የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ጥሪ፤የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ጫና፤ትራምፕ የውጭ እርዳታ እንዲቆም ማዘዛቸው
ሐሙስ፣ ጥር 22 2017
አምነስቲ ኢንተርናሽናል በአማራ ክልል የሚካሄደው የጅምላ እስር እንዲቆም በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና እንዲያደርግ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጥሪ አቅርቧል፣ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ኑሮን እንዳከበደባቸው ለዶቼቬለ ተናግረዋል። አዲሱ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸው የውጭ እርዳታ መስጠት እንድታቆም ያስተላለፉት ትዕዛዝ ኢትዮጵያን እንደሚጎዳ ከወዲሁ እየተነገረ ነው።
በኢትዮጵያ ከጥቂት ሳምንት በፊት የነዳጅ ዋጋ መጨመሩ የኑሮውን ጫና ማክበዱን ዶቼቬለ በተለያየ ጊዜያት ያነጋገራቸው የተለያዩ ከተሞች ነዋሪዎች ተናግረዋል ። ከዋጋ ጭማሪው ጋር የነዳጅ እጥረቱ ተደምሮ በትራንስፖርት አገልግሎት በግብርና በፋብሪካ ውጤቶችና በሌሎችም ምርቶች ላይ ያስከተለው የዋጋ ንረት ነዋሪዎችን አማሯል። የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ባስከተላቸው ችግሮች ላይ አስተያየታቸውን በፌስቡክ ካሰፈሩት አንዱ አንዋር ዋሴ
«የዋጋ ጪማሪው ሳይሆን የቸገረን ፣ነዳጅ በተለይ ቤንዚን በማደያዎች ስለጠፋ ነው ሲሉ ምክንያቱንም ገልጸዋል። ቸርነት አባይነህ በአጭሩ በጣም ከባድ ነው ሲሉ እሸቱ አብነት ደግሞ የትራንስፖርት ዋጋ እጅግ መጨመሩን ጠቅሰው ግን ወዴት እየሄድን እንደሆነ አልገባኝም የሚል ጥያቄ አቅርበዋል። ወሎ ደሴ በሚል የፌስቡክ ስም የተጻፈ አስተያየት«ከዚህ ቀደም የሳንቲም ጭማሪ ሲደረግ የዋጋ ንረት መጣብን እንልን ነበር። አሁን ግን የዋጋ ጭማሪውን ለማስላት ይከብዳል። በጥቂት ዓመታት ከ18 ብር ተነስቶ 101 ገባ። አሁን ያለው የዋጋ ግሽበት ሳይሆን የኑሮ ውድመት ነው። ኑሯችን እየወደመ ነው።መሄጃ አጥተናል ሲል ያማርራል ። ገዛኽኝ ገብሬ «የሕዝባችን ትከሻ ድንቅ ነው።» ሲሉ ሚ ማንቼ ማንቼ ደግሞ « በቀን አንዴ መብላት አቃተን እኮ ! ፍትህ ለደሀው! ማኅበረሰብ የሚል ጥሪ አቅርበዋል። የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች ከመጠን በላይ የዋጋ ጭማሬ አድርገዋል ያሉት አቡ ጀዌን ችግሩም ይሄን የሚቆጣጠር ፤ ጉዳዩ ይመለከተኛል የሚል አካል አለመኖሩ መሆኑን ገልጸዋል።የነዳጅ ዋጋ መጨመር ያስከተለው የዋጋ ንረት
ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ መንግሥት በአማራ ክልል መጠነ -ሠፊ ዘመቻ የከፈቱበትን 4ኛ ወር ምክንያት በማድረግ በዚህ ሳምንት አጋማሽ ባወጣዉ መግለጫ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በኢትዮጵያ የሚፈጸመውን የሰብአዊ መብት ጥሰት አይቶ እንዳለየ ማለፉን እንዲያቆም ጠይቋል። የኢትዮጵያ መንግስት ያለፍርድ ቤት ዉሳኔ ያሰራቸዉን ሰዎች ዓለም አቀፍ ዕዉቅና ባለዉ ፍርድ ቤት እንዲያቀርብ ወይም እንዲለቅ የመብት ተሟጋቹ ድርጅት ጥሪ አቅርቧል።
በዚህ ዘገባ ላይ በፌስቡክ ከተሰጡ አስተያየቶች አንዱ የአቢቡዋል ያምራል አጭር አስተያየት ነው።«ለእውነት፣ለሰብዓዊነት የቆመ ሰው ሁሉ ሊደግፈው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በእስሩ ምክንያት እየተንገላቱ ያሉ ሰዎችንና ቤተሰቦቻቸውን ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡» አባይ ወዲያ ማዶ አባይ ወዲያ ማዶ ደግሞ ቢዘገይም ጥሩ መነቃቃት ነው።ሲሉ አየነው ፈረደ «እውነት ነው በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን በደል አይቶ እንዳላየ ማለፍ በጣም ያሳፍራል። የአለም ሥርአት ተደፍቋል.። የሚለው ደግሞ የኩን ፈየኩን ኢላሂ አስተያየት ነው።በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ተፅዕኖ እንዲደርግ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ
ዩናይትድ ስቴትስ ባለፈው ዓመት ብቻ ግጭት፣ ድርቅ እና የምግብ ዋስትና እጦት ለገጠማቸው ኢትዮጵያውያን የሕይወት አድን ርዳታ ለማቅረብ 676 ሚሊዮን ዶላር ወጪ አድርጋለች። ይሁንና አዲሱ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸው የምትሰጠው ይህን መሰሉ ርዳታ ለ90 ቀናት እንዲቆም ያሳለፉት ትዕዛዝ ካሁኑ በኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ ተዘግቧል።ዶቼቬለ ትራምፕ ያሳለፏቸው ይህን መሰል ውሳኔዎች በኢትዮጵያ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራሉ? ሲል ባቀረበው ዝግጅት ላይ በፌስቡክ የተለያዩ አስተያየቶች ተሰጥተዋል።
አብዛኛዎቹ እርዳታው ሀገሪቱን ከመለወጥ ይልቅ ወደ ኋላ እንድትሄድ ያደረገ ስለሆነ ቢቀር አይጎዳንም የሚሉ ናቸው። ከመካከላቸው የአብርሃም በንቴ አስተያየት«እርዳታ ሃገርን ሲቀይር ያየነው ፣አውሮጳ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኃላ ያገኘችው ማርሻል ፕላን ብቻ ነው በተረፈ እርዳታ ሃገርን ሲያደቅ እንጂ ሲያለማ አልታየም ለጥቁሮች ብቸኛው መፍትሄ እራስን በራስ መቻል አለቀ»ይላል። ታደሰ ንጉሴ «ከጥገኝነት ወጥተንና በራስ አቅም ከልመና የምንላቀቅበት ጥሩ አጋጣሚ ይዞልን ሊመጣ ይችላል። ሲሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል። «አሜሪካ አይደለም ለዘጠና ቀን ለዘጠና አመት ድጋፏን ብታቆም ለዚህ ምስኪን ማህበረሰብ ምንም አይቀርበትም!!!» የሚለው ደግሞ የመልካሙ አበባው አስተያየት ነው።
የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ውሳኔዎች በኢትዮጵያ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራሉ?
አሳዬ አመኑ በለጠ እርዳታው መቆሙ ኢትዮጵያ እራሷን በራሷ እንድትችል ያደርጋታል» ሲሉ አቢ ሲሉ «በአሜሪካ ተማምኖ የተፈጠረ ሀገር የለም እንደውም በዚህ አጋጣሚ እንደ ሀገር ሌሎች አማራጮችን የሚናይበትን እድል ሊፈጥርልን ይችላል ሁሌም በተረጂነት ስሜት ታስረንና እየተሸማቀቅን መኖር ሊያበቃለት ይገባል።» ብለዋል።«ምንም ተጽእኖ አያሳድርም» ሲሉ በልበ ሙሉነት ሀሳባቸውን የጀመሩት መሸሻ ሶስና ደስታ ደግሞ «ኢትዮጵያን የሚያሳድራት፣ የሚመግባት እግዚአብሔር ነው፤ ራሷ አሜሪካ ለራሷ ትወቅ እኛ እግዚአብሔር አለን አይጥለንም» በማለት መተማመን በአሜሪካ ሳይሆን በእግዚአብሔር ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል። ካሳ ደሳለኝ ሽሮ በበኩላቸው« በምንችለዉ አቅም መረዳዳት እንጅ ከታላቋ አሜሪካ የሚገኝ ነገር የለም።» በማለት እቅጩን ተናግረዋል።
ኂሩት መለሰ
ፀሐይ ጫኔ