1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

የአሜሪካ ምርጫ እና የትውልደ ኢትዮጵውያን የንግድ ተቋማት ባለቤቶች ዕይታ

አበበ ፈለቀ
ዓርብ፣ ጥቅምት 22 2017

ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን የንግድ ተቋማት ባለቤቶች ኢኮኖሚውን በማነቃቃትም ሆነ የንግዱን ማህበርሰብ በመደገፍ የሪፐብሊካን ፓርቲ እና ዶናልድ ትራምፕ የተሻሉ አማራጮች መሆናቸው ላይ ይስማማሉ። ያም ሆኖ የምርጫ ውሳኒያቸው መስፈርቶች የኢኮኖሚ አቋማቸው ብቻ ሳይሆን እንደ ጤና መድህንና፣ የስደተኞች ጉዳዮች እንደሆኑም ጠቅሰዋል።

ካማላ ሐሪስ እና ዶናልድ ትራምፕ
ካማላ ሐሪስ እና ዶናልድ ትራምፕ የተፋጠጡበት የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በመጪው ማክሰኞ ይካሔዳልምስል David Swanson/Mike Blake/REUTERS

የአሜሪካ ምርጫ እና የትውልደ ኢትዮጵውያን የንግድ ተቋማት ባለቤቶች ዕይታ

This browser does not support the audio element.

በአሜሪካው የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውስጥ አንዱ አብይ ጉዳይ ኢኮኖሚው እንደመሆኑ የንግድ ትቋማት እና የንግዱ ማህበረሰብ ሚና ወሳኝ እንደሆነ ተገለጸ። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን የንግድ ተቋማት ባለቤቶች ኢኮኖሚውን በማነቃቃትም ሆነ የንግዱን ማህበርሰብ በመደገፍ የሪፐብሊካን ፓርቲ እና ዶናልድ ትራምፕ የተሻሉ አማራጮች መሆናቸው ላይ ይስማማሉ። ያም ሆኖ የምርጫ ውሳኒያቸው መስፈርቶች የኢኮኖሚ አቋማቸው ብቻ ሳይሆን እንደ ጤና መድህንና፣ የስደተኞች ጉዳዮች እንደሆኑም ጠቅሰዋል።

በመጪው ማክሰኞ የሚደረገው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ልክ እንደማንኛውም የአሜሪካ ዜጋ ሁሉ ለንግዱ ማህበረሰብም መስቀለኛ መንገድ ሆኗል። የዋጋ ግሽበቱ፣ የግብር ፖሊሲው፣ እና መሰል ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ሁሉንም አስጨንቀዋል።

በቅርቡ በተደረግ መጠይቅ አብዛኛወቹ የንግድ ተቋማትና ባለሃብቶች የዋጋ ግሽበቱና መሰል የእኢኮኖሚ አለመረጋጋቶች ዋና ትኩረቶቻቸው እንደሆኑ ያሳያል። ሃያ በመቶ የሚሆኑ የንግድ ባለቤቶች ደግሞ ለየትኛው እጩ፣ የትኛውን ጉዳይ መነሻ አድርገው ድምጻቸውን እንደሚሰጡ አልወሰኑም።

ትራምፕ ዳግም ቢመረጡ ለአፍሪቃ ምን ማለት ይሆን?

የተለያዩ የንግድና የቢዝነስ ተቋማት ባለቤቶች የሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያ አሜሪካውያንም በዘንድሮው፣ አጣብቂኝ ውስጥ የገባ በመሰለ ምርጫ ላይ ያላቸውን አስተያየትና እሳቤ ጠይቄያለሁ።
ማህፉዝ ሙመድ እዚህ ቨርጂኒያ ውስጥ የሬሜዲ የግብር አገልግሎትና የማህፉዝ የመድን ዋስትና ድርጅት ባለቤት ነው። ማህፉዝ ሁለቱም እጩ ተፎካካሪወች ለመምረጥ አስቸጋሪ መሆናቸውን ጠቁሞ፣ ሪፐብሊካኖች ኢኮኖሚውን በማንቀሳቀስ ረገድ የተሻለ አማራጭ እንዳላቸው ይስማማል።

ምክትል ፕሬዝደንት ካማላ ሐሪስ እንደ ጄኒፈር ሎፔዝ ያሉ ዕውቅ ድምጻውያንን በመጋበዝ የምረጡኝ ዘመቻዎቻቸውን ሲያካሒዱ ቆይተዋል።ምስል Evelyn Hockstein/REUTERS

ያም ሆኖ ማህፉዝ ድምጼን ለማን ልስጥ በሚለው ጥያቄ ላይ የበለጠ ወሳኞቹ ጉዳዮች ከስደተኛ ጉዳዮች፣ ከጤና ዋስትናና መሰል አቋሞች ጋር የተያያዙ በመሆናቸው ወደ ዲሞክራቶች ሊያዘነብል እንደሚችል ገልጿል።

ማሕደረ ዜና፣ የዩናይትድ ስቴትስ ምርጫና የዕጩዎቹ የዉጪ መርሕ

ወ/ሮ ሰላም ተፈራ በሜሪላንድ ውስጥ የሬስቶራንት ባለቤት ናቸው። ምርጫ በመጣ ቁጥር ሁሉም እጩ ተወዳዳሪ የመራጩን ቀልብ ለመሳብ የማይገባው ቃል ስለሌለ፣ ተግባራቸውን ከተመረጡ በኋላ የምናየው ነው ብለዋል። ለኢኮኖሚውና ለንግዱ ማህበረሰብ ግን ሪፐብሊካኖችና ዶናልድ ትራምፕ እንደሚሻሉ ገልጸው ድምጻቸውንም ለሪፐብሊካኖች ለመስጠት እንደሚያመዝኑ ገልጸዋል።

ወ/ሮ ሰላም በተለይ ዲሞክራቶች ጋር ያለያያቸው ሪፐብሊካኖች ለኢኮኖሚውና ለንግዱ ማህበረሰብ ያላቸው ድጋፍ ብቻ ሳይሆን በተለይ ዲሞክራቶች ከእኛ ባህል ጋር የሚጣረስ አቋም መያዛቸው ጭምር ነው ባይ ናቸው።

ዶናልድ ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ ለመመለስ በሚያደርጉት የምረጡኝ ዘመቻ የቀድሞው የፎክስ ቴሌቭዥን ጣቢያ ባልደረባ ተከር ካርልሰን ያሉ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎችን ድጋፍ እየተጠቀሙ ናቸው። ምስል Brendan McDermid/REUTERS

አቶ ለማ ጌታቸው ክሊቭላንድ፣ ኦሃዮ ውስጥ በርካታ ትላልቅ አፓርትመንቶችና ህንጻወች በመገንባት በሪል ስቴት ቢዝነስ ውስጥ ተሰማርተዋል። አቶ ለማ ዶናልድ ትራምፕና ሪፐብሊካኖች ለኢኮኖሚውም ሆነ ለቢዝነስ የተሻለ አማራጭ እንደሚያመጡ ተናግረው፣ እሳቸው ግን በዚህ ምርጫ ላይ ለሌሎች የጤናና የስደተኞች ጉዳዮች ትኩረት እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

ስለ ካማላ ሐሪስ የምርጫ ቅስቀሳ መዝጊያ ጎናጭ ንግግር ቃለ-መጠይቅ

በሬስቶራንት ቢዝነስ ውስጥ ያሉት አቶ ሲሳይ ድማሙም እንደንግድ ድርጅት ባለቤት ብቻ ሳይሆን እንደግለሰብም የምርጫ መስፈርቱ የእጩወቹ ግለሰባዊ ስብዕናና ግብረገብ መሆኑን ይናገራሉ። እናም ሁለቱም እጩወች የየራሳቸው ችግሮችን የተሸከሙ መሆናቸው አንዳቸውንም የመምረጥ ፍላጎት እንዳላጨረባቸው ይናገራሉ።

ከማላ ሃሪስም ሆኑ ዶናልድ ትራምፕ እንደ ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ አይነት የንግድ ማህበረሰብን ቀልብ ለመግዛት የምረጡኝ ዘመቻቸውን አጧጡፈዋል። የነዚህ ግለሰቦች ድምጽም የነገውን አዲስ አስተዳደር የኢኮኖሚ አቅጣጫ በመወሰኑ ረገድ ሚና አለው።

አበበ ፈለቀ 
እሸቴ በቀለ
ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW