1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ መግለጫ

ማክሰኞ፣ መስከረም 10 2015

ተፋላሚ ኃይላት ወደ ሰላማዊ ድርድር የሚመጡበትን ሁኔታ ለመፍጠር በኢትዮጵያ የ10 ቀናት ቆይታ አድርገው የተመለሱት በአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር የተፋላሚዎቹ ቁልፍ ልዩነት የእርሰ በርስ መተማመን አለማዳበር ነው አሉ።

USA/Äthiopien Mike Hammer US-Sonderbeauftragter am Horn von Afrika
ምስል Seyoum Getu/DW

«በበይነ መረብ የተደረገ መግለጫ»

This browser does not support the audio element.

በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልእክተኛ ማይክ ሐመር ከጳጉሜ 01 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ዋሽንግተን ዲሲ እስከተመለሱበት መስከረም 06 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ለ10 ቀናት በኢትዮጵያ ቆይተዋል። በዚህ ጊዜም በኢትዮጵያ መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት ሰላማዊ እልባት እንዲያገኝ ሲያበረታቱ መቆየታቸውን ሐመር አብራርተዋል። ልዩ መልዕክተኛው በቆይታቸው ስለቀጣዩ የሰላም ውይይት ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት፣ ከአፍሪካ ህብረት እና ዓለም አቀፍ አጋሮች ካሏቸው ጋር ሲመክሩ መቆየታቸውንም ዛሬ ከቀትር በኋላ ለጋዜጠኞች በበይነ መረብ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አመልክተዋልም።

ስለሰሜን ኢትዮጵያ አሁናዊ ሁኔታ እና ስለ መፍትሄው በተሳታፊ ጋዜጠኞች የተጠየቁት ሐመር የኤርትራ ሠራዊትም ጭምር የተሰለፉበት ጦርነት እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

«የኤርትራ ሠራዊት የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ ለጦርነት መሰለፉ ያሳስበናል፤ እንቃወማለንም። የትኛውም የውጭ ተዋናይ የኢትዮጵያን የግዛት ሉዓላዊነት ማክበር ጦርነቱ እንዳይቀጣጠል ያግዛል። ስለዚህ ጉዳይ ከአስመራ ጋር ቀጥታ የምንወያይ ነው የሚሆነው። ጦርነቱ በኢትዮጵያ የትግራዋይ፣ አማራ እና አፋር ህዝብን ሰቆቃ ያበዛል። ይባስ ብሎ የኤርትራ ሠራዊት በዚህ ላይ መሳተፍ ሌላኛውን አስከፊ ሁኔታ እንዳያስከትል እንሰጋለን። » ሲሉም ተናግረዋል።

ምስል Minasse Wondimu Hailu/AA/picture alliance

ሐመር ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሓማት እና ከህበረቱ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴንጉን ኦባሳንጆ ጋር አሜሪካ የሰላም ጥረቱን ልትደግፍ በምትችለበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን በመግለጫቸው አንስተዋል። ከተመድ ዋና ጸሐፊ ልዩ መልዕክተኛ ሐና ቴተህ እና ከአውሮፓ ህበረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አኔተ ቬበር ጋርም በጉዳዩ ላይ መክረው ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ጠቁመዋል። የመስከረም 01 ቀን 2015ቱ የትግራይ ኃይሎች የሰላም ጥሪን ተከትሎ በኢትዮጵያ መንግሥት የተሰጠው ምለሽ አለመኖሩ እና ጦርነቱን ተከትሎ በቀጣይስ ምን ሊከተል ይችል ይሆን የሚል ጥያቄም ቀርቦላቸው፤ «የትግራይ ኃይሎች በቅርብ ጊዜው የመስከረም አንዱ መግለጫቸው ተኩስ አቁም በማድረግ የትም ቦታ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመደራደር ጥሪ ማቅረባቸው ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት ቁርጠኛ ናቸው ብለን ነው የወሰድነው። ግን ከዚያም በኋላ የቀጠለው ጦርነት በእርግጥ አሳስቦናል። ዩናይትድ ስቴትስ የተጀመረውን የሰላም ጥረት በተለይም በአፍሪካ ህብረት የሚመራውን የሰላም ሂደት ለመደገፍና ተፋላሚ ኃይላት ወደ አንድ ጠረጴዛ እንዲመጡ በቁርጠኝነት ትሠራለች። ከኦባሳንጆ ጋር በነበረን ውይይትም እንደ ዩ.ኤስ ያሉ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አካላት ለሰላም ሂደቱ የበኩላቸውን እንዲጫወቱ ነው የጠየቁን።» ሲሉ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ማይክ ሐመር ለግጭቱ ዘላቂ መፍትሄ ሊሆን የሚችለው በተፋላሚ ኃይላት መካከል ሊፈጠር በሚችለው መተማመን እና በኢትዮጵያውያን በራሳቸው ነው ሲሉም የጦርነቱን ዘላቂ መፍትሄ አመላክተዋል።  «መፍትሄው መምጣት ያለበት ከኢትዮጵያውያን ከራሳቸው ነው። ሀገራቸው እኮ ነው። በዚህ ውስጥ የዩናይትድ ስቴትስ ሚና ይህን ከባድ ጊዜ እንዲያልፉ በጠንካራ ዲፕሎማሲ ማገዝ ነው። ተስፋ የምናደርገውም ተፋላሚ ኃይላቱ ከአውዳሚው ጦርነት ወጥተው ተስፋ እና ብልጽግና ወደ ሚያመጣው ሰላም ይመጣሉ የሚለውን ነው።» ብለዋል።

ምስል Solomon Muchie/DW

በኢትዮጵያ ተፋላሚ ኃይላት ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ የማይመጡ ከሆነና ሰብዓዊ ቀውስን የሚያስቀጥለው ጦርነት ከላባራ ምናልባት አሜሪካ እንደማዕቀብ ያሉ አማራጮችን ትመለከት ይሆን የተባሉት ልዩ መልዕክተኛው «ቀዳሚው ትኩረታችን ዲፕሎማሲ ነው» ሲሉ መልሰዋል። «ተፋላሚዎቹ ወደ ሰላም እንዲመጡ ዩናይትድ ስቴትስ የተለያዩ አማራጮችን ትመለከታለች፤ ለጊዜው ግን ዋና ትኩረታችን በዲፕሎማሲ ላይ አብዝተን መስራት ነው። እንደ የአውሮፓ ህብረት እና የአፍሪካ ህብረት ያሉ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ጋር እየሠራን ያለነውም ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ነው።» ሲሉም አክለዋል።

አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰላማዊ ድርድሩ ዝግጁ መሆን ማረጋገጡን እና የህወሓት ኃይሎች መስከረም 01 ቀን 2015ዓ.ም. ያስተላለፉትን የሰላም ጥሪ ትደግፋለች የሚሉት ሐመር፤ ከተፋላሚ ኃይላት መተማመን ሰፍኖ ወደ ድርድር መሄድ ይጠበቃል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ልዩ መልዕክተኛው በአዲስ አበባ የአሜሪካ አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰን ጋር ሆነው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ከምክትል ጠ/ሚኒስተር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዲሁም ሌሎች ባለሥልጣናት ጋር ባደረጉት ውይይትም በሰሜን ኢትዮጵያ የጦርነቱ ዳግም ማገርሸት ብሎም የኤርትራ ኃይሎች በጦርነቱ መሳተፍ እንዳሳሰባቸው እንዳብራሩላቸው እና በአፍሪካ ህብረት ስር እየተካሄደ ያለው የሰላም ጥረቱ እንዲፋጠንና ለጦርነቱ መቋጫ እንዲያበጅ እንደጠየቋቸውም ገልጸዋል።

ምስል Seyoum Getu/DW

«ተፋላሚዎችን ወደ አንድ ለማምጣት ዋናውና መሰረታዊው ጉዳይ መተማመንን በሂደት መገንባት ነው። በጦርነቱ በተሰቃየው ህዝብ መካከልም ይህን የመተማመን ስሜት ማስረጽ ያስፈልጋል። ያን መተማመን የሚያመጡ ሂደቶችት ላይ ነን አሁን።» በማለትም ጦርነቱን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ተስፋን አሳይተዋል። ማይክ ሐመር ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በተጨማሪ ከትግራይ ክልል ባለሥልጣናትም ጋር ያልተገደበ ሰብዓዊ ድጋፍ በጦርነት ተጎጂ አካባቢዎች ላይ እንዲዳረስ ሰብዓዊ መብትም እንዲከበር አጽእኖት መሰጠቱን ነው ያመለከቱት። «ዩናይትድ ስቴትስ የኢትዮጵያን አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንደምታከብር እና ኢትዮጵያውያንን የሚጠቅም ዘላቂ ሰላም እንዲኖር ትሻለችም» ብለዋል፤ ልዩ መልዕክተኛው በፕሬዝዳንት ጆይ ባይደን በኃላፊነቱ በተሾሙበት ጥቂት ወራት ውስጥ በኢትዮጵያ ያደረጉት ሦስተኛ ጉብኝታቸው መጠናቀቅን በማስመልከት በሰጡት መግለጫ።

ሥዩም ጌቱ 

ነጋሽ  መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW