዛኛው አካባቢ ለወራት በቀጠለው ጦርነት የኢትዮጵያ መንግሥት ሪፖርቱን ባይቀበለውም "ድሮንን ጨምሮ በከባድ መሣሪያዎች በተሰነዘሩ ጥቃቶች በሲቪል ሰዎች ላይ ሞት እና የአካል ጉዳት" መድረሱን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ማረጋገጡ ይታወሳል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የሀገሪቱን አጠቃላይ የፀጥታ ሁኔታ "በከፍተኛ ሁኔታ የተሻሻለ" ነው ሲሉ ገልፀዉታል። "አሁን ከባድ ኪሳራ ደርሶባቸዋል" ያሏቸው የፋኖ ታጣቂዎች ጋር በቆየው ጦርነት ምክንያት የአማራ ክልል መዋቅሩ ተሽመድምዶ እንደነበር እና አሁን "የሚታገል" ያሉት መዋቅር ስለመትከሉ፣ ከተሞች ሰላም ስለመሆናቸው አብራርተዋል።

በክልሉ አደገኛ ያሉት ነውጥ ተደርጎ እንደነበር ሆኖም "ጠላት" ያሉት ኃይል በእጅጉ ስለመዳከሙ በዝርዝር ገልፀዋል። በታጣቂዎች ላይ የሚሰነዘረው የድሮን ጥቃት ቀጣይ መሆኑን ሆኖም ግን በሕዝብ ላይ መሣሪያው እንደማይተኮስ ተናግረዋል። 

በአማራ እና ኦሮሚያ ያሉ ታጣቂዎች "የጅል" እና "የሞኝ" እቅድ ይዘዋል

ሰሞኑን አዲስ አበባ ላይ ሊደረግ ታቅዶ በመንግሥት ክልከላ የተጣለበት ሰላማዊ ሰልፍ መከልከሉ ትክክል መሆኑን የገለፁት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ምክንያት ብለው የጠቀሱት "የብጥብጥ አላማ ያለው መሆኑን" ነው። 

ጽንፈኛ ብለው የሚጠሩት የፋኖ ታጣቂ ባህርዳርን ተቆጣጥሮ ፊቱን ወደ አዲስ አበባ የማድረግ "የጅል" ያሉት እንቅስቃሴ እንደነበር፣ ኦነግ ሸኔ በኦሮሚያ ክልል መንግሥትን በኃይል አስገድጄ የሰላም ድርድር ውስጥ አስገባለሁ በሚል "የሞኝ" ያሉት እቅድ እንደነበራቸውም ዘርዝረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ሦስተኛ ዙር የሰላም ንግግር ሊያደርጉ እንደሚችሉ ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ተናግረዋል። ምስል Michael Tewelde/AFP

የመንግሥትና የኦነሠ ሦስተኛ ዙር ንግግር ይኖር ይሆን ?

በመንግሥት እና በኦነግ ሸኔ መካከል የነበረውን ድርድር ሕዝብም ፣ መንግሥትም ይፈልጉት እንደነበር፣ "በመጀመርያው ንግግር ጥሩ ርቀት" ተሂዶ እንደነበር"፣  ሁለተኛው ላይ ግን "ያልተጠበቁ ጥያቄዎች ተነሱ" በማለት የሥልጣን አካፍሉን ጥያቄ ጭምር ከኦነግ ሸኔ ለመንግሥት መቅረቡንም ተናግረዋል። ሦስተኛ ዙር ንግግር ይኖራል የሚል ግምት እንዳላቸውም የሠራዊቱ አዛዥ ገልፀዋል።

የአማራ ክልል መንግሥት ትናንት የታጠቁ ኃይሎች በሰባት ቀናት ውስጥ በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን እንዲሰጡ ጥሪ አድርጓል። ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁሉ እንዳሉት ኢትዮጵያ የግጭት አዙሪቷ በቃ ካልተባለ ከፊት የሚኖረው አደጋ አደገኛ ነው።

ሰለሞን ሙጬ
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሰ 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW