1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

የአሜሪካን ኢትዮጵያውያን ሕዝብ ጉዳይ ኮሚቴ(ኤፓክ) ጥሪ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 18 2015

የአሜሪካን ኢትዮጵያውያን ሕዝብ ጉዳይ ኮሚቴ(ኤፓክ)በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ዙሪያ፣ከዩናይትድስቴትስ ኮንግረስ አባላት ጋር ተወያየ። በውይይቱ ዜጎች በማንነታቸው ተለይተው የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዲቆሙ ጥሪ ቀርቧል።

US Kongress Vertreter aus Äthiopien
ምስል Ato Yome Fisseha

የኢትዮጵያውያን ኮከስ አባላት በአሜሪካ ያስተላለፉት ጥሪ

This browser does not support the audio element.

የአሜሪካን ኢትዮጵያውያን ሕዝብ ጉዳይ ኮሚቴ(ኤፓክ)በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ዙሪያ፣ከዩናይትድስቴትስ ኮንግረስ አባላት ጋር ተወያየ ። የኤፓክ ዋና ጸሐፊና የቦርድ አባል አቶ ዮም ፍሰሐ በተለይ ለዶይቸ ቨለ እንደገለጹት፣ በአሜሪካን ኮንግረስ የኢትዮጵያ ካውከስ አባላት ጋር የተካኼደው ይኸው ውይይት፣ እጅግ ውጤታማ ነበር።

አቶ ዮም እንዳሉት፣የአሜሪካን ኢትዮጵያውያን ሕዝብ ጉዳይ ኮሚቴ(ኤፓክ)፣ባለፉት ሁለት ዓመታት የኢትዮጵያን ጥቅም የሚደግፉ የኮንግረስ አባላትን በማስመረጥ፣የኢትዮጵያ ካውከስ እንደገና እንዲቋቋም አድርጓል።

"የኢትዮጵያ ካውከስ ማለት እንግዲህ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቁ፣ ስለኢትዮጵያ ጉዳይ የሚከታተለው የምክር አባላት ማለት ናቸው።ይህ እንግዲህ ከሁለቱም ፓርቲዎች ነው። ዲሞክራት ወይም ሪፐብሊካን ሊሆን ይችላሉ። ዓላማው አድርጎ የሚሰራቸው የኢትዮጵያን ጉዳይ የሚከታተሉ ስለሆኑ ነው፤ እና ለኢትዮጵያ ጠቃሚ የሆኑ ሕጎች እንዲወጣ፣ የንግድ ልውውጥ በአሜሪካና በኢትዮጵያ እንዲኖር፣ግንኙነታቸው የሁለቱ ሃገሮች ጥሩ ግንኙነት እንዲኖራቸው የሚያደርጉ የኮንግረስ አባላት፣ እነዚህ እንዲህ ነባር የሆኑ የኮንግረስ አባላት ናቸው።"

የኤፓክ አመራሮች፣ሰሞኑን ከነዚሁ የኮንግረሱ የኢትዮጵያ ካውከስ አባላት ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሄደዋል።

በዚሁ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ በተካሄደ ውይይት ላይ፣ በአሜሪካ ኮንግረስ፣ ኢትዬጲያ ካውከስ ዋና ሊቀመንበር ጆን ጋራሜንዲ እና የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር መነጋገራቸውን አቶ ዮም ተናግረዋል።

"ዋሽንግተን ዲሲ፣ኮንግረስ ሄዶ የኢትዮጵያ ካውከስ ዋና ሊቀመንበር የሆኑትን ኮንግረስማን ጆን ጋራሜንዲ እና የሥራ ባልደረቦቻችንን አግተው ነበር።በጣም ጥሩ ከቀባበል አደረጉልን። ጋራሜንዲ ፒስ ኮር ተማሪ እያሉ ኢትዮጵያ መጥተው፣ በ1960ዎቹ እ ኤ አ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰርተው የነበሩ፣ ሃገራችንን የሚወዱ ሰው ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም እንዲሆን ዴሞክራሲንና ሰብዓዊ መብት እንዲከበር በጣም የሚሹ ሰው ናቸው እና ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት በአገራችን ላይ ያለውን ችግር በመስማታቸው በጣም ማዘናቸውን ነው የገለጹልን።"

በአሜሪካ ኮንግረስ የኢትዮጵያ ካውከስ አባላት ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በተካሄደው በእዚሁ ውይይት፣ የተነሱ ዋና ዋና ጉዳዮች ምንድን ናቸው? ስንል የጠየቅናቸው፣የኤፓክ ዋና ጸሐፊና የቦርድ አባል ሲመልሱ የሚከተለውን ብለዋል።

"ዜጎች በማንነታቸው መገደል፣መታሰር፣ የቤት ማፍረስ፣ የሰብአዊ ጥሰትን ሁሉ በሚመለከት አዝኛለሁ ብለዋል፤እናም አንዳንድ ጥያቄዎች ጠየቁን።ስንት ሰው ቤት እንደደረሰበት ጠየቁን አዲስ አበባ ውስጥ ያው የምንሰማውን ነገርናቸው። እነዚህ ሰዎች ከ10 እስከ 15 ዓመት እዚህ ቤት ውስጥ እንደኖሩ፣ከእዛ ደግሞ ግብር እየከፈሉ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች በድንገት ቤታቸው እንደፈረሰ፣ እንደውም በማንነታቸው ቤቱ እንፈረሰባቸው፣ገልጸንላቸዋል።በተለያዩ ጊዜ በሃገሪቱ በሙሉ በወለጋ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ እንደተፈናቀለ፣በአጠቃላይ ወደ አራት ሚሊዮን የሚሆኑ የተፈናቀሉ ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳሉ፣ እና ብዙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖች ለረሃብ እንደተጋለጡ ሁሉ ይህን ተነጋግረናል።"

የአሜሪካ ኮንግረስ አባል ጆን ግራማንዴም፣በተነሱት አጀንዳዎች ላይ፣ ከሌሎቹ የካውከሱ አባላት፣ከአሜሪካ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት(ሴኔት)እንደራሴዎች፣ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ መንግስት ባለሥልጣናት ጋር በመነጋገር ጉዳዩን እንደሚከታተሉ የገለፁላቸው ሲሆን፣ ውይይቱ በጣም ውጤታማ እንደነበር አቶ ዮም አስረድተዋል።

ኤፓክ በቀጣይም፣በኢትዮጵያ የሚፈጸሙ ማናቸውም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና መፈናቀሎች ቆመው የተሟላ ሰላም እንዲሰፍን የሚደረገውን ጥረት የሚያግዙ ተግባራትን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ከአቶ ዮም ገለጻ ለመረዳት ችለናል።

"እስራትንና መፈናቀል እንዲቆም ነው የምንፈልገው።ሃገራችን እንድታድግ ነው የምንሻው እኛ የፖለቲካ ድርጅት አይደለንም። ነገር ግን ሃገራችን ሰላም እንዲሆን እና ህዝቡ ደግሞ ኑሮው እንዲሻሻልለት ነው የምንጥረው።ሥራችንን ወደፊት እንቀጥላለን።ኤፓክ፣ ወደፊት የኢትዮጵያን ጥቅሞች የሚያስጠብቁ የኮንግረስና የሴኔት አባላት እንዲሚረጡ፣ትውልደ ኢትዮጵያውያን ኮንግረስ ውስጥ እንዲመረጡ፣ሴኔት ላይ እንዲመረጡ፣ የማድረግ ጥረታችንን እንቀጥላለን።"ብለዋል።

ታሪኩ ኃይሉ

ታምራት ዲንሳ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW