1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ሱዳን ገቡ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 29 2013

በሁለት ቀናት የሱዳን ቆይታቸው ከጠቅላይ ምኒስትር አብደላ ሐምዶክ፣ ከሉዓላዊ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት፣ ከውጭ ጉዳይ እንዲሁም የውኃ እና መስኖ ምኒስትሮች ጋር እንደሚወያዩ የመርየም አል-ሳዲቅ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን ትናንት በአስመራ ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ተገናኝተው ነበር

Jeffrey Feltman
ምስል picture-alliance/Kyodo/MAXPPP

በምሥራቅ አፍሪካ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን ሱዳን ገቡ። ልዩ መልዕክተኛው ዛሬ ኻርቱም ሲደርሱ የሱዳን ውጭ ጉዳይ ምኒስትር መርየም አል-ሳዲቅ አል-መሀዲ ተቀብለዋቸዋል።  

በሁለት ቀናት የሱዳን ቆይታቸው ከጠቅላይ ምኒስትር አብደላ ሐምዶክ፣ ከሉዓላዊ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሉቴናንት ጄኔራል አብዱል-ፋታህ አል-ቡርሀን፣ ከውጭ ጉዳይ እንዲሁም የውኃ እና መስኖ ምኒስትሮች ጋር እንደሚወያዩ የመርየም አል-ሳዲቅ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን እና አብረዋቸው የተጓዙ ልዑካን ትናንት በአስመራ ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ተገናኝተው ነበር።

የኤርትራ ማስታወቂያ ምኒስትር የማነ ገብረ መስቀል ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና የአሜሪካው ልዩ ልዑክ ጄፍሪ ፌልትማን ለአራት ሰዓታት የዘለቀ ውይይት ማድረጋቸውን በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።

"አሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ችግሮችን ለመፍታት በምታደርገው ጥረት ኤርትራ በትብብር ለመሥራት ዝግጁነቷን" ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለአምባሳደሩ እንዳስታወቁ የማስታወቂያ ምኒስትሩ የማነ ገብረ መስቀል ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ላለው ውጥረት እና በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ላይ ለተፈጠረው አለመግባባት መፍትሔ ለመፈለግ የሚደረገውን ዓለም አቀፍ ጥረት አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን እንደሚመሩ ልዩ ልዑክ ሆነው መሾማቸው ባለፈው ሚያዝያ 16 ቀን 2013 ዓ.ም ይፋ ሲሆን የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ምኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ገልጸው ነበር።

ባለፈው ማክሰኞ ሚያዝያ 26 ቀን 2013 ዓ.ም ጉዟቸውን የጀመሩት አምባሳደሩ የመጀመሪያ መዳረሻቸው ያደረጉት የግብጽ ዋና ከተማ ካይሮን ነበር። ረቡዕ ዕለት ከአምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን የተገናኙት ፕሬዝዳንት አብዱልፋታህ አል ሲሲ "በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ምክንያት የግብጽን የውኃ ድርሻ የሚያሳንስ ማናቸውም የኢትዮጵያ እርምጃ አገራቸው እንደማትታገስ" መናገራቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።  

ከግብጽ ውጭ ጉዳይ ምኒስትር ሳሜህ ሽኩሪ ጭምር የተወያዩት የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ በበኩላቸው የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር "እንዲህ አይነቱን አሳሳቢ ጉዳይ ለመፍታት ቁርጠኛ ነው" ማለታቸው በአሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ ተጠቅሷል።

በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በከፍተኛ ኃላፊነት ያገለገሉት ጄፍሪ ፌልትማን ከጎርጎሮሳዊው 2012 እስከ 2018 ዓ.ም. ባሉት አመታት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ ነበሩ።

ልዩ መልዕክተኛው በምሥራቅ አፍሪካ ጉዟቸው ከግብጽ፣ ኤርትራ እና ሱዳን በተጨማሪ ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙ ተገልጿል።

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW