1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሜሪካን ምርጫ ዘመቻ 2ኛ ክርክር

ረቡዕ፣ ጥቅምት 7 2005

ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ የምርጫ ቅስቀሳና ፉክክሩ ቀጥሏል። ትናንት ኒውዮርክ በተካሄደዉ ሁለተኛ የምርጫ ፉክክር ክርክር ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ባለፈዉ ከገጠማቸዉ ሽንፈት አገግመዉ ታይተዋል። በተለይም በሀገር ዉስጥ ኤኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ተፎካካሪያቸዉን ሚት ሮምኒን መብለጣቸዉ ተገልጿል። ፕሬዝደንታዊ የምርጫ ክርክሩ ሶስተኛ ዙር ይቀረዋል።

ምስል Reuters

ለፕሬዝዳትነት የሚፎካከሩት ሁለቱ ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች ትናንት ኒዮርክ ያደረጉት የፊት ለፊት ክርክር ከዚሕ ቀደም ዴንቨር ላይ ካደረጉት ብዙ የተሟሟቀ፥ የብዙዎችን ትኩረትም የሳበ ነበር።የሪፐብላካኖቹ እጩ ፕሬዝዳት ሚት ሮምኒ ከተመረጡ የፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ መስተዳድር አባባሰዉ ያሉትን የሥራ ቁጥር ለመቀነስ ቃል ገብተዋል።

«ፕሬዝዳንት ከሆንኩ አሜሪካ ዳግም እንድትሰራ አደርጋለሁ።በጀቱን አመጣጥናለሁ።ፕሬዝዳንቱ አላደረጉትም።እኔ ግን አደርገዋለሁ።የሕክምና እና የማሕበራዊ አገልግሎትን ለመጪዉ ትዉልድ በሚጠቅም መልኩ እናሻሽላለን።ፕሬዝዳንቱ ይሕን ብለዉ ነበር።ግን አላደረጉትም።ገቢያችንን አሳድጋለሁ።በነገራችን ላይ እነዚሕ ነገሮች ከዚሕ ቀደም ሰርቼያቸዋለሁ።በአገረ-ገዢነት አገልግያለሁ።መስራት እንደሚቻል አሳይቻለሁ።»

አገረገዢ ሮምኒ፥-ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማና መስተዳድራቸዉ አሸባሪነት ለማጥፋት ብዙም አልሰሩም፥ ቤንጋዚ ሊቢያ ላይ የተገደሉትን የአሜሪካ አምባሳደርና ሌሎች ዲፕሎማቶች ከጥቃት ለመከላከል አልጣሩም በማለትም ወቅሰዋቸዋል።የፕሬዝዳት ኦባማ አፀፋ ግን ታዛቢዎች እንዳሉት ለሮምኒና ለደጋፊዎቻቸዉ ጠንካራ በትር አይነት ነበር።

«ሐገራችንን ወደፊት ሥለምትራመድበት፥ መሠረታዊ ልዩነት ያላቸዉ ራዕዮች አሉ።አገረ ገዢ ሮምኒ ጥሩ ሰዉ ናቸዉ ብዬ አምናለሁ።ቤተሰባቸዉን ይወዳሉ፥ እምነታቸዉን ያከብራሉ።የዚያኑ ያክል ግን፥ ከተዘጋ በር ጀርባ ሆነዉ፥-«47 በመቶዉ የሐገሪቱ ሕዝብ ሐላፊነት መሸከምን እንቢኝ ያለ፥ ሰለባ ነዉ» ብለዉ ሲናገሩ፥ ሥለማ እንደሚናገሩ ማሰብ አለባቸዉ። ብዬ አምናለሁ።»

ክርክሩን የመራዉ የአሜሪካዉ ዓለም አቀፍ የቴሌቪዥን ጣቢያ CNN ባሰባሰበዉ የሕዝብ አስተያየት መሠረት በክርክሩ ኦባማ በአርባ ስድስት ከመቶ የመሪነቱን ሥፍራ ይዘዋል።ሮምኒ ያገኙት ሰላሳ-ዘጠኝ ከመቶ ነዉ።ምርጫዉ አስራ-አራት ቀን ነዉ-የቀረዉ።

አበበ ፈለቀ

ነጋሽ መሀመድ

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW