1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሜሪካ ዴሞክራሲ

ሰኞ፣ ጥር 8 2015

በ1859 መጨረሻ አፈ ጉባኤ ለመምረጥ በተነሳ ዉዝግብ ምርጫዉ ሁለት ወር ፈጅቶ ነበር።በ163ኛ ዓመቱ ዘንድሮ ረጅም ጊዜ የፈጀ ምርጫ ተደረገ።4 ቀን።ለ14ኛ ዙር ድምፅ ከተሰጠ በኋላ እንደራሴ ኬቪን ማክካርቲ የአፈ ጉባኤነቱን ስልጣን የያዙት በ15ኛዉ ዙር፣ ትራምፒስት የሚባሉት 20 የፓርቲቸዉ እንደራሴዎች ያቀረቡትን ቅድመ ሁኔታ ተቀብለዉ ነዉ።

USA Repräsentantenhaus | Wahl des Sprechers
ምስል Liu Jie/Xinhua/picture alliance

የአሜሪካ ዴሞክራሲ፣የሕግ ስርዓትና ፖለቲከኞችዋ

This browser does not support the audio element.

የአዲሱ ዓመት ጅምር ለአሜሪካ ለፖለቲከኞች የመልካም ምኞት፣ የተስፋ፣ የዕቅድ፣ ብቻ አይደለም።በዉጪ መርሐቸዉ ሩሲያን የሚያክል ጠላታቸዉን አንድም አሜሪካዊ ሳይሞት፣በ55 ቢሊዮን ዶላር ወጪ፣ በዩክሬኖች ሕይወትና ዉድመት እያዳከሙ ነዉ።ድፍን አዉሮጳን እየነዱ ነዉ።የዋጋ ግሽበትንና የኮሮና ስርጭትን ተቆጣጥረዉታል።ሪፐብሊካኖች የሕግ መምሪያ፣ ዴሞክራቶቹ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቶችን በበላይነት ይመራሉ።የኃይል ሚዛን ተመጣጥኗል።መጥፎ ዓይደለም።ብዙ አለመቆየቱ እንዲጂ ክፋቱ።ሪፐብሊካኑ በአፈ-ጉባኤ ምርጫ ይነታረኩ ገቡ።ዴሞክራቶቹ በተቀናቃኞቻቸዉ ክፍፍል አፊዘዉ ሳያበቁ፣ በፕሬዝደንታቸዉ ቅሌት አንገታቸዉን ደፉ።የቀድሞዉን ፕሬዝደንት ተመሳሳይ ቅሌት የሚመረምረዉ የፍትሕ አካል ያሁኑንም ፕሬዝደንት ቅሌት ለማጣራት ይባትል ያዘ።This is America----ይሉናል።ላፍታ በግርድፉ እንቃኛቸዉ።
                              
ኢትዮጵያዊዉ ፖለቲከኛ አባዱላ ገመዳ መስከረም 2003 የምክር ቤት አፈ-ጉባኤነቱን መዶሻ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጨብጡ፣ መገረምን ከትልቅ ፈገግታ በቀየጠ ስሜት ተዉጠዉ፣ መዶሻዉን እያገላበጡ ሲመለከቱ በቴሌቪዥን መስኮት አይተን ነበር።የመገረም፣ መፍገግ፣ ማገላበጣቸዉ ሰበብ ምክንያት ትንሿ መዶሻ ቁመት፣ ግዝፈት፣ ሥልጣናቸቸዉን አለመመጠኗ ሊሆን፣ ላይሆንም ይችላል።
ምክንያታቸዉን አልነገሩንም።ነግረዉንም ከሆነ አልሰማንም።አዲሱ የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ኬቪን ኦዉን ማክካርቲም ልክ እንደ አባዱላ ሁሉ መዶሻቸዉን እያገላበጡ ተመለከቱ፣ ሳቁ።አሳቁ።አስጨበጨቡም።
                                
«ቀላል ነበር---ሐህ።ይህን ያክል ይሆናል ብዬ አላሰብኩም።የአናሳዎቹ መሪ ጄፍሪስ አመሰግናለሁ።ሐኪም፣ ላስጠነቅቅሕ እፈልጋለሁ።ከሁለት ዓመት በፊት ከኔ ጉባኤ ያገኘሁት  100 በመቶ (ድምፅ) ነበር»
ጥር 7፣2023 (ከዚሕ በኋላ ያለዉ ዘመን በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ።) ዩናይትድ ስቴትስ በሐብት ብዛት፣ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ስርፀት፣በጉልበትም ከዓለም አንደኛ ናት።የዚያኑ ያክል የብዙ ሐገር ተወላጆችን አሰባጥራ የምታኖር፣ ደሐን-ከቱጃር፣ ስስታምን ከለጋሽ፣ ደጎችን-ከነብሰ ገዳዮች፣ ሐቀኞችን-ከወንጀለኞች፣ ቅኖችን-ከአጭበርባሪዎች ቀይጣ የያዘች ሐገርም ናት።
ብዙ በመበደርም የሚያክላት የለም።በቅርቡ የወጣ ዘገባ እንደሚያመለክተዉ ከ31 ትሪሊዮን በላይ ዕዳ ያናጥርባታል።ይሕቺን ግዙፍ፣ልዕለ ኃያል፣ ሐብታም፣የተቃርኖ ቅይጥ ሐገርን የሚዘዉረዉ መንግስታዊ ስርዓት የሚያስተናብራቸዉ ሶስት ቅርንጫፎች፣ ሕግ አዉጪዉ፣ ሕግ አስፈፃሚና ተርጓሚዉ ብዙ አዋቂዎች እንደሚያምኑበት፣ ግልፅ መስመር፣በሕግ የተገደበ ስልጣንና ልዩነት አላቸዉ።
የመንግስትነቱን ሥልጣን የሚፈራረቁበት ግን ሁለት የፖለቲካ ማሕበራት ብቻ ናቸዉ።ለዘብተኛዉ የዴሞክራቲክ ፓርቲና ወግ አጥባቂዉ የሪፐብሊካን ፓርቲ። አምና ሕዳር በተደረገዉ የግማሽ ዘመን የምክር ቤት አባላት ምርጫ የዴሞክራቱ እንደራሴዎች ሕግ መወሰኛዉን (ሴኔት)፣ የሪፐብሊካኑ  የሕግ ምምሪያዉን (በልማዱ ሐዉስ) ምክር ቤቶችን  አብላጫ ቁጥር መያዛቸዉ ሕግ የማዉጣቱን የሚያመጣጥን፣የክትትልና ሚዛን የማስጠበቅ (Check and Balanace) ሥርዓትን የሚያጠናክር ተደርጎ ተወድሶ ነበር።
ግን አንድ ፓርቲን የወከሉ፣ አንድ ዓላማና መርሕ አነገብን የሚሉ፣ባንድ ዘመን የተመረጡ፣ ያንድ ምክር ቤት እንደራሴዎች አንድ መሪ ለመምረጥ ሲከፋፈሉስ?ዘንድሮ ዩናይትድ ስቴትስ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዉስጥ የማይሆን የሚመስለዉ ሆነ።
በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ የያዘዉ የሪፐብሊካን እንደራሴዎች ተከፋፈሉ፤ ፅንፈኛ፣ወይም በቀድሞዉ ፕሬዝደንት ስም አፍቃሬ ትራም (ትራምፒስት) የሚባሉት እንደራሴዎች በተቀሩት ላይ አምፀዉ ለምክር ቤቱ አፈ ጉባኤነት ለታጩት እንደራሴ ድምፅ አሰጥም አሉ።
ለዩናይትድ ስቴትስ ፖለቲከኞች መከፋፈል በርግጥ እንግዳ አይደለም።በ1859 መጨረሻ የያኔዉን የምክር ቤት አፈ ጉባኤ ለመምረጥ በተነሳ ዉዝግብ ምርጫዉ ሁለት ወር ፈጅቶ ነበር።በ163ኛ ዓመቱ ዘንድሮ ረጅም ጊዜ የፈጀ ምርጫ ተደረገ።4 ቀን ወሰደ።ለ14ኛ ዙር ድምፅ ከተሰጠ በኋላ እንደራሴ ኬቪን ማክካርቲ የአፈ ጉባኤነቱን ስልጣን የያዙት በ15ኛዉ ዙር፣ ትራምፒስት የሚባሉት 20 የፓርቲቸዉ እንደራሴዎች ያቀረቡትን ቅድመ ሁኔታ ተቀብለዉ ነዉ።
የዩናይትድ ስቴትስን ፖለቲካ የሚያጠኑት ፕሮፌሰር ስኮት ሉካስ እንደሚሉት የአክራሪዎቹ ወይም ትራምፒስት የሚባሉት እንደራሴዎች እርምጃ አፈ ጉባኤዉን ከማገት የሚቆጠር ነዉ።ለወደፊቱም ምክር ቤቱን ሊያሽመደምዱት ይችላሉ።
«እነሱ (አክራሪዎቹ) አሁን ምክር ቤቱን ማሽመድመድ፣ ምናልባትም ጨርሶ ማንኮታኮት ይችላሉ።ምክር ቤቱን ካሽመደመዱትና ሥራዉን እንዳያከናዉን ካደረጉት ለአሜሪካ ፖለቲካዊ ሥርዓት ከባድ ፈተና ነዉ።የዛሬ ሁለት ዓመት ትራምፕ ሥልጣን እንደያዙ እንዲቀጥሉ ለማድረግ በምክር ቤቱ ሕንፃ (ካፒቶል)ን ካጠቁ ወዲሕ የሚፈልጉት ይሕንን ነዉ።»
ማክካርቲ የአክራሪዎቹን ድምፅ  ለማግኘት ከተቀበሉት ቅድመ ግድታ ጥቂቱ ፣በአፈ ጉባኤዉ ላይ መታመኛ ድምፅ እንዲሰጥ ከምክር ቤቱ አባላት አንዱ ከጠየቀ ድምፅ ይሰጣል።እያንዳዳቸዉ አክራሪ እንደራሴዎች በምክር ቤቱ ዋና ዋና ኮሚቴዎች ዉስጥ ይሾማሉ።በተለይ በሕግ ኮሚቴዉ ዉስጥ የማፅደቅና ድምፅን በድምፅ የመሻር ስልጣን ይኖራቸዋል።
ሶስተኛዉ ደግሞ ፕሮፌሰር ሉካስ እንደሚሉት ምክር ቤቱ መደበኛ ሥራዉን ከመስራት ይልቅ አሉባልታና ሴራን በማጣራት እንዲጠመድ የሚያደርግ ነዉ።
                                                       
«መዘንጋት የሌለበት ሌላዉ ጉዳይ ማክካርቲ በሴራ ትወራና ላይ የተመሰረቱ አልቡላታዎችን ለማረጋጋጥ በስብሰብና የእማኞችን ቃል በመቀበል የምክር ቤቱንም የራሳቸዉንም ጊዜ  እንዲያጠፉ ተብትቦ የሚይዝ ነዉ።ስለ ባይደኖች፣ስለ ኮሮና ተሕዋሲ፣ትራምፕ ስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ከስልጣን ሊያስወግዷቸዉ ሞክረዋል ስለተባሉ ግዛቶች ወዘተ--- ምክር ቤቱ በነዚሕ ላይ ሲነታረክ ስለጤና፤ስለትምህርት፣ስለስደተኞች ስለ ምጣኔ ሐብት ሁነኛ መርሕ እንዳይቀርፅ ያደርጉታል።»
የካሊፎርኒያዉ የቀድሞ ሳንዲዎች ቸርቻሪና የእሳት አደጋ ሰራተኛ የዩናይትድ ስቴትስን ሶስተኛ ትልቅ ስልጣን ያዙ።አባታቸዉ የእሳት አደጋ ሰራተኞች አለቃ ነበሩ።በፖለቲካዉ አባታቸዉም እናታቸዉም የዴሞክራቲክ ፓርቲ አባላት ነበሩ።እሳቸዉ እንዳባታቸዉ የእሳት አደጋ መከላከያን ሥራ ሞከሩት ግን አልቀጠሉበትም።
ፖለቲካን የተቀየጡትም የወላጆቻቸዉን ርዕዮተ ዓለም ተቃርነዉ የሪፐብሊካኑ ፓርቲ አባል ሆነዉ ነዉ።ያባታቸዉን ሥራ አልወደዱትም፣ የፖለቲካ አቋማቸዉን ይቃረናሉ።ምክራቸዉን ግን አልዘነጉም፣ይፍልጉታልም።
«አባቴ ሁል ጊዜ የሚነግረኝ አስፈላጊዉ ነገር አጀማመርሕ አይደለም፣ አጨራረስሕ እንጂ እያለ ነበር።አሁን ለአሜሪካ ሕዝብ ጠንክረን መፈፀም አለብን።»
የቀድሞዉ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ 320 የሚስጥር ሰነድ እቤታቸዉ ደብቀዉ በመገኘታቸዉ ለፍርድ እንዲቀርቡ ፕሬዝደንት ጆሴፍ ባደንና የዴሞክራቲክ ፓርቲ ፖለቲከኞች አጥብቀዉ እየተሟገቱ ነዉ።የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ አቃቤ ሕግና የፌደራሉ የምርመራ ቢሮ (FBI) ልዩ ባለሙያዎች መድበዉ ጉዳዩን እየመረመሩ ነዉ። 
በዚሕ መሐል የናረዉ የሪፐብሊካኑ የምክር ቤት እንደራሴዎች  ዉዝግብ ገለል፣ቀለለ፣ሰከን ማለቱ ሲነገር የፕሬዝደንት ጆሴፍ ባይደን የሚስጥር ሰነድ የመደበቅ ቅሌት ተጋለጠ።ለአሜሪካኖች አዲስ  ርዕስ፣ ለ80 ዓመቱ አዛዉንት ድርብ ዉርደት፤ለሪፐብሊካኖች ጠንካራ ዱላ፣ ለዴሞክራቶች ማፈሪያ ሆነ።አፈ ጉባኤ ማክካርቲ የመጀመሪያ ትልቅ ስራቸዉን አገኙ።
«ደሕና፣ ይህ እንግዴሕ ባንድ ራስ-ሁለት ምላስን የሚያሳይ፣ የአሜሪካ ሕዝብ መንግስቱን እንደማያምንም የሚያረጋግጥ ነዉ።የሕግ መምሪያዉ ምክር ቤቱ ልዩ መርማሪዉን ጨምሮ ሁሉም የሐገሪቱ የፍትሕ ስርዓት ክፍልን ሥራና አሰራርን በበላይነት የመከታተል ገለልተኛ ሕገ-መንግስታዊ ግዴታ አለበት።»

ምስል DW
ምስል Rod Lamkey/ZUMA Press/IMAGO
ምስል Evelyn Hockstein/REUTERS

ሕዳር 2፣ 2022 የፕሬዝደንት ጆ ባይደን ጠበቃ ዋሽግተን በሚገኘዉ ፔን ባይደን በሚባለዉ የባይደን የግል ቢሮ ዉስጥ በየሰንዱቁ የታጨቁ ሰነዶችን ሲያገላብጡ አናታቸዉ ላይ «ልዩ ሚስጥር» የሚል ፅሁፍ የሰፈረባቸዉን ወረቀቶችን አገኙ።ከዚያ በሕዋላ ዴልዌር ከሚገኘዉ መኖሪያ ቤታቸዉ፣ከቢሮና ከገራዣቸዉ  ሳይቀር ተመመሳሳይ ሰነዶች ይጎለጎሉ ጀመር። 
ሰነዶቹ ፕሬዝደንት ባይደን የፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ምክትል በነበሩበት ዘመን የተመሰጠሩ ናቸዉ።ስለ ዩክሬን፣ስለኢራን፣ስለ ብሪታንያ የሚያወሱና የአሜሪካ መንግስትን አቋም የሚዘረዝሩ ናቸዉ።በአሜሪካ ሕግ መሰረት «ሚጥስጥር» ፣«ብርቱ ሚስጥር» እና «ልዩ (ክላሲፋይድ) ሚስጥር» የሚባሉ ሰነድና መረጃዎች የሚመለከተዉ ባለስልጣን ሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ በየመስሪያ ቤቱ ከማየት ዉጪ በየግል ቤቱ ወይም ቢሮዉ መዉሰድና ማስቀመጥ አይፈቀድለትም።ፕሬዚደንት ጆ ባይደንም አላደረኩም ባይ ናቸዉ።

ምስል Saul Loeb/AFP/Getty Images

«ስለተገኘዉ ጉዳይ ተነግሮኛል።እዚያ ቢሮ ዉስጥ የመንግስት ሰነድ የያዘ ነገር መኖሩን መስማቴ አስገርሞኛል።በሰነዱ ዉስጥ ስላለዉ ነገር የማዉቀዉ የለም።ጠበቆቼም ሰነዱ ስለያዟቸዉ ጉዳዮች እንድጠይቅ አልጠቆሙኝም።»
ብዙ ሰዉ ሰማቸዉ ያመናቸዉ ግን ጥቂት ደጋፊያቸዉ ወይም ምንም ነዉ።የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጉዳዩን የሚያጣራ ልዩ መርማሪ ሰይሟል።የሪፐብሊካኖቹና የዴሞክራቶቹ ፖለቲከኞች አንዱ ሌላዉን ለማሳጣት የሚያደርጉት ሩጫም እንደቀጠለ ነዉ።
በሳምንቱ ምብቂያ ከወደ ኒዮርክ የተሰማዉ ዜና ግን ዴሞክራቶቹ በሪፐብሊካን ተቀናቃኞቻቸዉ ላይ ለሚተኩስት ቃላት ተጨማሪ አረር መሆኑ አልቀረም።ኒዮርክ ያስቻለዉ ፍርድ ቤት በታክስ ማጭበበር በተከሰሱት በፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ኩባንዮች ላይ የ1.6 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት ጥሏል።
ነዉጠኛዉ፣ ቱጃር ፖለቲከኛ ግን በ2024 ለሚደረገዉ ምርጫ ለመወዳደር እየተዘጋጁ ነዉ።ባይደንም ይወዳደራሉ ነዉ የሚባለዉ።ሁለቱም ግን በይፋ አላሳወቁም።በትራምፕ ዘመን የፀጥታ አማካሪ ሆነዉ የሰሩት ጆን ቦልተን  የሁለቱም ቅሌት በክብደት-ቅለት መመዘኛ ቢለያይም «ሁለቱንም ለፕሬዝደንትነት ከመወዳደር የሚያግዳቸዉ መሆን ነበረበት።» ይላሉ።ብዙዎች ግን አያግዳቸዉም ባዮች ናቸዉ።ምክንያቱም  It is America----ይሉሐል።

ምስል Evan Vucci/AP Photo/picture alliance

ነጋሽ መሐመድ 

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW