የአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት ድጋፍ መቆም፣ ቀጣዩ ጠቅላላ ምርጫ እንዲሁም የሲቪክ ድርጅቶች ሚና
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 28 2017
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት (USAID) የገንዘብ ድጋፍ መቋረጥ ሲቪል ድርጅቶች ለቀጣዩ ዓመት ጠቅላላ ምርጫ በሚያደርጉት ሥራ ላይ ተጨባጭ ጫና ማሳደሩ እንደማይቀር አስታወቀ።ሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች በዚህ ድጋፍ መቆም ምክንያት የደረሰባቸው ተጽዕኖ በዝርዝር እየተጠና መሆኑንም የምክር ቤቱ ኃላፊ ገልፀዋል።
መንግሥትልዊ ላልሆኑት ድርጅቶች ፈቃድ የሚሠጠው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን በበኩሉ ሁሉም ሲቪል ድርጅቶች በአሜሪካ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ ሲደረግላቸው የነበሩ ፕሮጀክቶች፣ የጊዜ ገደባቸው፣ በጀታቸው እና የድጋፉን መቋረጥ ተከትሎ የተቀነሱ ሠራተኞቻቸውን ብዛት እንዲያሳውቁት ጠይቋል።//
ኢትዮጵያየአሜሪካ የተራድዖ ድርጅት (USAID) ባለፈው የግሪጎርያን 2024 ብቻ ለኢትዮጵያ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርጎ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። ሀገር በቀል ሲቪል ድርጅቶች በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና እና በሌሎች መስኮች ከሚያከናውኗቸው የልማት ተግባራት አብዛኛዎቹ ከዚሁ ድርጅት በሚገኝ የሀብት ምንጭ የሚሠሩ ስለመሆኑ ይነገራል።
በተመሳሳይ በሰብአዊ መብት፣ በፍትሕ፣ በዴሞክራሲ ጉዳዮች ላይ የተሰማሩ ሲቪል ድርጅቶች በቀጣይ ምርጫ ላይ ዘርፈ ብዙ ሚና የሚኖራቸው ቢሆንም የድጋፉ መቋረጥ ቀላል ግምት የሌለው ዐሉታዊ ጫና እንደሚያሳድር የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አህመድ ሁሴን ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።
ኃላፊው አክለውም "ባሉን አንዳንድ መረጃዎች ምርጫው ላይ ሊሠሩ ይችላሉ" ሲሉ ድጋፉ ምርጫን በመሰሉ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ተቋርጦ እንደማይቀር ፍንጭ መኖሩን ጠቁመዋል።
በውጭ ድጋፍ እና እርዳታ ጥገኛ የሆነው የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ምህዳር በተለይም ጠቅላላ ምርጫ ሲቃረብ የሰብአዊ መብት እና የዴሞክራሲ ዕድገት ላይ ደጋፊ ተግባራትን የሚያከናውኑ የሲቪል ድትጅቶች ቁልፍ ሚናቸው እንዳይደናቀፍ ያሰጋል።
የቪዥን ኢትዮጵያ ኮንግረስ ሥራ አስኪያጅ ታደለ ደርሰህ ረጂዎች ገንዘብ ለመልቀቅ "መጀመርያ ሀገራችሁ ሰላም ይስፈን" የሚል ቅድመ ሁኔታ እያስቀመጡ መሆኑን ጠቅሰው፣ ያም ሆኖ በእርዳታ የሚፀና የዴሞክራሲ ባሕል የለም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አህመድ ሁሴን ከዚህ በፊት ለዶቼ ቬለ እንዳሉት በአሜሪካ ድጋፍ መቋረጥ ምክንያት የአብዛኞቹ ሲቪል ድርጅቶች ሥራቸው ተደናቅፏል። በምርጫ ላይ የሚሠሩትም ከዚህ እንደማይርቁ ነው የሚታመነው።
"በተለይ በ ኤች አይ ቪ፣ በሳንባ ነቀርሳ - ቲቪ፣ በተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት ላይ ይሠሩ የነበሩ ድርጅቶች በሙሉ ከ 90 በመቶ በላይ ተሰርዘዋል። ባለን ክትትልም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በርካታ ክልሎች ላይ መጠነ ሰፊ የሆነ ፕሮጀክት ይዘው አንዳንዶቹ 10 ሚሊየን ዶላር፣ ሰባትም፣ አምስትም የሦስት አራት ዓመት ተከታታይ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችል ውለታ ገብተው እየሠሩ ነው የነበረው።"
ሲቪል ድርጅቶች ያስተምራሉ፣ ያነቃሉ፣ የቅድመ፣ ምርጫ ሂደት እና ድህረ ምርጫ ሁኔታን ይከትልተላሉ፣ የመራጮች መብት እንዲከበር፣ ፍትሐዊ እና ትክክለኛ ምርጫ ስለመከናወኑም ይከታተላሉ። ይህ ያለ ውጭ ሀገራት የሀብት ድጋፍ እና እገዛ የሚቻል ግን አይደለም። በዚህ ረገድ ሀብት ከውስጥ እንዲሰበሰብ መንግሥት ቁርጠኛ መሆን አለበት የሚለው መከራከርያ ይነሳል።
ምርጫ በተቃረበ ጊዜ ሁሉ በየሆቴሎች የሚሰጡ ልዩ ልዩ ስልጠናዎች፣ የሚደረጉ ስብሰባዎች፣ በልዩ ልዩ ርዕሶች ይፋ ይደረጉ የነበሩ የጥናት ውጤቶች በተለይ ከአሜሪካ ድጋፍ መቋረጥ ወዲህ መቀዛቀዝ ስለመስተዋሉ ዘገባዎች ያሳያሉ።
ይህ ሁኔታ የጎላ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ እንቅስቃሴ ከማይስተዋልበት ከዚህ ወቅት ተዳምሮ በመጪው ምርጫ ላይ ስለሚኖረው ተጽዕኖ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስተያየት እንዲሰጥበት ለማድረግ ተደጋጋሚ ጥረት ብናደርግም ምላሽ አላገኘም።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብድርጅቶች ባለሥልጣን የአሜሪካ ድጋፍ መቋረጥን ተከትሎ ሁሉም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተለይ ከ ዩ ኤስ ኤይድ ድጋፍ ያገኙ የነበሩት በዚሁ እርዳታ ተክለውት የነበረን ፕሮጀክት ርዕስ፣ የጊዜ ገደብ፣ ዘርፉን፣ የበጀት መጠኑን፣ የፕሮጀክቱን ተጠቃሚዎች ብዛት እንዲሁም ሥራው በመዘጋቱ ምክንያት የተቀነሱ ሠራተኞችን ብዛት እንዲያሳውቁ ጠይቋል።
ሰለሞን ሙጬ
ነጋሽ መሐመድ
ማንተጋፍቶት ስለሺ