የአማራ ክልል 10ኛ መደበኛ ጉባኤና የክልሉ ሠላም
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 22 2017
“በአማራ ክልል ያለውን ጦርነት መቀልበስ ተችሏል” ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ገለጡ፣ በአንፃሩ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬሌ የሰጡ አንዳንድ የክልሉ ነዋሪዎች “አሁንም በክልሉ ሠላም የለም” ብለዋል፡፡
የ11 ወራት የክልሉን መንግሥት ሪፖርት ለአማራ ክልል ምክር ቤት ያቀረቡት ርዕሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ፣ በነበረው ጦርነት በ11 ወራት 2000 ትምህርት ቤቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ እየተገባደደ ባለው ዓመት 147 ሠዎች በኮሌራና በወባ ህይወታቸው ማለፉም ተመልክቷል፣ ከ5ሺህ በላይ ህፃናት ህይወታቸው አልፎ የተወለዱ ሲሆን ከ290 በላይ እናቶች ደግሞ ከወሊድና እርግዝና ጋር በተያያዘ መመታቸው ለምክር ቤቱ በቀረበ ሪፖርት ተመልክቷል፡፡
የአማራ ክልል የሠላም ሁኔታ “ተሻሽሏል” መባሉና የነዋሪዎች አስተያየት
ባለፈው ቅዳሜ በተጀመረውና ነገ ይጠናቀቃል ተብሎ በሚጠበቀው የአማራ ክልል 10ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የክልሉን የ11 ወራት ሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡት ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በአብዛኛዎቹ ዘርፎች የተሻሉ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል፡፡ከሁለት ዓመታት በፊት ጀምሮ በክልሉ የተፈጠረውን ጦርነት መቀልበስ ተችሏል ያሉት አረጋ ከበደ፣ ሆኖም አሁንም በክልሉ ሙሉ ሠላም ለማምጣት መተባበር እንድሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
“ዘላቂ ሠላም ለማምጣት ታጠቀው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ከጠመንጃ ይልቅ በሀሳብ የበላይነት በውይይትና በንግግር እንዲያምኑ ሁላችንም የበኩላችን ጥረት አጠናክረን መቀተል ይኖርብናል፡፡” ብለዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በክልሉ ያለውን ሠላም መቀልበስ መቻሉን ቢገልፁም አሁንም ደም አፋሳሽ ጦርነቶች በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች መቀጠላቸውንና በብዙ አካባቢዎች “ሠላም አለ” ማለት እንደማይቻል አስተያየት የሰጡን የፈረስ ቤት፣ የላስታና የአቸፈር ወረዳዎች አስተያየት ሰጪዎች ይገልፃሉ፡
በተለይ ከላስታ አስተያየታቸውን የሰጡን ነዋሪ፣ “ህዝቡ ሠላም ይፈልጋል፣ ሠላም ግን የለም ህዝቡ በሁለቱም በኩል እየተጎዳ ነው፣ ሠላም ነው የሚባለው ትክክል አይደለም፣ የትኛውንም ቦታ ሠላም ነው ለማለት አይቻልም፡፡” ነው ያሉት፡፡
በግብርናው ዘርፍ የተገኘው ምርትም ከእቅድ አኳያ ከፍትኛ መሆኑና በዚህ የግብርና ወቅት የ8.8 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ግዥ ተፈፅሞ 5.5 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ወደ አርሶ አደሩ ማሰራጨት መቻሉን ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል፡፡
በ2016/17 የምርት ዘመን በአማራ ክልል 170.4 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተገኝቷል” ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ
በ2016/17 የምርት ዘመን 5.3 ሚሊዮን ሄክታር ማሳ በማልማት 170.4 ሚሊዮን ኩንታል (የእቅዱን 104%) ምርት ማግ ኘት እንደተቻለ ያመለከቱት አቶ አረጋ፣ ይህም ምርታማነትን 32.3 ኩንታል በሄክታር ማሳደግ እንደተቻለ አብራርተዋል፡፡ የተገ ኘው ምርት ከቀዳሚው ዓመት ከተመረተው 145.3 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ሲነፃፀር የ25.1 ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ እንዳለውም በሪፖርታቸው ገልጠዋል፡፡
አንድ የአችፈር ወርዳ አርሶ አድር በአካባቢያቸው ባለፈው ዓመት የተሻለ ምርት እንደተመረተ ቢናገሩም፣ የማዳበሪያ አቅርቦቱ ግን ወቅቱን ያለጠበቀና በየመደብሩ እንደ ሸቀጥ “እየተቸረቸረ ነው” ሲሉ ተችተዋል፡፡
“... እስካሁን ድረስ ቦቆሎ ላይ ዩሪያ አልተጨመረም፣ ዳፕ ጠፋ ተብሎ ደግሞ ወቅቱ ካለፈ በኋላ ዘግይቶ መጣ” ብለዋል፡፡ ስርጭቱም ችግር እንዳለበት የሚናገሩት አርሶ አደሩ በየመደብሩ እንደሸቀጥ እየተሸጠ እንደሆነ እንዲህ ሲሉ ገልጠዋል፣ “ቅባት በሚሸጥበት ሱቅ ሁሉ ተደርድሮ ታየዋለህ፣ በረንዳው ሁሉ ማዳበሪያ ተደርድሮበት ታያለህ፣ ወደ ሸቅጥነት ቅይረውታል፡፡” ብለዋል፡፡
በትምህርቱ ዘርፍ ለ7 ሚሊዮን ተማሪዎችነ ለመመዝገብ ተከታታይ ሙከራዎችን ማድረግ ቢቻልም በክልሉ ከ2.8 ሚሊዮን በላይ ተማሪ መመዝገብ እንዳልተቻለ ሪፖርት ያቀረቡት አቶ አረጋ ከተመዘገቡት መካክልም 19% የሚሆኑት ማቋርጣቸውን አመልክተዋል፡፡ ባለፉት 11 ወራት ብቻ ባለው ጦርነትምክን ያት 2000 ትምህርት ቤቶች መጎዳታቸውን ገልጠዋል፡፡
በአማራ ክልል 706 አፀደ ህፃናት፣ 9ሺህ 590 1ኛና መለሰተኛ 2ኛ ደረጃና 701 በአጠቃላይ 10997 ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ በሪፖርቱ ተገለጧል፡፡
“በ11 ወራት 5ሺህ 364 ጨቅላ ህፃት ህይወታቸው አልፎ ተወልደዋል” የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር
በጤናው ዘርፍ ባቀረቡት ሪፖርት በርካታ የተሻሉ አፈፃፀሞች ቢኖሩም እየተገባደደ ባለው በጀት ዓመት ከወሊድ ጋር በተያያዘ 293 እናቶች ህይወታቸው አልፏል፣ 5ሺህ 364 ጨቅላ ህፃናት ደግሞ በእናታቸው ማህፀን እንዳሉ ህይወታቸው አልፎ የተወለዱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ 16ሺህ የሚጥጉ ከ 5 ዓመት እድሜ በታች የሆኑ ህፃናት ደግሞ ለከፋ የምግብ እህል እጥረት የተጋለጡ መሆናቸውን በሪፖርታቸው አመልክተዋል፡፡
የአማራ ክልል ምክር ቤት የሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ አበራሽ ታደሰ ባቀረቡት ሪፖርት ባለፉት 11 ወራት 1000 በሚጠጉ ሴቶችና ህፃናት ላይ የመደፈርና የመጠለፍ ጥቃቶች መድረሳቸውን አመልክተዋል፡፡
“አንድ ሺህ የሚጠጉ ሴቶች ጥቃት ደርሶባቸዋል” የህፃናት፣ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ
“ 937 ሴቶች የአስገድዶ መደፈር፣ 48 ሴቶች ላይ ደግሞ የተለፋ ጥቃት ድርሶባቸዋል፡፡” ነው ያሉት፣ በክልሉ ካለው ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ አንፃር ችግሩ ከዚህ ሊከፋ እንደሚችል ወ/ሮ አበራሽ ተናግረዋል፡፡
እየተካሄደ ባለው የአማራ ክልል ምክር ቤት ባለፉት 11 ወራት 1 ሚሊዮን 936 ሠዎች በወባ የተያዙ ሲሆን 96ቱ በጤና ተቋማት ህይወታቸው ሲያልፍ 3ሺህ 289 ሠዎች ደግሞ በኮሌራ በሽታ ተይዘው 51 ህይወታቸው እንዳለፍ ተገልጧል፡፡
የአማራ ክልል 10ኛ መደበኛ የምክር ቤት ስብሰባ የክልሉን የ2018 በጀትና ልዩ ልዩ ሹመቶችን በማጽደቅ ነገ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ነጋሽ መሐመድ
ታምራት ዲንሳ