1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ዕጩዎች የፖሊሲ ዕይታ

ዓርብ፣ ጥቅምት 1 2017

አሜሪካውያን መራጮች አዲሱ ፕሬዝደንታቸውን ለማምረጥ ጥቂት ቀናት በቀራቸው በአሁኑ ወቅት ዕጩዎቹም ፖሊሲዎቻቸውን በስፋት በማስተዋወቅ ላይ ይገኛሉ። ሁለቱን ዕጩ ፕሬዚዳንቶች ካማላ ሃሪስንና ዶናልድ ትራምፕን ያፋጠጠው፣ የዘንድሮው የአሜሪካ ፕሬዚንታዊ ምርጫ፣ ከፍተኛ ፉክክር የሚታይበት እንደሚሆን ይጠበቃል።

ካማላ ሃሪስ እና ዶናልድ ትራምፕ
የዘንድሮው የአሜሪካ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ እጩ ተፎካካሪዎች ካማላ ሃሪስ እና ዶናልድ ትራምፕምስል Andrew Caballero-Reynolds/AFP/Getty Image | Alex Wong/Getty Images

የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ዕጩዎች የፖሊሲ ዕይታ

This browser does not support the audio element.

ፕሬዚዳንታዊ ዕጩዎቹ፣ ዲሞክራቷ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስና ሪፐብሊካኑ ዕጩ ዶናልድ ትራምፕ፣ የውጭ ጉዳይን በተመለከት የጎላ የፖሊሲ ልዩነት ባይኖራቸውም፣ የአሜሪካን የውስጥ ጉዳይን በተመለከተ የየራሳቸው የሆነ አቅጣጫ መንደፋቸውን፣ የዶይቸ ቨለ ዘጋቢ ያነጋግራቸውና በአሜሪካ የሚኖሩ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ። 

ሁለቱን ዕጩ ፕሬዚዳንቶች ካማላ ሃሪስንና ዶናልድ ትራምፕንያፋጠጠው፣ የዘንድሮው የአሜሪካ ፕሬዚንታዊ ምርጫ፣ ከፍተኛ ፉክክር የሚታይበት እንደሚሆን ይጠበቃል።

የውጭ ጉዳየ ፖሊሲ አቅጣጫ

በኒውዮርክ ስቴት ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ቢኒያም አዋሽ፣ የምርጫ ዘመቻውን አስመልክተው በሰጡን አስተያየት፣ ማናቸውም ቢመረጡ በተለይ አፍሪቃን በተመለከተ እንደወትሮው የተለየ የፖሊሲ አቅጣጫ አይጠበቅም ነው የሚሉት።

«የእነሱ መመረጥ፣ ዶናልድ ትራምፕ  ወይም ካማላ ሃሪስ ብዙም ዓይነት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ልዩነት አያመጣም። የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የዲሞክራቲክ ፓርቲውም ሆነ የሪፐብሊካን ፓርቲው የቆመበት ዋና ዋና ትኩረት፣ ቻይና እና ሩሲያ በተመለከተ ነው። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ በመካከለኛው ምሥራቅ ምዕራብ እስያ ያለው ብሔራዊ ጥቅማቸው ነው። ስለዚህ እነዚህ ናቸው ዋናው ትኩረታቸው»።

አንገብጋቢው የስደተኞች ጉዳይ

በዘንድሮው ምርጫ ሁለቱን ዕጩዎች በከፍተኛ ደረጃ እያወዛገቡ ካሉ ጉዳዮች መካከል፣ ስደተኞችን በተመለከት ያላቸው አቋም ነው። በተለይ የዶናልድ ትራምፕ የዘመቻ ቡድን፣ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ፣ የተለሳለሰ አቋም በመያዝ ችግሩ እንዲባባስ አድርገዋል በማለት የሰላ ሂስ ይሰነዘሩባቸዋል።

ፕርፌሰር ቢኒያም ከዚህ አኳያ፣ የሪፐብሊካን ፓርቲውን ዕጩ ዶናልድ ትራምፕ አቋም እንደሚከተለው ፈትሸውታል።

«በጣም ሻይለኛ የሆነ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኀበረሰብ ቀውስ አለ። እናም ለዚህ መፍቻ ነው የሚባለው አንዱ ያለ ሕጋዊ ዶክመንት (ሰነድ) የሚገቡት በተለይ በሜክሲኮ አድርጎ ያንን የማቆም ጉዳይ ስለዚህ ምንድነው ፖለቲካው የጥላቻ በተለይ ዘር ተኮር የሆነ ጥላቻ የፖለቲካ የሆነ አረማመድ እና አካሄድ ነው ያሰቡት እንጂ ተጨባጭ ለአሜሪካ ሕዝብ ለምሳሌ ኢንቨስትመንት፣ ሥራ መፍጠር፣ ትምህርት፣ ጤና ለሁሉም በተገቢው እንዲደረስ ዓይነት ፖሊሲ የላቸውም፤እንደውም በተቃራኒው ነው ያለው»።

በዘንድሮው የአሜሪካ ፕሬዝደentawi ምርጫ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ መነጋገሪያ እና የክርክርም ነጥብ መሆኑ እየተገለጸ ነው። ምስል Carlos A. Moreno/picture alliance/ZUMA Press Wire

በዲሞክራቲክ ፓርቲው ዕጩ ምክትል ፕሬዝደንት ካማላ ሃሪስ በኩል የሀገር ውስጥ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው እይታስ ምን ይሆን?

«በሃሪስ በኩል፣ ዲሞክራቲክ ብዙ ጊዜ አቋማቸው በተቻለ መጠን ለሕዝብ የሚቀርብ አንዳንድ ጠቀሜታ ሥራ መንግሥት መሥራት እንዳለበት ያምኑበታል»።

«ፕሮጀክት 2025»

የኢትዮጵያ አሜሪካዊያን የሲቪክ ድርጅቶች ሊቀመንበር አቶ መስፍን መኮንን፤ ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘውና የጋዜጠኞች የሙያ ድርጅት የሆነው የናሽናል ፕሬስ ክለብ ባልደረባም ናቸው።የቀድሞ ፕሬዚዳንት ቢመረጡ፣ ገቢራዊ አድርገዋለው የሚሉትና «ፕሮጀክት 2025» የተባለውን ሰነድ በተመለከተ፣ አቶ መስፍን ተከታዩን አስተያየት ለዶይቸ ቨለ ሰጥተዋል።

«ፕሮጀክት 2025 የተባለው የተነደፈው እንደምታውቀው፣ በራሱ በትራምፕ ታማኞችና የቀድሞ አስተዳደር ባለሥልጣናት ነው የተሳተፉበት፤ እና ይኼ በጣም አደገኛ የሆነ ሁኔታ ነው»።

ዶናልድ ትራምፕ በፕሮጀክት 2025 ከነደፏቸው ዕቅዶች መኻከል፣ የትምህርት ሚኒስቴር መስሪያ ቤትን ማፍረስ እንደሚፈልጉ ያስታወቁበት ይገኝበታል። ዜጎች የሚጠቀሙባቸው የማኀበራዊ ዋስትና ጥቅማ ጥቅሞችም ወደ ግል ለማዞርም ወጥነዋል ይላሉ አቶ መስፍን።

«አሁን እኮ እንደ ሶሻል ሴኩሪቲ ዓይነት ሁሉ ወደ ግል አዛውረን ልናቀርብ ነው እያሉ ነው። ሶሻል ሴኩሪቲ ለሁሉም አሜሪካዊ የተዘጋጀና ለወደፊት ሥራ ሠርቶና ለፍቶ የተረፈውና ያጠራቀመው ነው።ያንን እንደገና አይተው ወደ ግል ለማዞር እያሰቡ ነው። እዚህ ፕሮጀክት 2025 ላይ፤ እንደዚህ ዓይነቱ በጣም አደገኛ ነው አካሄዳቸው፣ ለምሳሌ የትምህርት ዲፓርትመንት የሚባለውን ሙሉ ለሙሉ አጥፍቶ ሌላ ዓይነት ስትራቴጂ ለማውጣት ነው»። ብለዋል።

ታሪኩ ኃይሉ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW