1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቀዳማዊት እመቤት ጂል ባይደን የአፍሪቃ ጉብኝት

ሐሙስ፣ የካቲት 16 2015

የአሜሪካ ቀዳማዊ እመቤት ጂል ባይደን በትናንትናው ዕለት ናምቢያ ገብተዋል።ቀዳማዊ እመቤቷ በሚያደርጉት የአምስት ቀናት የአፍሪቃ ጉብኝት ወደ ኬንያም ያቀናሉ ተብሏል።ጉብኝቱ በአህጉሪቱ ያለውን የአሜሪካ አጋርነት ለማጠናከር ያለመ ነው ቢባልም፤ አንዳንድ ተንታኞች ግን በአፍሪቃ የቻይና እና የሩስያን ተጽዕኖ ለመመከት ነው ይላሉ።

US-Midterm - Jill Biden
ምስል Jacquelyn Martin/AP/picture alliance

ጉብኝቱ የሩሲያና ቻይናን ተፅዕኖ ለመመከት ነው ተብሏል

This browser does not support the audio element.

 

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ባለፈው አመት  በዋሽንግተን ዲሲ 50 የሚጠጉ የአፍሪካ መሪዎች የተገኙበት የአሜሪካ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ አካሂደዋል።በዚህ ወቅትም በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር በመመደብ የአፍሪቃን ዲሞክራሲ በፋይናንስ ለመደገፍና ለማጠናከር ማቀዳቸውን  ይፋ አድርገዋል። ፕሬዝዳንት ባይደን በጎርጎሪያኑ በ2023 ዓ/ም አፍሪካን እንደሚጎበኙ በጨረፍታ ገልፀው ነበር። ያም ሆኖ እሳቸው በትናንትናው ዕለት የዩክሬን ዋና ከተማ ኪቭ ሲገቡ፤ ባለቤታቸው ደግሞ ወደ አፍሪቃ አቅንተዋል። 
የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ቀዳማዊት እመቤት ጂል ባይደን የአምስት ቀናት የአፍሪካ ጉብኝታቸውን ለመጀመር ትናንት ናሚቢያ ገብተዋል።ቀዳማዊ እመቤቷ ቀጣዩ የጉብኝት አቅጣጫቸው ወደ ኬንያ ሲሆን፤ ጉብኝቱ በአህጉሪቱ ያለውን የአሜሪካ አጋርነት ለማጠናከር ዋሽንግተን ባለፈው ዓመት በገባችው ቃል መሰረት ነው ተብሏል። 
አንዳንድ ተንታኞች ግን ጉብኝቱ ሩሲያ በአፍሪካ እያሳየች ያለውን ተጽእኖ ለመመከት የሚደረገው ጥረት  አካል እንደሆነ ያምናሉ። ኬንያዊው የፖለቲካ ተንታኝ ፕሮፌሰር ሙኔኔ ማቻሪያን በዚህ ይስማማሉ። እሳቸው እንደሚሉት ጉብኝቱ የቻይና እና የሩስያ ተጽዕኖን ለመከላከል የተደረገ  ነው ።
«ታውቃለህ፣ በሆነ መንገድ የማግባባት እና የመከላከል አይነት ነገር  ነው። ምክንያቱም ምዕራባውያን በቻይናውያንም ሆነ በሩሲያውያን እየተሸነፉ ነው። ቻይናውያን በመዋዕለ ንዋይ ፍሰት መስክ  ሩሲያውያን ደግሞ ከጦርነቱ አንፃር, ዩክሬንን እየመሩ ነው።ሩሲያ ስለ አፍሪካ መንግስታት ግንዛቤ ያላት ይመስላል።» 

ምስል Michael Reynolds/Pool via CNP/picture alliance

ፕሮፌሰር ማቻሪያን እንደሚሉት ይህንን አጀንዳ ለማሳካት የቀዳማዊ እመቤቷ አፍሪቃን በውል የመረዳት ሁኔታ ላይ ይወሰናል። ምክንያቱም እሳቸው የአህጉሪቱን ሁኔታ  በደንብ ከተገነዘቡ የባይደን አስተዳደር ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር እና ሩሲያ እና ቻይና በቀጣናው ውስጥ ያላቸውን ተፅዕኖ ለመቀነስ የሚወሰደውን ርምጃ በደንብ እንዲገነዘብ ይረዳል። 
«እሷን ይሰማት ይሆናል። በዚህ መሰረት አንዳንድ ማስተካከያዎችን ያደርግም ይሆናል። ቀዳማዊት እመቤቶች ሁል ጊዜ ይፋዊ ባልሆነ መንገድ ሁለተኛ ቦታ ላይ ያሉ ናቸው። ምክንያቱም ባይደን ምን እየተካሄደ እንዳለ ለማወቅ በመሞከር ላይ ችግር አለባቸው። እሷ ከማንም በተሻለ ሁኔታ ልታስረዳው ትችል ይሆናል።  ከዚያም ማስተካከያ ለማድረግ በጣም ፍላጎት ካለው፤ በአፍሪካ ውስጥ የዩናይትድ ስቴትስን ምስል እንዴት ማሻሻል እና ማስተካከል እንደሚችል ይገነዘባል።»
ናሚቢያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ጉብኝቱን አስመልክቶ ትናንት ባወጣው መግለጫ የቀዳማዊ እመቤቷ ጉብኝት ሴቶች እና ወጣቶችን በማብቃት፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት እና የጋራ ዲሞክራሲያዊ እሴቶችን በማስተዋወቅ ላይ ያተኩራል ። በዚህም መሰረት ከእያንዳንዱ ሀገር ቀዳማዊ እመቤቶች ጋር በመገናኘት በወጣቶች ተሳትፎ  በሴቶችን ማብቃት እና ፆታ ላይ የተመሰረቱ ጥቃቶችን ለመከላከል ከሚሰሩ ድርጅቶች ጋርም ውይይት ያደርጋሉ። የፖለቲካ ተንታኙ እንደሚሉት እንዲህ አይነቱ ተግባር በቅንነት ከተሰራ ልዩነትን ለማጥበብ ይረዳል።
«በአጠቃላይ ሰዎች በቅን ልቦና የሚሰጥ ድጋፍን ይሻሉ,። እናም በዩናይትድ ስቴትስ ላይ ምንም ዓይነት ጥላቻ እንዳይኖራቸው ያድርጋል። በየትኛውም ደረጃ አንዳንድ ልዩነቶችን ለማጥበብ ማድረግ የሚቻለው በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ በማተኮር ለምሳሌ የሴቶችን አቅም ማጎልበት፣ወጣቶችን ማብቃት እና ወደፊት ራሳቸውን መደገፍ እንዲችሉ ማድረግ ነው።»
ቀዳማዊ እመቤት ጂል ባይደን ቀደም ሲል  አፍሪቃን ለስድስት ጊዜ ያህል የጎበኙ ቢሆንም ቀዳማዊ እመቤት ሆነው ሲጎበኙ ግን ይህ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነው። 

ምስል Sarah Silbiger/REUTERS

ፀሀይ ጫኔ
ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW