የአማርኛ ሊቃውንት ጥናታዊ ሥራዎች ላይ ያተኮረ ጉባዔ
ሰኞ፣ መጋቢት 25 2015
አማርኛ በቴክኖሎጂ እና ሰው ሠራሽ ዕውቀት እንዲሁም የኢትዮጵያ ሊቃውንት ጥናታዊ ስራዎች ላይ ያተኮረ ጉባዔ ተካሄደ። አማርኛ ጥንታዊ ብቻ ሳይሆን፣ከቴክኖሎጂ ጋር አብሮ የሚሄድ ዘመናዊ ቋንቋ መሆኑን ምሁራን በዚሁ ጊዜ ገልጸዋል።
ተቀማጭነቱን እዚህ አሜሪካ ያደረገው፣ ኢትዮጵያዊነት የዜጎች ማስከበሪያ ድርጅት/ኢትዮጵያዊነት/፣ በግዕዝ ፊደላት አቅም ላይ ያተኮረ ተከታታይ የበይነ መረብ ውይይት እያካሄደ ይገኛል። ከዚህ ቀደም ስለ ኢትዮጲክ ማለትም ግዕዝ ፊደል ታሪካዊነት፣ የሃገር ቅርስነት፣የአፃፃፍ ስልጡንነትና ለድምፀት አመቺነት እንዲሁም ለሃገር እና ህዝብ አንድነት ስላበረከተው አስተዋጽኦ፣በዘርፉ ምሁራን ውይይት አካሄዷል።
አሁን ደግሞ አማርኛ፣ በቴክኖሎጂና ሰው ሠራሽ ዕውቀት የደረሰበትን ዕድገት የተመለከተ የምሁራን ውይይት ባለፈው ቅዳሜ አስተናብሯል። ድርጅቶቱ ስለኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ፊደላት በተከታታይ ውይይት ለማካሄድ ስለተነሳሳበት ምክንያት የድርጅቱ ሊቀመንበር ዶክተር ዕርቁ ይመር ሲያስረዱ፣የሚከተለውን ተናግረዋል።
"በእኛ በኢትዮጵያውን መኻከል፣ከሌሎች የተሻለ አቅምና ቀልጣፋነት ያለው መሆኑን ግንዛቤ ያንሳል።በዚያም ምክንያት ካለማወቅ የተነሳ የፊደሉን ጥቅምና ቀልጣፋነት በሚገባ ሁላችንም አናከብረውም።እና ያንን በሚመለከት ግንዛቤ ለመፍጠር ቀደምት ኢትዮጵያውያን ታሪካችንን ባህላችንን ሙዚቃችንን ሁሉ በብራና ጽፈው ሸክፈው ያቆዩት በዚህ ፊደል በመሆኑ የኢትዮጵያን ታሪክ ለማወቅ ይህንን ፊደል ማወቅና መገንዘብ ያስፈልጋል።እና ይህንንም ትኩረት ለመስጠት ነው።የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ከሆኑት የጥበብ ሥራዎች ከትውልድ ትውልድ ሲሸጋገር ሲሳሳብ የመጣው በዚህ ፊደል አማካይነት ነው።"
የጥንታዊ ጽሁፎችና የሥነ ፈለክ ተመራማሪ የሆኑት መጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ፣ጥንታዊ የግዕዝ መጽሐፍት በማኀበራዊ የተፈጥሮ ሳይንስ ዙሪያ በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናት፣ጥንታውያኑ መጻሕፍት ያበረከቱትን አስተዋጽኦ አብራርተዋል።
በዚህም መሰረት፣ጥናት አቅራቢው ዶክተር ሮዳስ በፍልስፍና፣በሥነ ፈለክ፣በህክምና በሥነ አራዊት እንዲሁም በማዕድን ጥናት ሰፊ የመጻሕፍት ክምችት እንዳለ አስረድተዋል። ይህም በዓለም ላይ ከ20 በላይ በሚደርሱ ዩኒቨርሲቲዎች በመጠናት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል። "ይህ እንግዲህ ብራና መጻሕፍት በየቦታው ይጠናል ማለት ነው።ይህ ጥናት ዛሬ በጣም ሰፍቶ፣ከ20 በላይ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች ግዕዝን እስከ ፒኤች ዲ ድረስ በመስጠት ይጠናል።"
የፊዚክስ ትምህርት ሊቅና የኮምፒውተር ፕሮግራመር የሆኑት አቶ ኣምሃ አስፋው ሌላው የዚህ ውይይት ጥናት አቅራቢ የነበሩ ሲሆን፣ምሁሩ የአማርኛን የስዋሰው ሕግ የተከተለ የኮምፒውተር ፕሮግራም መፍጠራቸው ተነግሮላቸዋል።
ትሁታዊ እኩለት ተልሄት(ኢኪውቫለነት ኢኩዌሽን) የተባለ መጽሐፍ መጽሐፍ ደራሲ የሆኑት አቶ ኣምሃ፣ሳይንሳዊ ቋንቋዎችን እንዴት ወደ አማርኛ መጠቀም እንደሚቻል በምሳሌ አስደግፈው አብራርተዋል።
"ይህ በብዛት የምጠቀምበት ዘዴ ስለሆነ ረዘም ያለ ትእነት/አናሊስስ/ማለት ነው ትእነት ተነተነ ከሚለው ጋር ነው የመጣው፤መጀመሪያ የእንግሊዝኛውን ዐሳብ እናጠናለን።ቃሉንም ማጥናት ይገባናል ግን ዐሳቡ ከቃሉ ይበልጥ ዋጋ አለው።ምሳሌ ዳይናሚክ የሚለው ቃል የተገኘው ኀይለኛ ከሚለው የግሪክ ቃል ነው።ርግጥ ዐሳቡ ከኀይል ጋር ቢተሳሰርም መሠረታዊ ዐሳቡ ከመጓዝ ጋርም ያለ ነው።ስለዚህ እነሱ ቃሉን ከኀይል ብቻ ስላገኙት እኛም እንደዛ ማድረግ የለብንም።ዐሳቡን እንጂ ቃሉን ብቻ ስለማንከተል።መጓዝ፣መሄድ፣መንቀሳቀስ ከተሰኙት ቃሎች ተነስተን የምንፈልገውን ቃል ለማግኘት እንሞክራለን።"
አቢሲኒካ የተባለ ቡድን በበኩሉ፣ አማርኛን በሰው ሠራሽ ዕውቀት ለትምህርት፣ለቋንቋ እና ሠነዶች ተተግባራዊነት ላይ ገለጻ አድርጓል።
በቀረቡት ጥናቶች ላይ፣ ጥያቄዎች ቀርበው ምላሽና ውይይት የተካሄደ ሲሆን፣ ኢትዮጵያዊነት ድርጅት በቀጣይም በሌሎች የተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የአፍሪቃውያኑን ጨምሮ ከቴክኖሎጂ ጋር በተየያዘ የት እንደደረሱ የሚያመላክት የውይይት መድረክ እንደሚያዘጋጅ በዚሁ ጊዜ ተገልጿል።
ታሪኩ ኃይሉ
አዜብ ታደሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ